>

እንደ ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ቀልደኛ (ኮሚክ) በዓለም የለም! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

እንደ ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ቀልደኛ (ኮሚክ) በዓለም የለም!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ኩምክና ጥሩ ነው፡፡ ግን በአግባቡና በዓላማ ሲኮመክ ይበልጥ ጥሩ ነው፡፡ በሀገር ደረጃ መራር ቀልድ እየተወኑ በሕዝብና ባገር መቀለድ ግን ወደማይወጡት ችግር ይከታል፡፡ ስለዚህ ቀልድን ወይም ኮሜዲን ወይንም ኩምክናን ሥርዓትና ወግ ባለው ሁኔታ መተወን ለሁሉም ይበጃልና ዶክተር አቢይን የምትቀርቡ ሰዎች ጠ/ሚው ወደአይምሮው እንዲመለስና ዙሪያ ገባውን እንዲመለከት ብትመክሩት ደግ ነው፡፡ የዛሬ ቀልድ ለነገ መሪር ልቅሶ እንደሚዳርግ ካልተረዳ እንደአቃቂ ፈረስ ወደፊት እንጂ ወደጎንና ወደኋላ እንዳያይ ዓይነ ኅሊናው በሆነ ነገር ተሸብቧል ማለት ነውና ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ “ትዕቢትሰ ፀሩ ለክርስቶስ…” የምትለዋን ጥቅስም አስታውሱት፡፡

በነገራችን ላይ በኮሜዲው ዓለም አንድ በጣም “የምወደው” ገጸ ባሕርይ አለ፡፡ ጄኔራል አድሚራል አላዲን ይባላል፡፡ የምናባዊቷ ዋዲያ ሪፓብሊክ መሪ ነው፡፡ ያን የኮሜዲ ፊልም የደረሰ ሰው በጣም ተዋጥቶለታል፡፡ ያላያችሁት በወለላዋ ይሁንባችሁ እዩት፡፡ የሀገሬ መሪዎች እሱን እሱን እየመሰሉኝ ብዙውን ጊዜ እገረማለሁ፡፡ የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት በተለይ ከሩቅ ሲያዩት ያማልላል፤ እርሱን ለማግኘትም ብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ ይከታል፤ ያስዋሻል፤ ያቅጠፈጥፋል፤ ያጋድላል፤ ያገዳድላል፤ ከሃይማኖትና ሞራል ዕሤቶች – ከባህልና አስተዳደጋዊ ወግ ልማዶች ያስወጣል፤ የማያ’ረገው የለም ብሃፂሩ፡፡ ሲይዙት ደግሞ እጅግ ያባልጋል፡፡  እንኳን ለወዳጅ ለጠላትም የሚመኙት አይደለም፡፡ ባጠገቡ ሲያልፉ ደግሞ “ግማቱ” ሌላ ነው፡፡ ዕንቅልፍና የኅሊና ዕረፍት በዝናና በሀብት የሚለወጥበት ቦታ፡፡ 

ዶክተር አላዲን ማነው ዶክተር አቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የነበረው ትኅትናና የሀገርና የወገን ፍቅር በጥቂት ወራት ውስጥ እንደጪስ በንኖና እንደጤዛ ረግፎ በሀገርና በወገን በይፋ መቀለዱንና የጭቃ ጅራፉን እንደልቡ ማንጓት መጀመሩን ደሴ ላይ የተናገራት የኮሜዲ ቃል አብሣሪ ነበረች፡፡ በማሾፍ መልክ እንዲህ ብሎ የተናገራት – “ለአማራው ክልል የምንመድበውን በጀት እናንተ ሚሊሺያ በማሰልጠን ትጨርሱታላችሁ…” ከዚህ የበለጠ ቀልድ በየትኛውም ዘመንና በየትኛውም የዓለም ክፍል ተቀልዶ አያውቅም፤ ወደስተፊትም ይቀለዳል ተብሎ አይገመትም – አቢይ ራሱ የራሱን ሪከርድ ካላሻሻለ በስተቀር ማለቴ ነው፡፡ ለአማራ ክልል የሚመደበውን በጀትና ለትግራይና ኦሮሞ ክልሎች የሚመደበውን በጀት፣ ትግራይና ‹ኦሮምያ› በፊት በድብቅ አሁን ደግሞ በግልጽ የሚያሰለጥኑትን ወታደርና የሚያከማቹትን የጦር መሣሪያ፣ ወዘተ. ለሚያውቅ የሰውዬው መራር ቀልድ ይገባዋል፡፡ አምባገነኖች ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ዐይን ቦሙ ኢይሬእዩ፣ ዕዝን ቦሙ ኢይሰምዑ፣ አንፍ ቦሙ ኢይፄንዑ” ብሎ እንደጠቀሳቸው የጣዖት ስዕሎችና (መዝ. ዳዊት  115:4-8) ትንቢተ ሕዝቅኤልም በምዕራፍ 12 ቁጥር 2 ላይ  ስለልበ ደንዳና ሕዝቦች “የሰው ልጅ ሆይ፤ በዐመፀኛ ሕዝብ መካከል ተቀምጠሃል፤ የሚያዩበት ዐይን አላቸው፤ ነገር ግን አያዩም፤ የሚሰሙበትም ጆሮ አላቸው፤ ነገር ግን አይሰሙም፤ ዐመፀኛ ሕዝብ ናቸውና።” ሲል እንደተናገረው ሁለመናቸው ድፍን ነው፡፡ ልባም አንባቢ ለነሱም ያዝናል፡፡ እንዘንላቸው፡፡ በአንዳች የገደሉም ይሁን የባህሩ ጋንኤል ተለክፎ ካልሆነ በስተቀር ሰው ወድዶና ፈቅዶ እንደነአቢይ አይሆንምና፡፡ ለመገደል መቁረጥ እንዳለ እኮ ለመግደልም መወሰን አለ፡፡ ይህች የሦስት ቀን የስደት ምድራዊ ሕወት የማታሰየን ነገር የለም፡፡ ይህም ሁሉ ይገርመኛል ታዲያ፡፡ መንግሥቱ ኃ/ማርያምን እስኪ አሁኑ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አስቡት፡፡ አቢይ ከ30 ዓመታት በኋላ ምን ሊመስል እንደሚችል ደግሞ ገምቱ፡፡ የኬኒያው ዳኒ፣ የግብጹ ሙባረክ፣ የዚምባብዌው ሙጋቤ፣  በቀደምለት … ሰሞኑን …. ተከታትለው ሄዱ አይደል? “እንዲህ ልጠግብ በሬየን አረድኩ” አለች ያቺ ምስኪን ሴት፡፡ ታዲያ ለምኑ ነው ይሄ ሁሉ ተንኮልና ሤራ? ለምኑ ነው ይሄ ሁሉ ሸርና መጠላለፍ? ለምኑ ነው ይሄ ሁሉ ዘረኝነትና ጎጠኝነት? ለምን? ለምን? ጠይቁ፡፡ 

አማራ ክልል የሚባለው አካባቢ አንድም ሰው እንዳይወጣለት አቢይ የዓዞ ዕንባ እያነባ በአንጻራዊነት ጥሩ ጥሩ የሚባሉ አመራሮችን አንድም እርስ በርስ በማገዳደል፣ አንድም በሥውር የሤራ ጥልፍልፎሽ ገዳዮችን አስርጎ በማስገባት ነገር ግን እርስ በርስ እንደተገዳደሉ ትያትር ቢጤ ተውኖ በመጨፍጨፍ፣ አንድም የሚሰጋባቸውን አጠገቡ ጎልቶ በቅርብ በመቆጣጠር፣ አንድም ከዕውቀትና ትምህርታቸው ጋር ወደማይያያዝ ሥራ በመመደብ፣ አንድም ከሥራ በማፈናቀል …. የአማራን ክልል ባዶ ለማስቀረት ቀን ከሌት እየታተረ ነው፡፡ ይሳካለታል አይሳካለትም ወደስተፊት የምናየው ይሆናል፡፡ የነብሩን ጅራት ይዞ እየታገለ ለመሆኑ እጅግ በጣም ግልጽ ነው፡፡ ነብሩ ሲዞርበት ግና….(ያን ቀን አለማየት ነው፤ ቀኑም ቀርቧልና!)፡፡ የተኛ ሲነሳ ተራራም አይገታውም፡፡

“ቂጡ ላይ ቁስል ያለበት ውሻ እንደልቡ አይጮህም” እንዲሉ በፊት መለስ ሥር አሁን ደግሞ አቢይ ሥር ሉጥ ሉጥ የሚለው ብአዴንም ሆዱ ከሞላ ሌላው ደንታው አይደለምና አማራውን በማጥፋት ረገድ አቢይንና ላኪዎቹን እየተባበረ ይገኛል፡፡ ይህ ከእጅ አይሻል ዶማ ዓይነት የሆዳሞችና የከሃዲዎች ስብስብ አማራውን እያስጠቃ እስከመቼ እንደሚኖር አንድዬ ይወቀው፡፡ ለጥቅሙ ያደረ እንኳንስ ብሔሩን ልጅና ሚስቱንም ለጭዳ እንደሚያቀርብ የታወቀ ነውና ብአዴንን ተስፋ ማድረግ ለበለጠ መላላጥና ውድመት መጋለጥ መሆኑን ልባሞች ተገንዝባችሁ አፋጣኝ መፍትሔ ፈልጉ፡፡ ከብአዴን ውስጥም ደህና ሰዎች ካላችሁ ጊዜ ሳትፈጁ አንዳች ነገር አድርጉ፡፡

ከሰሞነኛ የአቢይ ቀልዶች ጥቂቱን ልበልና ነገሬን ልቋጭ፡፡ አቶ ዮሐንስ ቧ ያለውን የመለስን ፋውንዴሽን እንዲጠብቅ ማድረጉ አላዲን ለሩጫ ውድድር ተሠልፎ ሳለ ሊቀድሙት ሲሉ በሽጉጡ እየቀለጠመ ብቻውን ሮጦ ሪባኑን መበጠሱን የሚያስታውስ ነው፡፡ (በፈጠራችሁ ያን ፊልም ደግማችሁም ቢሆን እዩልኝ! አምባገነኖችን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡) አቢይ የዮሐንስን አቋም ያውቃል፡፡ መለስ በአማራው ላይ የሠራውን ግፍና በደልም ያውቃል፡፡ አማራን ለማጥፋት ቆርጦ በተነሣ ሰይጣን ስም የተገነባን ተቋም – ምን እንደሚሠራ እንኳን በውል የማይታወቅ ባዶ ግቢ  – እንዲጠብቅ ይህን ሣተና “መሾም” መራር ቢሆንም ቀልዱ ግን የቀልዶች ሁሉ ቁንጮ ነው፡፡ ነገ በነፃነታችን ዘመን አቢይ በሕይወት የሚተርፍ ከሆነ – ቢተርፍ በጣምምምም ደስ ይለኛል! – ማፈርን አያውቅም እንጂ እጅግ የሚያፍርበት ቆሻሻ ድርጊት ነው – ይሉኝታቢስነትና ውለታቢስነት የሞላበት አስጠሊታ ምደባ ነው፡፡ አማራንም በእግረ መንገድ ለማዋረድ የታሰበ ይመስላል፡፡ ለአቢይ ሥልጣን መያዝ አማራው በተለይም ብአዴን የከፈለው መስዋዕትነት እየታወቀ በብአዴን ላይ እንዲህ ጢባጢቤ መጫወት ባልተገባ ነበር – ብአዴን በተፈጥሮው በጥቅምና በፍርፋሪ ሥልጣን የታወረ ሆኖ በዚያም ላይ ብዙዎቹ አማራ ያልሆኑ ሠርጎ ገቦች በመሆናቸው ይህን ዓይነቱን ጥቃት ለመመከት የሚያስችል ቁመና ባይኖራቸውም “ፈጣሪስ ምን ይለኛል?” ተብሎ የግፍና የበደሉ ልጓም ያዝ መደረግ ነበረበት፡፡ ስለሆነም ይህ ቀልደኛ ጊዜው ሲደርስ በዚህች ቀልዱ ብቻ ለፍርድ መቅረቡ አይቀርም፡፡

ጄኔራሎቹንና የጦር መኮንኖችን እንዳለ ጠራርጎ ከሥራ በማስወጣት አንዳንዶቹንም ከሙያቸው ጋር በፍጹም ወደማይቀራረብ የሥራ ዘርፍ በመመደብ ያሳየን ቀልድም ሰውዬው ከእውነት ይልቅ ለፌዘኛ ተውኔት የቀረበ ለመሆኑ ዓይነተኛ ማስረጃ ነው፡፡ ዝም እንዳልል ይህን አልኩ – “አልኩ” ማለትም በጊዜው ዋጋ አለውና፡፡ በቃኝ፡፡ 

EMAIL: ma74085@gmail.com

Filed in: Amharic