ግቢው ! ዩኒቨርስቲው !!
(አሥራደው ከፈረንሳይ)
እንዳልነበሩበት – ተናዳፊ ንቦች ፤
ለህዝባቸው ጥቃት – ዘብ ቆሞ አዳሪዎች ፤
የዕውቀትን ጥበብ – ትምህርት ቀስመውበት፤ ለለውጥ ሃዋሪያነት – ሃሳብ ላመኑበት፤
በአንድላይ ተነስተው – እንዳልተመሙበት፤
ዘመን አሳልፎ – ዘመንን ደርቶ ፤
ሳየው ይገርመኛል ግቢው አንቀላፍቶ ፤ ግቢው አንኮራፍቶ ::
” ፋኖ ተሰማራ – ፋኖ ተሰማራ ፤ ”
” እንደነ ሆ ቺ ሚን – እንደ ቼ ጉቬራ ፤ ”
“መሬት ላራሽ ይሁን – ገባርነት ይጥፋ ፤ ”
” የድሃ ልጅ ይማር – ትምህርት ይስፋፋ ፤
” ሃሳብን በሃሳብ – እያሞሻለቅን፤ ትምህርት እንማር – እንቅሰም እውቀትን ::
ማለቱ ቀረና !
የአይምሮ ባዶነት – የሃሳብ ድህነት፤ የህሊና ዝገት – ሃሞተ ቢስነት ፤
ተደማምረውበት – ጎሣ_ ዘረኝነት ፤
ይታያል ተኝቶ – ግቢው አንቀላፍቶ ፤
ግቢው አንኮራፍቶ ::
የባዶነት ስሜት – ኳኳታ _ ኳኳታ ፤
የውስጣዊ ቁሸት – ክርፋት _ ክርፋት ሽታ፤
ቂም በቀል ጥላቻ – ተደማምረውበት፤
ይታያል ተኝቶ – ግቢው አንቀላፍቶ፤
ግቢው አንኮራፍቶ ::
ዘመን አሳልፎ – ዘመንን ሸኝቶ ፤
የዘርና_ ጎሣ – ድሪቶ ደርቶ ፤
ሳየው ይገርመኛል – ግቢው አንቀላፍቶ ፤
ግቢው አንኮራፍቶ ::
ኩርር !! ኩርር !! ኩርር !!
አንድ ቀን
በአገራችን ኢትዮጵያ፤ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች፤ በተማሪዎች መሃከል ያለው ፤ የዘርና የጎሣ፤ የቂም በቀል ጥላቻና ብጥብጥ፤ ህወሓትና አጋሮቹ፤ የዘር ፖለቲከኞች ለ30 ዓመታት፤ ተክለው እየኮተኮቱ ያሳደጉት ቁልቋል ውጤት ነው ::
የዘርና የጎሣ ፖለቲካ አቀንቃኞችና ካድሬዎቻቸው፤ ወጣቱን አይኖቹን ብቻ ሳይሆን፤ አይምሮውንም በዘርና በጎሣ መሃረብ ከልለው በማደናበር፤ ወጣቱን አመክነዋል፤ አገራችንንም ገድለዋል ::
የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች የሠረቁት፤ የአገራችንን ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን፤ የወጣቱን ህልምና ዕድሜ፤ የአገራችንንም ሠላምና ልዕልና ጭምር ነው ::
የራሳቸውን ዕድሜ አገባደው፤ በወጣቱ ዕድሜ ገበጣ የሚጫወቱትን፤ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች፤ ወጣቱ በአብሮነቱ ጸንቶ በመተባበር በቃ ሊላቸው ይገባል ::
መማር ማለት፤ የአስተሳሰብ አድማስን በማስፋት፤ በአብሮነት ማማ ላይ ሆኖ ፤ አርቆ በማስተዋል፤ ዛሬን በሠላም እየኖሩና እየተማሩ፤ ነገን በተስፋ በማለምለም ፤ ለራስ፤ ለቤተሰብና ለአገር ዋልታ መሆን ነው ::
በግጥም ያቀረብኳት ወቀሳዬን ሰምቶ፤ ወጣቱ በአብሮነት ማማ ላይ ሆኖ፤ እጅ ለእጅ በመያያዝ፤ አገር ገዳይ ትውልድ ከመሆን ይልቅ ፤ አገር ገንቢ የመሆን ተስፋንው እንዲሰንቅ ምኞቴ ነው ::