
ዘሩን አጩሆ የሚጠራ ግለሰብና ጥንብ የያዘ ጅብ ..

ቅድስት ወንደሰን
* ብዙዎች ላንቃቸው እስኪነቃ ለመንደራቸው ይጮሃሉ ፤ ስለጎጣቸው ይዘምራሉ ። ወንዛቸውን ያመልካሉ ። ስለ ሌላው ወንዝ መድረቅ ፣ ስለ ወዲያኛው ቀዬ መጎስቆል ይተጋሉ ። ከዚያኛው መንደር ቅዱስ ይልቅ የራሳቸው መንደር እርኩስን ይቀድሳሉ ። የጎጣቸው ካልሆነው ሊቅ ይልቅ የጎጣቸውን ደንቆሮ ያነግሳሉ….
—-
ሕወሓት በ27 አመታት የዘራብን ዘረኝነት እንደ ካንሰር እየሰረሰረ እንደ አንድ አካል የነበርነው ኢትዮጵያውያንን ቆራርጦ ወደ መንደር ቅርጫት ውስጥ እየወረወረን ይገኛል ። በዚህም የአንድነታችን ጥብቀት ወደ ጥልቁ የመከፋፈል አሮንቋ ሲያዘግም በየእለቱ እያየን ነው ።
.
ብዙዎች ላንቃቸው እስኪነቃ ለመንደራቸው ይጮሃሉ ፤ ስለጎጣቸው ይዘምራሉ ። ወንዛቸውን ያመልካሉ ። ስለ ሌላው ወንዝ መድረቅ ፣ ስለ ወዲያኛው ቀዬ መጎስቆል ይተጋሉ ። ከዚያኛው መንደር ቅዱስ ይልቅ የራሳቸው መንደር እርኩስን ይቀድሳሉ ። የጎጣቸው ካልሆነው ሊቅ ይልቅ የጎጣቸውን ደንቆሮ ያነግሳሉ ። የሰው መመዘኛው ስነምግባሩ ፣ የስራ ልምዱ ፣ ታማኝነቱ ፣ የትምህርት ዝግጅቱ ሳይሆን ” የማን ብሔር ነው ? የማን ዘር ነው ? ” የሚለው ነው ፤ አለያም አጥንትና ደሙ ነው ። አጥንት ፣ ስጋና ደም ለሰው ልጅ ማክበሪያነትም ሆነ ማቅለያነት የሚያገለግል መስፈርት ሆኗል ። በአንዳንዶች ዘንድ አጥንትና ደም እንዲሁም ስጋ ከሐይማኖትም በላይ እየተመለኩ መጥተዋል ።
.

.
ዘረኝነት ፍፁም አንድ ልንሆንበት በሚገባን ጉዳይ ላይ እንኳ ለያይቶ ሲያቆመን እያየን ነው ። ጠ/ሚንስትር አብይ ባሸነፉት የኖቤል ሽልማት እንኳ ….. ሽልማቱን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ደስታቸውን በአደባባይ ሰልፍ ሲገልፁ ይህ ስሜት በተመሳሳይ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች አልታየም ። በሌላ መልኩ በደንቢ ዶሎ ስለታገቱት ተማሪዎች መላው አማራ በሰልፍ ተቃውሞውን ሲያሰማ ይህም በሌላው ክልል አልታየም ። በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በፅንፈኞች ከፎቅ ላይ ጭምር እየተወረወሩ ሲገደሉ ” የሟች ብሔር ነኝ ! ” የሚለው ወገን ሙሾ ሲያወርድ ” የኔ አጥንትና ደም አይደለም ” የሚለው ደግሞ ሲሳለቅ ታይቷል።
.
ማፈናቀል ዘር እየተቆጠረ ሆኗል ፣ አፈናቃይም በዘር የተደራጀ ቡድን ሆኗል ። ከፖለቲካና ከአመለካከት ውጪ ሰዎችን እያሰባሰበ ያለው አጥንትና ደም መሆኑ በዝቷል ። የጋሪዮሽ ዘመን አስተሳሰብ እንኳ ያለው ቢሆን ዘሩን እስከተቀኘ ድረስ የአጨብጫቢ መንጋን ከየጎሬው መጥራት ይችላል ። ቀድሞውንም ከዘሩ ውጪ አስተሳሰቡ የሚጠየቅበት መድረክ አይኖርም ። በአሁኑ ወቅት በአገራችን ዘሩን አጩሆ የሚያቀነቅን ግለሰብና ጥንብ ይዞ የሚጮህ ጅብ አንድ ናቸው ። ሁቱም አብዝተው በጮሁ ቁጥር አይን ጨፍኖ ወደነሱ የሚሮጥላቸው ተመሳሳያቸውን አያጡም ። በሰለጠነ አስተሳሰብና በአንድነት መንፈስ በአርአያነት ስናወድሳቸው የነበሩ አዛውንቶች እንኳ ከሰፊው የኢትዮጵያዊነት ውቂያኖስ ወጥተው በመንደር ኩሬ ለመንቦጫረቅ ሲሮጡ እያየን ነው ።
.
ዘረኝነት አገርንም ሆነ ዜጎችን የሚበላ የዘመናችን አውሬ ነው ። በዘረኝነት ውስጥ በፍፁም አዎንታዊ እሴት የለም ። ዘረኝነት ከጥፋት የሚያተርፈው ቡድን የለም ። እየወረደ ሄዶ ቤተሰብ ውስጥ ይገባል ። ይህን ክፉ መንፈስ ልንሰብረው ይገባል ። በተለይ በዚህ ካንሰር የተያዙት አመራሮችና አክቲቪስቶች በመተባቡር ልናቆማቸው ካልቻልን ….. አገር ቀርቶ ፣ ወገን ቀርቶ ፣ ቤተሰብ ቀርቶ እኛም እራሳችን የለንም ፤ አንኖርም ።