>

የደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ 8ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ !!! (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

የደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ 8ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ !!!

ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ያረፉት ከዛሬ ስምንት ዓመታት በፊት (የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም) ነበር፡፡
ጥቅምት 12 ቀን 1923 ዓ.ም. በዋግ አውራጃ ዐምደ ወርቅ ከተማ ከአባታቸው ከአቶ ውድነህ ተፈሪና ከእናታቸው ወይዘሮ አበበች ወልደየስ የተወለዱት ማሞ ውድነህ፣ ወደ ስነ ጽሁፉ ዓለም በመዝለቅ (በተለይ በስለላ ሥራ ላይ ያተኮሩ) 53 መጻህፍትን ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ወደአማርኛ በመተርጎም ለአንባቢያን አድርሰዋል።
በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ገና በልጅነታቸው ወላጆቻቸውን ያጡት ማሞ፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በ15 ዓመት እድሜያቸው እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በ1948 ዓ.ም. ልብወለድ ጽሁፎች መጻፍ የጀመሩት ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፣ የመጀመርያ ጽሑፋቸው ባለ 160 ገጽ የሆነውና በትያትር መልክ የተተወነው ‹‹የሴትዋ ፈተና – አለፈ በደህና›› የሚል ነበር፡፡ በ1960 ዓ.ም.  ‹‹ብዕር እንደዋዛ›› በሚል ርእስ ባሳተሙት የግጥም መጽሐፋቸው ታሪክንና መንፈሳዊነትን ለወጣቶች አስተምረውበታል፡፡
ደራሲ ማሞ ውድነህ ቀደምት ከሆኑት ጋዜጠኞች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ‹‹ፖሊስና እርምጃው›› የተባለው ጋዜጣ መሥራችና ዋና አዘጋጅም ነበሩ። ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ለረጅም ዓመታት ሰርተዋል።
ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፣ ወደ ሥነ ጽሑፉ ዓለም በጥልቀት እንዲገቡ ምክንያት የሆናቸውን አጋጣሚ የተፈጠረው በ1952 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱም እርሳቸው ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› ጋዜጣ ላይ ‹‹የት ትገኛለች?›› በሚል ርዕስ ለጻፉት መጣጥፍ ዕውቁ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹እሱስ የት ይገኛል?›› በማለት የሰጠው የሚል ምላሽ ለረጅም ጊዜ አከራክሯቸዋል፡፡
የጽሑፍ እሰጥ አገባው በወንዶችና ሴቶች መካከል ያለውን የወግ ልዩነት አስመልክቶ የተደረገ ሙግት ነበር፡፡ በወቅቱ በስፋት ተነባቢ በነበረው በዚሁ ጋዜጣ የቀጠለው ክርክር እስከ መንግሥት ባለሥልጣናት ድረስ አነጋጋሪ ለመሆን እንደበቃ ይነገራል፡፡
ክርክሩ የበርካቶችን ቀልብ በመሳቡ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ መኰንን ሀብተ ወልድ ‹‹ጉዳዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ነው›› በማለት መጠናት አለበት ብለው አምባሳደር ዘውዴ ረታ ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞና ኮሚቴው ሁለቱንም ተከራካሪዎች ጠርቶ ባነጋገራቸው ወቅት ‹‹ፊት ለፊት ቢገናኙ ይገዳደላሉ›› ተብሎ በሕዝቡ ይናፈስ በነበረው ወሬ ምክንያት ፖሊስ በመካከላቸው ቢገኝም ባለጉዳዮቹ ማሞ ውድነህና ጳውሎስ ኞኞ ተሳስቀው መሳሳማቸው የኮሚቴውን አባላት ያስደነቀ አጋጣሚ እንደነበር ደራሲ ማሞ በህይወት በነበሩበት ጊዜ ተናግረዋል።
ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ በ‹‹የካቲት›› መጽሔት ላይ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ‹‹የአገራችንን የባህል ልብስ ለብሰው ቢታዩስ?›› በሚል ርዕስ ያቀረቡት አስተያየት የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ የነበሩት አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ ማዕረጉ በዛብህ 150 ብር እንዲቀጡ ምክንያት ሆኗል፡፡
ከባለቤታቸው ከወ/ሮ አልማዝ ገብሩ ጋር ከ50 አመት በላይ በትዳር ያሳለፉት ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ አሁን ላለው ትውልድ ትልቅ ተምሳሌት ስለመሆናቸው በሚያውቋቸው ሰዎች የሚመሰከርላቸው ሰው ናቸው።
‹‹በትዳር ለረዥም ጊዜ ለመኖርዎ ምስጢሩ ምንድነው?›› ተብለው ተጠይቀው ሲመልሱም፣ ‹‹መተማመንና መቻቻል›› በሚል በአጭሩ የገለጹት ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፣ ልጆቻቸው አንድም ቀን ጭቅጭቅ ሰምተው እንደማያውቁ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ ‹‹ችግር ሲኖር ቤት ቆልፈን እንነጋርበታለን›› በማለት ልጆቻቸው ክፉ ቃል ሳይሰሙ ማደጋቸውን ይናገራሉ፡፡
– – –
ስድስት ልጆችና 10 የልጅ ልጆችን ለማየት የበቁት ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ‹‹ሀብታችን ልጆቻችን ናቸው›› በማለት በኩራት የመናገር ልምድ ነበራቸው፡፡ በመጨረሻም ባደረባቸዉ ሕመም ምክንያት የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም በ81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
በስለላና በወንጀል ምርመራ ላይ በሚያጠነጥኑ በርካታ የትርጉም ሥራዎቻቸውና ድርሰቶቻቸው የሚታወቁት ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ ሥራዎቻቸው ሕዝባዊነትንና ባሕል አክባሪነትን የተላበሱ በመሆናቸው ዘመን ተሻጋሪ ያደርጋቸዋል፡፡
ከደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ስራዎች መካከል ጥቂቶቹ …
1. ሁለተኛው የዓለም ጦርነት
2. የሴቷ ፈተና
3. ከወንጀለኞቹ አንዱ
4. ቤኒቶ ሙሶሊኒ
5. የገባር ልጅ
6. ሁለቱ ጦርነቶች
7. አደገኛው ሰላይ
8. ዲግሪ ያሳበደው
9. ካርቱም ሔዶ ቀረ?
10. የ፮ቱ ቀን ጦርነት
11. የደቡብ ሱዳን ብጥብጥ
12. ብዕር እንደዋዛ
13. ሞንትጐመሪ
14. የኤርትራ ታሪክ
15. የኛ ሰው በደማስቆ
16. የ፪ ዓለም ሰላይ
17. ምጽአተ-እሥራኤል
18. ሰላዩ ሬሳ
19. የ፲፯ቱ ቀን ጦርነት
20. የካይሮው ጆሮ ጠቢ
21. የበረሃው ተኩላ
22. ዘጠና ደቂቃ በኢንተቤ
23. ጊለን-የክፍለ ዘመኑ ሰላይ
24. የኦዴሳ ማኅደር
25. ከርታታዎቹ
26. ከሕይወት በኋላ ሕይወት
27. ስለላና ሰላዮች
28. ምርጥ ምርጥ ሰላዮች
29. ዕቁብተኞቹ
30. አሉላ አባነጋ
31. የሰላዩ ካሜራ
32. ሰላይ ነኝ
33. በዘመናችን ከታወቁ ሰዎች
34. ዕድርተኞቹ
35. ሾተላዩ ሰላይ
36. ማኅበርተኞቹ
37. በረመዳን ዋዜማ
38. የበረሃው ማዕበል
39. ኬ.ጂ.ቢ.
40. ሲ.አይ.ኤና ጥልፍልፍ ስራዎቹ
41. ዩፎስ-በራሪ ዲስኮች
42. መጭው ጊዜ
43. ዮሐንስ
44. የአሮጊት አውታታ
45. እኔና እኔ
46. ኤርትራና ኤርትራውያን
47. ሞት የመጨረሻ ነውን?
48. የደረስኩበት ፩
49. የደረስኩበት ፪
Filed in: Amharic