>

ከአድዋ ድል በኃላ ስማቸው በወርቅ ቀለም ከተፃፈላቸው ጀግኖች መሃል ዋንኛው ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ!!! (ሀይሉ ስንታየሁ)

ከአድዋ ድል በኃላ ስማቸው በወርቅ ቀለም ከተፃፈላቸው ጀግኖች መሃል ዋንኛው ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ!!! 

ሀይሉ ስንታየሁ
እንደ ደጋ ገብስ እንዲያ ኮስሶ
ያስቆረጥማል ጠላቱን ኮሶ
የዳኘው ጀግና ባልቻ አባ ነፍሶ”
በአገምጃ ሶዶ(ወሊሶ) በሚባል ቦታ በነሀሴ ወር 1854 ዓ.ም ተወለዱ ባልቻ ሳፎ (አባ ነፎሶ) በእናታቸው ጉራጌ በአባታቸው ኦሮሞ ሲሆኑ ገና በልጅነት እድሜያቸው በጦር ሜዳ ተገኝተው ነበር፤ የምኒልክ ጦር አሸንፎ ለምኒልክ ስለ ምርኮኞች ና ስለሞቱት ሰዎች ሲነገሯቸው ..ከእነዚህ መሃል ብልቱ ተቆርጦ የተገኘበት ብላቴና መኖሩን ሲነገራቸው አፄ ምኒልክ እጅግ አዘኑ አፄ ምኒልክም ባልቻን ሊያሳድጉት በኃላፊነት ወደ አዲስ አበባ ይዘውት ሄዱ.።ባልቻ በቤተ መንግሥት ውስጥ በጦር ሙያ ተኮትኩቶ በጎልማሳነቱ የመድፍ ተኩስ ተምሮ ለአፄ ምኒልክ ከፈረንሳይ ሀገር የተሰጣቸው መድፎች የሚተኩስ የሚያስተኩስ ጎበዝ ጀግና ሆነ ባልቻ…
የዓድዋው ጦርነት ሥመ ጥር ጀግናው ባልቻ አባ ነፍሶ ፋሽስት ጣልያን ኢትዮጵያ በድጋሚ ስትወር ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋራ ፀብ ስለነበራቸው ባልቻ ከጣልያን ጎን ይሰለፋሉ ብለው ጣልያኖች አሰቡ። ደጃዝማች ባልቻ በንጉሱ ላይ ቅሪታ ቢኖራቸውም በአገር ጉዳይ ላይ ሌላ ድርድር መግባት አልፈለጉም ስለሆነም ጦራቸውን ማሰባሰብ ጀመሩ እናም ከነ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ፣ አበበ አረጋይ፣ በላይ ዘለቀና አቡነ ጴጥሮስ ጋራ ስለ ጦርነቱ የሚስጥር ደብዳቤ መለዋወጥ ጀመሩ። ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ አምስት ሺ ጦራቸውን ይዘው በ፸፱ ዓመታቸው ከትውልድ መንደራቸው ከአገምጃ ሶዶ ተነስተው አዲስ አበባ ደረሱ ከዛም ረጲ ተራራ ላይ ሆነው መድፋቸውን ጠምደው የሌሎችን አርበኞች መልዕክት ይጠባበቁ ጀመር።ሺ የባልቻ ሰላይ የነበሩት በባንዳ ተይዘው ሲገደሉ ጣሊያን በአውሮፕላን ሆኖ የደጃዝማች ባልቻ ጦርን እየተከተለ በጣም ብዙ ሰው ፈጀባቸው። በህይወት ዘመናቸው ጣልያንን ሁለት ጊዜ የተዋጉት ብዙ ወታደር የነበራቸው ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ብቻቸውን ቀሩ። ባልቻ ሁለት ወንድሞች ነበሯቸው ፊታውራሪ ገብረ መድህን እና ፊታውራሪ ሳህለሚካሄል ሁለቱም በጦርነት ተማርከውና ተገለዋል። በዚህም ጊዜ ደጃች ባልቻ እንዲህ አሉ
ጦር መጣ ይላሉ እኔ ምን ቸገረኝ 
እናቴም ልጅ የላት ለእኔም ወንድም የለኝ!
ደጃዝማች ባልቻ በልጅነታቸው ከጦርነት ላይ ተማርከው በአፄ ምኒልክ ቤት ያደጉ ታማኝ የጦር መኮንን የነበሩ…ከዓድዋ ጦርነት ፊት በጅሮንድ ተብለው የንብረት ኃላፊ ነበሩ። ኋላ በዓድዋ ጦርነት ላይ ፊታውራሪ ገበየሁ በጦርነት ላይ በጀግንነት ሲያልፉ መድፈኛነቱን ተክተው በመቀሌ እና በዓድዋ ጦርነት በጀግንነት ተዋግተዋል። በጦርነቱም ከጠላት በተተኮሰ ጥይት ጆሯቸው በመቆረጡ ባለቅኔው እንዲህ አሞገሳቸው
ማን እንዳተ አርጎታል የእርሳሱን ጉትቻ
የዳኘው አሽከር አባ ነፍሶ ባልቻ!
ከአድዋ ድል በኃላ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ በምኒልክ ዘመን የመድፈኛ ክፍል ኃላፊ የጦር መሳርያ ና የግምጃ ቤት ሀላፊ ሆነው የኢትዮጵያ ጦር መሳርያ በየአይነት ዓይነቱ ማስቀመጣቸው ይታወቃል። ደጃዝማች ባልቻ በእድሜ በዕውቀት ሲጎለብቱ ሲዳሞን እንዲያስተዳድሩ ተደርገ። ከዚያን በኃላ የሃረር ገዢ ሆነው ሐረርጌን እንዲያስተዳድሩ በልጅ እያሱ አማካኝነት ተሾመ። ራስ ተፈሪ ደግሞ ከሲዳማ ማዶ ያለው የጊሚራ መሬት እንዲያስተዳድር በልጅ እያሱ አማካኝነት ተሾመ። ልጅ እያሱ ይህንን ያደረጉት ከመጀመሪያ በተፈሪ ና በባልቻ መካከል ቅሬታ በመፈጠሩ ተራርቀው እንዲገዙ ነበር. ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ሐረርጌን ለአራት አመታት አስተዳድሩ. በዚህ መሀል ተፈሪ ደግሞ የአባቴን ሀገር ሐረርጌን ላስተዳድር የሚል ጥያቄ ለእቴጌ ጣይቱ አቀረቡ? ወደ ሲዳማ ሳይጓዙ አ.አበባ ተቀመጡ። ተፈሪ ንጉሠ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ተብለው ኢትዮጵያን እንዲያስተዳድሩ ሲሾሙ ከደጃዝማች ባልቻ ጋራ ቅሪታ ተፈጠረ በኃላም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደጃዝማች ባልቻን አባ ነፍሶን ከአገር አስተዳዳሪነት ሹመት አነሷቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለባልቻ አባነፍሶና ለበላይ ዘለቀ ከፍተኛ ጥላቻ እንደነበራቸው ብሎም ከእርሳቸው ውጭ የሌላ ኢትዮጵያዊ ስም ሲጎላ ይናደዱ እንደነበር ስለሀይለስላሴ የተፃፉ መጽሐፍት ያስረዳሉ። ከንጉሥ ጋራ ወደ ሌላ ፀብ መግባት ያልፈለጉት ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ከዘመዶቻቸው ሀገር ከእነ ሙሉ ክብራቸው ተቀምጠው የተጣላውን እያስታረቁ እስከ ሁለተኛ የጣልያን ወረራ ዘለቁ።
ጦር መጣ ይላሉ እኔ ምን ቸገረኝ
እናቴም ልጅ የላት ለእኔም ወንድም የለኝ!
የጠላት ጦር ደጃዝማች ባልቻ ወደሚኖርበት እስከ ጉራጌ አገር ድረስ በመዝለቅ በእሳቸው ላይ ዘመተባቸው ህዝቡም ከዳቸው ወታደሮቹም ለህይወታቸው ሲሉ ሸሿቸው ደጃዝማች ባልቻ ሁለቱ አሽከሮቻቸው ከእሳቸው ጋራ 3 ሰው ብቻ ቀረ ብዛት ያለው የጣልያን ጦር ከበባቸው ወዴትም መሄድ አልቻሉም ። በመጨረሻም እጅህን ስጥ መሳሪያክን ጣል ብሎ ጣልያኑ ሲያዛቸው ደጃዝማች ባልቻ እኔ እጄን የምሰጥ ሰው አይደለሁም ..ትጥቄን አልሰጥም ብለው ነጩን ጣልያን ገድለው በራሳቸው ጥይት የራሳቸውን ህይወት አጠፉ። እጃቸውን እንካን ለጠላት ሳይሰጡ በራሳቸው ሽጉጥ ጥቅምት 27 1929 ዓ.ም ተሰው። ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ በአካል ጉድለት ምክንያት ልጅ ወልደው ዘራቸውን ባይተኩም የጀግና ውለታ የማይረሳ የኢትዮጵያ ህዝብ ልጃቸው ሆኖ ታሪካቸውን ሰዘክር ሊኖር ይገባል። ክብር ለሀገር ለሞቱት ጀግኖች አባቶቻችን።
Filed in: Amharic