>

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም በመግደል የተጠረጠረው ተከሳሽ የእምነት ክህደት ቃል ሰጠ!!! (ታምሩ ጽጌ)

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም በመግደል የተጠረጠረው ተከሳሽ የእምነት ክህደት ቃል ሰጠ!!!

ታምሩ ጽጌ
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምንና ጓደኛቸውን በመግደል ተጠርጥሮ ክስ የተመሠረተበት የመከላከያ ሠራዊት አባል፣ የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጠ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን የወንጀል ክስ እየመረመረው በሚገኘው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በሽብርና የሕገ መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጠሩ ወንጀሎች አንደኛ ወንጀል ችሎት የእምነት ክህደት ቃሉን የሰጠው ተጠርጣሪ ተከሳሽ አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ነው፡፡
በጄኔራል ሰዓረ መኮንንና በሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ ግድያ ተጠርጥሮ በእስር ላይ የሚገኘው አሥር አለቃ መሳፍንት፣ ድርጊቱን አለመፈጸሙንና ወንጀለኛም እንዳልሆነ የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ቃሉን ሰጥቷል፡፡ ተከሳሹ የተመሠረተበትን ክስ በመካዱ፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ያካተታቸውን 35 ምስክሮች አቅርቦ እንደ ክሱ ለማስመስከር እንዲችል ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ 35 ምስክሮችን ቆጥሮ የነበረው ከአሥር አለቃ መሳፍንት ጋር ክስ ተመሥርቶባቸው ከነበሩት የአብን አመራር አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ 12 ተጠርጣሪ ተከሳሾች ላይ የነበረ ቢሆንም፣ እነሱ ባለፈው ሳምንት ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር በመፈታታቸው ምን ያህል ምስክሮች በአሥር አለቃ መሳፍንት ላይ እንደሚያሰማ አልታወቀም፡፡
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን ምስክሮችን ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዕለቱ ቀደም ብሎ በተከሳሹ ላይ ቀርቦ የነበረው ክስ እንዲሻሻል በተሰጠው ትዕዛዝ ክሱ ተሻሽሎ በመቅረቡ ተነቦለታል፡፡ የተከሳሹ ጠበቆች አብረውት የነበሩ ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጡን በመጠቆም ክሱ ተለይቶ እንዲቀርብ ቢጠይቁም፣ ፍርድ ቤቱ አልተቀበላቸውም፡፡ በክሱ ላይ የሚሰሙት ምስክሮች እሱን በሚመለከት ክስ ላይ ብቻ በመሆኑ ክሱን መለየት አስፈላጊ አለመሆኑም ተገልጿል፡፡
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ላይ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ መገደላቸው፣ እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አቶ ምግባሩ ከበደና አቶ እዘዝ ዋሴ በተቀራራቢ ሰዓታት መገደላቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር
Filed in: Amharic