>
5:18 pm - Monday June 16, 7056

በቂ የውኃ አቅርቦት በሌለበት ንጽሕናችሁን ጠብቁ ማለት ምንድን ነው? (ከይኄይስ እውነቱ)

በቂ የውኃ አቅርቦት በሌለበት  ንጽሕናችሁን ጠብቁ ማለት ምንድን ነው?

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

በዓለማችን የተከሠተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሀገረ ኢትዮጵያም የመግባቱን መርዶ ሰማን፡፡ ባለሥልጣናቱ አትረበሹ አትደናገጡ ይሉናል፡፡ ዋናው ነገር የጥንቃቄ ርምጃዎች የተባሉትን ተግባራዊ ማድረግ ነው፤ ከጥንቃቄዎቹም መካከል አንዱና ዋነኛው ንጽሕናን መጠበቅ በተለይም የእጅን ንጽሕና ብለውናል፡፡ መልካም፡፡ በየክፍላተ ሀገራቱ ያሉ ከተሞችን የውኃ አቅርቦት ምንድረስ እንደሆነ በውል ባለውቅም እኔ ተወልጄ ባደግሁባት አዲስ አበባ ያለማጋነን ካለፉት ዐሥር ዓመታት ወዲህ ነዋሪዎች ከሚያሰሙት እሮሮ በመንግሥት ከሚሰጡት የሕዝብ አገልግሎቶች አንዱ የሆነው የንጹሕ ውኃ አቅርቦት ነው፡፡ የውኃ እጦቱ እንደየአካባቢው ከሳምንታት እስከ ወራት የሚዘልቅበት ልዩ ሁናቴ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባጠቃላይ በ3ት ቀናት አንድ ጊዜ የሚለቀቅበት አሠራር ነው ያለው፡፡ ይሄም አስተማማኝ አይደለም፡፡ ዛሬ የቧንቧ ውኃ ለመጠጥ አገልግሎት የሚውል አይደለም፡፡ ነገር ግን ዐቅም የሌለው አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል አማራጭ ስለሌለው ቢታመምም እየጠጣው ነው፡፡ ‹ውኃ አጋር› መጠቀሙ የራሱ የጎን ጠንቅ ሲኖረው፣ ውኃ ማጥሪያ/ማከሚያ እንክብሉ (Acquatabs water purification tablets ) የአቅርቦት ውሱንነት/አለመኖር ብቻ ሳይሆን ዋጋውም ለአብዛኛው ሕዝብ የማይቀመስ ሆኗል፡፡  

የውኃና ፍሳሽ አገልግሎቱን የሚያቀርበው የባለሥልጣን መ/ቤት ካለበት የአስተዳደር፣ የሠራተኞች ብቃትና ንዝህላልነት ችግሮች የተነሳ እከተለዋለሁ ለሚለውም መርሐግብር ተገዢ አለመሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቶናል፡፡ ከታዘብኩት ምክንያት አንዱ የመ/ቤቱ ሠራተኞች ነባር የብረት መስመሮችን በጎማ ሲቀይሩ በአብዛኛው ቦታዎች ነባሩን ከዋናው መስመር በሚገባ ሳይዘጉት ወይም ጨርሶውኑ ሳይዘጉት በየቦታው ውኃ እየባከነ ነው፡፡ ራሳቸው የፈጠሩትን ችግር ለማስተካከል በየመንደሩ ያልተቈፈረ አካባቢ አናገኝም፡፡ ለዚህ ሥራ ተብሎ ውኃ ይቋረጣል፡፡ በዚህም ምክንያት መ/ቤቱ ፈረቃ ባለው ሥርዓትም መስተናገድ የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ባጠቃላይ÷ የአ.አ. ሕዝብ በተለይ ቊጥሩ በእጅጉ የጨመረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሕዝብ ቈጠራ ባይደረግም እንኳ ካነበርንበት በመነሳት ትንበያ (projection) ይሠራል፡፡ በዚህም ምክንያት የውኃ አቅርቦት እጥረት ሊኖር እንደሚችል ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ ኃላፊነት ተሰምቶት የሚሠራና ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ‹ቸር› የሆነ አምባገነን አገዛዝ ቢኖረን የሕዝብን ቊጥር መጨመር፣ የከተሞችን መስፋፋትና የነዋሪዎቻቸው ቊጥር መጨመርን ተከትሎ ቀደም ብሎ ጥናት በማድረግ በመሪም ሆና በየደረጃው ባሉ ዕቅዶች ውስጥ አካትቶ ችግሩን ማቃለል፣ ቢያንስ አሁን በሚታይበት ደረጃ የከፋ እንዳይሆን ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ እስካሁን በዘለቀው ወያኔ/ኢሕአዴግ እና በወራሹ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ አገዛዞች የሕዝብ አገልግሎቶችን (ኤሌክትሪክ እና ውኃ) ለፖለቲካ አሻጥር የመጠቀም ነውረኛነትም ተስተውሏል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ያላት የገፀ-ምድርም ሆነ የከርሰ-ምድር ውኃ ሀብት ይታወቃል፡፡ በከተሞችም እንዲሁ፡፡ ለሕዝብ አስቦ በዘለቄታው የሚሠራ አካል ካለ እና ጅምር ፕሮጀክቶችም ካሉ እንደተጠበቁ ሆነው፣ አገዛዞች ዘመቻና ግርግር ስለሚወዱ ቢያንስ አሁን የተከሠተው ወረርሽኝ አንድ መፍትሄ እስኪገኝለት ድረስ የውኃ አቅርቦቱ በተቻለ መጠን በየዕለቱ የሚኖርበትን፣ ጎን ለጎን ደግሞ በየቀበሌው/ወረዳው ጥናትን መሠረት አድርጎ አንድ አንድ የጉድጓድ ውኃ ተቈፍሮ ለማኅበረሰቡ የጋራ አገልግሎት የሚሰጥበት መንገድ መቀየስ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ እኔ የቧንቧ ውኃን መሸጥ ነውር በሆነበት ቤተሰብና ማኅበረሰብ ውስጥ አድጌ ዛሬ አንዳንድ ስግብግቦች አንድ ባልዲ ውኃ ለማመን በሚቸግር ዋጋ ሲሸጡ ስናይ የማኅበራዊ ድቀቱን መጠን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ 

ሌላው ከተማው የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች የሉትም፡፡ ላለፉት 40 ዓመታት ከቀበሌ አስተዳዳሪዎች እስከ ከተማ ከንቲባዎች ምን ሲሠሩ እንደነበር አላውቅም፡፡ መለስተኛ ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶችም ንጹሕና ደረጃውን የጠበቀ መፀዳጃ የላቸውም፡፡ ቢኖራቸውም ለአጠቃቀም ምቹ ባለመሆናቸው ወይም በአብዛኛው የተበላሹ ስለሚሆኑ ለመጠቀም የሚጋብዙ አይደሉም፡፡ አንዳንዶቹም ለበሽታ የሚዳርጉ ናቸው፡፡ ጥቂት የማይባል ‹ከተሜ› ነኝ ባዩም በየመ/ቤቱም ሆነ በየመዝናኛ ሥፍራዎች የሚያሳየው የመፀዳጃ ቤቶች አጠቃቀም እጅግ የሚያሳፍር ነው፡፡ ይህ የዐቅም ብቻ ሳይሆን የሥልጣኔ ችግር ነው፡፡ የከተማው ማኅበረሰብም የንጽሕና ባህል አለው ለማለት አልደፍርም፡፡ አፉን በውኃ መጉመጥመጥና ዐቅም ባይኖረው እንኳን በመፋቂያ እንጨት ጥርሱን ማፅዳት አይወድም፡፡ የእግር ሹራቡ ኳ! ክርችም! እስከሚል ድረስ አጥልቆት የሚዞረው ቊጥሩ ቀላል አይደለም (ይህንን ቅንጦት ነው የሚል ከሌለ በስተቀር)፡፡ በታክሲና በሌሎች የሕዝብ ትራንስፖርት መገልገያዎች የምንጠቀምና በዚህም ምክንያት በየጊዜው በሽታ የምንሸምት በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ 

አንድ ተጨማሪ ሃሳብ አክዬ አስተያየቴን ላጠቃል፡፡ የዐቅም ጉዳይ ተግዳሮት ይሆናል ካልተባለ በሽታን ሊያመጡ የሚችሉ ተዋሕስያንን (ጀርሞች/ባክቴርያዎች) ሊያጠፉ የሚችሉ ኬሚካሎችን (disinfectants) ሕዝብ በብዛት በሚጠቀምባቸው ቦታዎችና መገልገያዎች (የሕዝብ ማጓጓዣዎች) ለመርጨት ታስቧል ወይ?

በኅብረተሰቡም ሆነ በአገዛዙ በኩል የሚደረጉ የጥንቃቄ ርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ አምላከ ኢትዮጵያ ከዚህ መቅሠፍት ይሰውረን፡፡ 

Filed in: Amharic