>

ትእምርታተ ማዕሌት :- የአምባገነንነት ምልክቶች በ‹በለጸገው› ኢሕአዴግ! (ከይኄይስ እውነቱ)

ትእምርታተ ማዕሌት:

የአምባገነንነት ምልክቶች በ‹በለጸገው› ኢሕአዴግ!

 

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

በሕወሓት ፍጹም የበላይነት ሲመራ የነበረው ቀዳማዊው ኢሕአዴግም ሆነ አሁን በ‹ብልጽግና› ሽፋን አድራጊ ፈጣሪ በሆነው ኦነጋዊው ኦሕዴድ የበላይነት የሚመራው ካልአይ ኢሕአዴግ አገዛዞች በመሆናቸው የአምባገነንነት ጠባይ ሥሪታቸው ነው፡፡ ከተፈጥሮአቸው ውጪ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ድከሙ ሲለን ከኵርንችት የበለስ ፍሬ እየጠበቅን እንጂ፡፡ የአገዛዙ ቁንጮ ራሱ ‹ብልጽግና› የኦሮሞ ነው ብሏል፡፡ (ባለቤቱም ሆነ አፎቹ ትርጕሙን አላስተባበሉም፡፡) እውነቱን ነው፤ ለማና ዘመዶቹ ጊዜው የእኛ ነው ያሉትን ማኅተም አሳረፈበት፡፡ ቀሪዎቹ 7ቱ በለመዱት አሽከርነት ቀጥለዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ከባለቤቱ ያወቀ ሆነው ‹ከሰውዬው› ታማኞች ወይም ቅርቦቹን ከሚያውቅ ሰው ሰምተናል የእሱ ሃሳብ የተለየ ነው በሚል ጉም ዘግነው ሌሎቻችሁም ካልዘገናችሁ ይሉናል፡፡ በምድር ላይ አፍጦ አግጦ የሚታየውን ጽድቅ ሸሽተው የማይመረመረው የሰው ኅሊናና አእምሮ ውስጥ ገብተው እንዲሆን የሚመኙትን ሌሎችም በጭፍን እንዲያምኑና እንዲቀበሉ ይደክማሉ፡፡ ልብ ያመላለሰውን ኩላሊት ያጤሰውን የሚያውቅ የሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስታችሁ ሌላውን ከማሳት ለጊዜው ከሱ የተሻለ የለም እስከነ ‹ጉዱ› ተሸክመን እንደግፈው ማለት መብታቸሁ ነው፡፡ እውን ኢትዮጵያ የወላድ መካን ነች? እንደ ዘመነ ሰዶም አንድም ሰው የላትም? እንደ ነቢዩ ኤልያስ ‹ያላዋቂ› ንግግር አይሆንብምን? በዘመኑ ጣዖት አምላኪ ነገሥታት ሠልጥነው ሕዝቡን ከአምልኮተ እግዚአብሔር ዞር ሲያደርጉ የተመለከተው ነቢዩ ኤልያስ ነቢያት አልቀው ብቻዬን ቀርቼአለሁ ሲል ለአምላኩ በምሬት አቤት አለ፡፡ እግዚአብሔርም አንተ የማታውቃቸው 7ሺህ ሠራዊት አሉኝ ብሎ ኩም አደረገው፡፡ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ምድር ሰው እንዳለው አንጠራጠር፡፡ ለሀገር አንድነትና ለሕዝብ ደኅንነት መሥጋት ተገቢ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ላይ ለረጅም ዓመታት ሠልጥኖ የቈየው እኔ ካልኩት ውጭ አማራጭ የለም፣ ቀሪው የጥፋት መንገድ ነው የሚል የገዢዎች የድንቁርና አስተሳሰብ ወደ ሕዝብም ተጋብቶ ከእገሌ ውጭ አለቀልን ማለት የአሳብ ምክነትና ሀገራዊ ሕማም ነው፡፡ 

ዐቢይ የአገዛዝ መሪ ነው፡፡ ያውም በጎሠኛነት የታወረውና መንግሥተ ሕዝብ በኢትዮጵያ እንዳይቆም ሾተላይ የሆነባት የኢሕአዴግ አለቃ፡፡ የአገዛዝ መሪ ደግሞ መምዕላይ (dictator) ነው፡፡ በጉልበት ሥልጣን ይዞ በጉልበት የሚገዛ፡፡ ግፋ ቢል ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንዳሉት ‹በጎ መምዕላይ› ሊሆን ይችላል፡፡ በተምታታ ንግግሩና ለሕዝብ የሚጠቅሙ በሚመስሉ አንዳንድ ተግባሮቹ ብዥታ መፍጠሩና የሕዝብን ስሜት ከወዲህ ወዲያ በማላጋቱ፡፡ አገዛዙ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እውነተኛ ገጽታውን በገሃድ እያሳየ ቢሆንም ማንአለብኝነቱ እንደ ድንገተኛ ደራሽ የተከሰተ አይደለም፡፡ እስቲ ከአንድ ዓመት ከ6ወራት ወዲህ በዐቢይ አገዛዝ የታዩትንና እየጎሉ የመጡትን የአምባገነንነት ምልክቶች ፣ የሱንም መምዕላይነት የሚያሳዩ ምልክቶችን ለአብነት እናንሳ፤

 • አገዛዙ ሕግና ሥርዓት ማስከበር አቅቶት በአገራችን አብዛኛዎቹ ክፍላተ ሀገራት ሥርዓተ አልበኝነት መንግሡ፤የሕዝብ የተረጋጋ ሕይወትና ሰላም መደፍረሱ፤ በተቃራኒው ሥልጣንን ለማስጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ኃይልን የመጠቀሙ አዝማሚያ መስተዋሉ፤ 
 • ከቡራዩው ጭፍጨፋ እስከ ልጃገረዶቹ (ተማሪዎቹ) እገታ (የጀዋር ቄሮዎች ባንድ ጀንበር በ86 ዜጎች ላይ የፈጸሙት አሰቃቂ ዕልቂት ሳይዘነጋ) ከዐቢይ ጀምሮ በተዋረድ ያሉ ባለሥልጣናት ፍጹም ተጠያቂነት አለመኖር፣ አልፎ ተርፎም ለሕዝብ የሚያሳዩት ንቀትና ማንአለብኝነት፤
 • ወያኔ ትግሬ ባህል ያደረገውን ገዢ ‹ፓርቲ› እና ‹መንግሥት› አንድ አካል አንድ አምሳል ሆኖ በመሥራት የሕዝብን ሀብት አገራዊ ላልሆነ የፖለቲካ ቡድን ዓላማና ፍላጎት በማዋል የሚታይ ሥር የሰደደ ንቅዘትና በሥልጣን መባለግ፤
 • በአገዛዙ ድጋፍና ዕውቅና በተረኝነት መንፈስ በሚንቀሳቀሱ ጐሠኛ ባለሥልጣናት፣ ግለሰብ ነጋዴዎች፣ አድርባዮችና ዘረኛ የፖለቲካ ቡድኖች ብሔራዊ ምልክት የሆኑ ተቋማትን (ለአብነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ) በተጠና መልኩ የማፍረስ ተግባራት፤
 • አገዛዙ ባሳየው ከፍተኛ ቸልተኝነት ጊዜው የኛ ነው በሚሉ የኦሮሞ ጎሠኛ ፖለቲከኞችና ቀስቃሾች ባሰማሯቸው የመንደር ወሮበሎች በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ፣ ካህናትና ምእመናን ሲታረዱና ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ ከዐቢይ ጀምሮ ክስተቱን ያስተናገዱበት መንገድ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በደል የደረሰበት ሕዝብ ብሶቱን በሰላማዊ ሰልፍ እንዳይገልጽ (በተለይም በአ.አ.) የተደረገው መዋቅራዊ አፈና የአገዛዙ ግልጽ መድልዎ ማሳያ መሆኑ፤
 • የአገዛዝ ሥርዓት ዋነኛ መለያ የሕግ የበላይነት አለመኖር ነው፡፡ በዚህም አገዛዙ የፍትሕ ሥርዓቱን ለራሱ መጠቀሚያ በማድረግ በየተቋማቱ በግዙፍ ወንጀሎች የሚፈለጉ ደናቁርት ጎሠኞቸን (ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የፖሊስ ሹም፣ የወህኒ ቤት ሹም፣  ወዘተ) አስቀምጦ፣ በዳኝነቱም በመርህ ሰውነት ሳይሆን በፆታ ኮታ አድርባይ መድቦ፣ እንዲሁም ሰው የጠፋ ይመስል ነውረኞቹን ግርማ ብሩንና አባዱላን (የአባይ ፀሐዬና የስዩም መሥፍን አቻዎችን) በዋና የኢኮኖሚ አማካሪነትና ደቡብ ተብሎ በተሰየመው ክ/ሀገር የሞግዚት አስተዳዳሪነት ሰይሞ ሲያበቃ፤ አገዛዙን የሚተቹና በሃሳብ የሚገዳደሩ ዜጎችን በዘፈቀደ የማሠርና የማንገላታት፣ የሕዝብ ጩኸት ሲበረክት ደግሞ ‹በምህረት/በይቅርታ› ሽፋን በአገር ጉዳይ ከፍተኛ ወንጀሎችንና ዝርፊያዎችን የፈጸሙ ጋር አደባልቆ የመልቀቅ አስነዋሪ ድርጊት፤
 • የአገሪቱ ከፍተኛ አስፈጻሚ አካል (ሚኒስትሮች ም/ቤት) ‹ሕግ አውጪ› ሆኖ መቀጠሉ፤  
 • በአመዛኙ ክፍላተ ሀገራት በአስተዳዳሪነት የተሰየሙት የጎሣ አለቆች በማዕከላዊው መንግሥት የተሰየሙ ሞግዚት ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ሕገ ወጥ የመንደር ወሮበሎችን በማደራጀትና መዋቅራዊ ድጋፍ በመስጠት የሕዝብን የዕለት ተዕለት ኑሮ ሲያውኩ ያለአንዳች ተጠያቂነት መታለፋቸውና አሁንም ድርጊቱ መቀጠሉ፤ 
 • በግብር ከፋዩ ሕዝብ የሚተዳደሩት የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤቶች (ቢሮክራሲ)  ከማዕከል እስከ ክፍለ ሀገር ተረኛ ነን ለሚሉ ኃይሎችና ቡድኖች መሣሪያ መሆናቸው፤
 • መንግሥታዊ መዋቅሮች በሙሉ (ከማዕከል እስከ ክ/ሀገር) ብልጽግና ነኝ ለሚለው ኢሕአዴግ የምርጫ መቀስቀሻ መሣሪያ መሆናቸው፤ ዐቢይ ያለ ሥርዓት ሳይሰየም የሚመራው አዲሱ ኢሕአዴግ ከሌሎች ለምርጫ ከሚወዳደሩ ‹የፖለቲካ ማኅበራት› ጋር ያለውን ግንኙነት ልክ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ሥልጣን ይመለከተዋል፡፡ በጠ/ሚኒስትርነቱ ከሚመራው ካቢኔ /ከሚኒስትሮቹ ያለው ግንኙነት እንዳደጉ አገሮች ጠ/ሚኒስትሮች ከአቻዎች ቀዳሚ (first among equals) ሳይሆን የአዛዥና ታዛዥነት እንደሆነ ሁሉ፣ በምርጫም ረገድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጋር ራሱን በእኩልነት እንደማያይ በተደጋጋሚ (የአንዳንድ ተቃዋሚ ‹ፓርቲ› መሪዎች በይፋ እንደተናገሩትና በተግባርም እንደታየው) ተስተውሏል፡፡ ለዚህም ዋና መገለጫው ከፍ ብለን የገለጽነው በጉልበት የያዘውን የመንግሥት ሥልጣን፣ መዋቅርና ሀብት እመራዋለሁ ለሚለው ፓርቲ ያለ ይሉኝታ በመጠቀም ምርጫውን አላስፈላጊ እያደረገው ነው፤በዚህም ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ እንደማይሆን ከበቂ በላይ ምልክት መታየቱ፣ ምርጫውን አስመልክቶ የገባው ቃል እንደ ሌሎች ቃልኪዳኖቹ ባዶ የቃላት ኳኳታ መሆኑን በተግባር አስመስከሯል፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የምርጫ ቦርድ አቅመ ቢስነት እና ችግር ሲከሰት በተአማኒነት ሊያርም የሚችል የዳኝነት ሥርዓት አለመኖሩ፤
 • እንደ ኦነግ ካሉ ከነትጥቃቸው ወደ አገር ውስጥ የገቡ አሸባሪ ድርጅቶች ጋር ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በምን መልኩ እንደሚንቀሳቀሱ የስምምነት ማዕቀፍ አለመኖሩ፤ አንዱ ክፍል ጫካ ገብቶ የሕዝብን ሰላማዊ ሕይወት  በሽብር ሲንጥ፣ ሌላው ደግሞ ከተማ ተቀምጦ ከአገዛዙ ተረኞች ጋር በመተባበር ሁሉ ለእኔ ይገባኛል በማለት አገር ሲያምስ ሀይ ባይ መጥፋቱ፤ በርካታ ባንኮችን ዘርፈው (የሕዝብ ገንዘብ ሳይመለስ እና አጥፊዎቸም ለፍርድ ሳይቀርቡ) እንደተራ ድርጊት በአባ ገዳዎች ዕርቅ ተፈጽሟል በሚል መሸፋፈኑ፤ 
 • ከኤርትራ አገዛዝ ጋር ያለው ግንኙነት ሕግና ሥርዓትን ያልያዘና መርህ አልባ መሆን፣ ለሕዝብም ይፋ የማይደረግና በዘፈቀደ የሚመራ መሆኑ የፈጠረው ሥጋት፤በተመሳሳይ መልኩ ከዐረብ አገራት ጋር ያለን የውጭ ግንኙነት እንዲሁ ሽፍንፍን መሆኑ እና ለወደፊቱ የሚያስከትለውን ውጤት በውል አለማወቅ፤

እነዚህ ከፍ ብለን የጠቀስናቸው እውነታዎች ከሞላ ጎደል የአገዛዙንና የጠ/ሚሩን አምባገነንነት ማሳያ ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ታዲያ ከስድስት ወራት ባነሰ ጊዜ ይካሄዳል ተብሎ ከሚታሰበው ምርጫ ምን እንጠብቅ? አገራችን ተመሳሳይ ግብ ያላቸው በሚመስል ሁለት አጥፊ ኃይላት ተሠቅዛ ተይዛለች፡፡ ማዕከሉን እየመራ ባለው ኦሕዴድ መራሽ ኢሕአዴግ (ብልጽግና) እና ክፍላተ ሀገራቱን (አ.አ. እና ድሬደዋን ጨምሮ) እንደ ቅርጫ ለመናጠቅ ባሰፈሰፉት ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶችና ቀስቃሽ ነን የሚሉ ግለሰቦች፡፡ 

የብልጽግናው ኢሕአዴግ አለባህርይው የጐሣ ፖለቲካን እስከ ‹ክልል› መዋቅሩ፣ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱን› እስከ አፋኝ ሕጎቹ ቀይሮ ለመንግሥተ ሕዝብ መደላድል የሚሆን የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ፤ ባንፃሩም ኢኮኖሚውን ሥር ከሰደደ ንቅዘትና ዝርፊያ እንዲሁም ከዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ጥገኝነት አላቆ ማኅበራዊ ፍትሕ ለማምጣት የሚያስችል ርምጃ ይወስዳል ብሎ ማሰብ ነፋስን መጐሰም ይመስለኛል፡፡ እስከመቼ ይሆን አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አምርሮ በሚጠላው ድርጅት እየተገዛ የአገሩን ጥፋት የሚጠባበቀው?

Filed in: Amharic