>
5:16 pm - Monday May 24, 0460

ንቅዘት እና ቅጥፈትን ተቋማዊ ያደረገ አገዛዝ (ከይኄይስ እውነቱ)

ንቅዘት እና ቅጥፈትን ተቋማዊ ያደረገ አገዛዝ

ከይኄይስ እውነቱ

 

‹‹የእኔ ሀብት መጽሐፎቼ ናቸው››

 • ሟቹ የወያኔ አለቃ መለስ ዜናዊ

‹‹እኛ እንደሌሎች ስንሰርቅ አንገኝም››

 • የኦነጋዊው ኦሕዴድ/ብልጽግና አለቃ ዐቢይ አሕመድ

 

ላለፉት 30 ዓመታት ገደማ ተሸርሽረው ኅብረተሰባችንን ዕርቃኑን ካስቀሩት የእሤት ሥርዓቶቻችን መካከል እውነት እና ታማኝነት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡ እነዚህ በምንም የማንተምናቸው ታላቅ ዋጋ የምንሰጣቸው፣ የምናከብራቸውና የምንሳሳላቸው የመልካም ሥነምግባር/ግብረገብነት ዓይነተኛ መገለጫዎች በውሸት/ቅጥፈት እና ሌብነት ተተክተዋል፡፡ እነዚህ በሃይማኖት በባህል ፀንተው የቈዩ የሥነምግባር አለቶች በተፈጠረው ማኅበራዊ ድቀት ከሥር መሠረታቸው ተናግተዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በቀላሉ የማይጠገን አደጋ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መልካም እሤቶች ባንድ ጀንበር አይገነቡም፡፡ እነዚህ ከቤተሰብ እስከ ኅብረተሰብ ያለውን ግንኙነት እንደ ድርና ማግ አያይዘው የአንድ አገር ሕዝብነትን፣ ብሔራዊ ማንነትን ከሚገነቡ ጡቦች መካከል በዐበይትነት የምናያቸው ናቸው፡፡ በእነዚህና ሌሎች መልካም እሤቶቻችን ላይ ነው የመለስ ወያኔና የዐቢይ ኦነጋዊ ኢሕአዴግ አገዛዞች የዘመቱት፡፡

አገዛዞች ሁሉ የሚጋሯቸው የጋራ ባህርያት አሏቸው፡፡ ለአብነት ያህል የሕግ የበላይነት አለመኖር፤ ሕግን የጭቈና÷ የአፈናና ሥልጣን ማስጠበቂያ መሣሪያ ማድረግ፤ ሕዝብን ለመቈጣጠር ማስፈራራት÷ እስር÷ ግድያ÷ ከሕግ ውጭ ኃይልን እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን መጠቀም፤ የመንግሥታዊ አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት አለመኖር፤ መገናኛ ብዙኀንን ጨምሮ ሁሉንም የመንግሥት ዘርፎች መቈጣጠር፤ ሐሰተኛና የተዛባ መረጃዎችን ለሕዝብ መስጠት፤በማንአለብኝነት በጠራራ ፀሐይና መዋቅራዊ በሆነ መንገድ የሕዝብና የአገርን ሀብት መዝረፍ፣ ግለሰብእናን ለመመለክ ማዘጋጀት ወዘተ.፡፡ እነዚህ አጠቃላይ ባህርያት እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዘረኝነትን ገንዘቡ እንዳደረገው የኢሕአዴግ ዓይነት አገዛዝ ደግሞ የሕዝብን አንድነትና የአገርን ህልውና ለሥልጣን መሥዋዕት ማድረጉ፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለጠላትና ባዕዳን አሳልፎ መስጠቱ እና የዝርፊያውና ቅጥፈቱ ቅጥ ማጣት ልዩ ባህርያቱ ናቸው፡፡ 

በዚህ አስተያየት መግቢያ ላይ የተነገሩት አባባሎች በኢትዮጵያ ምድር የጎሠኛነትን ሥርዓት በሕግ የመሠረተው፣ ‹ክልል› የተባለ 9 ‹የባንቱስታን ግዛቶችን› አዋቅሮ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው በፍላጎታቸውና በምርጫቸው ከአንዱ ክፍለ ሀገር ወደ ሌላ ተዘዋውረው ለመኖርና ለመሥራት ያላቸውን ነፃነት የገፈፈው፣ የአገር ባለቤትነት (ዜግነት) መብት ያሳጣው፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የ ‹9 አገር ሕዝቦች› ያሰኘው፣ ቋንቋ ተራ መግባቢያነቱ ተዘንግቶ ከክቡሩ የሰው ልጅ በላይ ሆኖ ለክፍፍልና እልቂት ምክንያት ያደረገው የወያኔ/ኢሕአዴግ አለቃ እና የወራሹ የኦሕዴድ/ኢሕአዴግ አለቃ ንግግሮች ናቸው፡፡

የወያኔው አለቃ ውሸት ገንዘቡም ቢሆን ያልሆነውን አያስመስልም ነበር፡፡ በጉልበቱ ሥልጣን ከያዘበት ወደ ጥልቁ እስከወረደበት ጊዜ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር ተጣልቶ ነበር የኖረው፡፡ ዕኩይነቱና ዕቡይነቱ እስከ መቃብር ነበር፡፡ የመለስ የእጁ ሥራ የሆነው የኦሕዴዱ አለቃ በተግባር የመንደሩን ሰዎች ፍላጎትና አጀንዳ እየፈጸመና እያስፈጸመ፣ በአፍኣ ኢትዮጵያን እያነሳና እያወደሰ፣ ሥልጣኑን ላለማጣት በሁለት ልብ እያነከሰ፣ ዓይኑን በጨው አጥቦ ባደባባይ እየዋሸና እያስዋሸ፣ ኢትዮጵያን እየገዘገዘና እያስገዘገዘ ድፍን ሁለት ዓመት ሊሞላው የ15 ቀናት ዕድሜ ብቻ ነው የቀረው፡፡ 

የንቅዘት ስልቱና ዓይነቱ እንዲሁም መገለጫው ብዙ ነው፡፡ 

 • ለዝርፊያ የተመቻቸ መዋቅርና ተጠያቂነት የሌለበት ሥርዓት መፍጠር፤ 
 • ብሔራዊ መለያ የሆኑትን ጨምሮ ነባር ተቋማትን ማፍረስ፣ 
 • ከታሪክ ፣ ከትምህርት/ዕውቀት፣ ከእውነት መጣላት፤ ሐሰትን ማንገሥ፤ 
 • ከቊልፍ የመንግሥት መዋቅሮች እስከ ተራ ሠራተኛ ምደባ በሙያ ብቃት÷በችሎታና የሥነምግባር ከፍታ በያዘ ሰብእና (integrity) ሳይሆን በራስ ጎሣ አባልነት መሆን፤ የአገር ኢኮኖሚ የራስ በሚላቸው ጥቂት ጎሠኞች ብቸኝነት ቊጥጥር ሥር (monopoly) እንዲውል ማድረግ፤ 
 • ሕግን ባለመስከበር አገር ማዘረፍ በዚህም በተዘዋዋሪ ከሌቦች ጋር ኅብረት መፍጠር ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ 

ወያኔ የተባለው የሽፍቶች ቡድን አለቃ እነዚህ ለአብነት ከተጠቀሱት የንቅዘት መገለጫዎች ሺህ ጊዜ እጥፍ የሚሆኑ ድርጊቶችን በትእዛዙ ፈጽሟል አስፈጽሟል፡፡ 

 • ‹ወርቆች› ካላቸው ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦችና ቡድኖችን (ኤፈርት የንቅዘት ውጤት ነው) ባንድ ጀምበር ‹ባለሀብቶች› አድርጓል፤ በ10 ዓመታት ጊዜ ብቻ ከኢትዮጵያ በእነዚህ ኃይሎች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ባሕር ማዶ የተዛወረው 30 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር (5 የዐባይን ዓይነት ግድብ ሊገነባ የሚችል ገንዘብ) የሕዝብ ሀብት የወያኔውን አለቃ ካልመሰለ ማንን ይምሰል?
 • ባገር ውስጥ ደግሞ የወያኔ የውሸት ‹ባለሀብቶች› መላ ሀገሪቱን በወረራ መልክ እንዲቀራመቱ አድርጎ፣ የልማት ባንክን ከ40 ቢልየን ብር በላይ የማይመለስ ዕዳ ታቅፎ እንዲሽመደመድ ያደረገው ማነው? የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንም እንደዚሁ፤
 • በግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶች ስም በወያኔ ባለሥልጣናት በመቶ ቢሊዮኖች ከሚቈጠር ገንዘብ ዝርፊያ አለቃቸው ከደሙ ንጹሕ ነው?
 • ባንዴ እንደ እንጉዳይ ለፈሉት ‹ባለሀብቶች› የመንግሥትና/የሕዝብን ሀብት ሁሉ አመቻችቷል÷ ንግድና ኢንቨስትመንትን አዛብቷል÷ገበሬውን የበለጠ አደይህቷል፤
 • ለአገር ለወገን የሚጠቅሙ እውነተኛ ነጋዴዎችን፣ ኢንቨስተሮችንና የፈጠራ ሰዎችን ሀብታቸውን ጥሪታቸውን ዘርፏል÷ ድርጅታቸውን ዘግቷል÷ ለእስር ለስደት ዳርጓል÷ አልፎ ተርፎም ገድሏል፤ 
 • ኃላፊነት ከማይሰማቸው፣ ስምና ታማኝነት ከሌላቸው፣ ዘርፈው እብስ ከሚሉ አጭበርባሪ የውጭ ‹ባለሀብቶች› (flight-by-night scammers) ጋር አባሪ ተባባሪ በመሆን ዜጎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል፣ የአገርን ኢኮኖሚ በቊጥር አድጓል እያስባለ በተግባር ዕርቃን አስቀርቷል፤ 
 • ውሸትን አፍልቆ በልማዳዊነት ሳይሰቅቀው ከመናገር አልፎ በግብር ከፋዩ ሕዝብ የሚተዳደሩ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃኖችንና የፓርቲ ሚዲያዎችን በመጠቀም ውሸትን ተቋማዊ በማድረግ አብዛኛው ሕዝብ ከመንግሥት የሚተላለፉ መረጃዎችን እንዳያምን፣ እንዳይቀበል ብሎም የመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን እንዳይሰማ አድርጓል፡፡

ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ የዘራፊዎች አለቃ በእውኑ ሀብቱ መጽሐፍ ነው? የልብ እውርነት/ኅሊና ቢስነት ካልሆነ በቀር ይህንን ጉድ በንቅዘት አይታማም ብለው ጠበቃ የሚሆኑ ሰዎችን ምን እንበላቸው?

እስቲ አሁን ደግሞ የቃልና የተግባርን ስምረት ‹‹እኛ እንደ ሌሎች ስንሰርቅ አንገኝም›› የሚለውን ዋስትና ከሰጠው የኦሕዴድ/ኢሕአዴግ አለቃ ለማየት እንሞክር፡፡ ከወያኔ ትግሬ ጋር በአሽከርነት ዘመናቸው በግብረአበርነት የሚጋሯቸው አገራዊ ጥፋቶች እንዳሉ ሆነው፣ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ተረኛ ‹ጌታ› ከሆነ ከወያኔ ከቀሰሙት ‹ልምድ› በመነሳት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በንቅዘትና ቅጥፈት አዳዲስ ሬከርዶችን አስመዝግበዋል፡፡

ሲሰርቁ አለመገኘትና ሲያሰርቁ መገኘት ልዩነቱ ምንድን ነው? ስልቻ ቀልቀሎ እንደማለት አይደለም? 

 • የባንኮቹን ዘረፋ ምን ስም እንስጠው? 
 • የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግፍ የተሞላበት ዕደላ ምን እንበለው? 
 • በተረኝነት መንፈስ የሚደረገው የመሬት ወረራንስ? 
 • ይሉኝታ ባጣ መልኩ በአብዛኛው ማኅበራዊ መሠረቴ ነው ከሚለው ጐሣ ቢሮክራሲው ውስጥ ከሚደረገው የተራ ሠራተኞች ቅጥርና የኃላፊዎች ምደባ ጀምሮ በቊልፍ መንግሥታዊ ተቋማት የሚደረጉ ሹመቶች የምን መገለጫዎች ናቸው?
 • ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች አገርን ለዘር ፍጅትና ጭፍጨፋ ሲያዘጋጁና ሲቀሰቅሱ በሚያስደነግጥ ዝምታ አልፎ በተቃራኒው በአ.አ. እና በድሬደዋ የሰላማዊ ዜጎችን ሕጋዊ እንቅስቃሴ መንግሥታዊ መዋቅርን ተጠቅሞ በኃይል ማፈን ንቅዘት ካልሆነ ምን ትርጕም እንስጠው?
 • በንግድ ባንክ ላይ እየተካሄደ ያለው የጥፋት ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉ በምን ይገለጻል? በኦሕዴድ የታገዘው የኦነግ ቀጥተኛ ዘረፋ ሳያንስ፣ የኢትዮጵያውያን ሀብት በሆነ ባንክ ላይ ተረኛ ደናቁርትና ዘራፊዎችን በወረራ መልክ በማስቀመጥ ሕዝቡ ለፍቶ ያገኘውንና የቆጠበውን ለዘራፊዎች ሲሳይ በማድረግ በፋይናስ ተቋሙ እምነት እንዲያጣና ተቋሙ የእኔ አይደለም የሚል ስሜት እንዲፈጥር (የሚፈለገውም ይህ ስለሆነ) ማድረጉ በቦርድ አባልነት በኃላፊነት የሚሰይማቸው በተለይም ተረኞች ነን የሚሉ ባለሥልጣናት ድርጊት አይደለም?    
 • በመንግሥት/ሕዝብ ሀብት ለሥልጣን የሚደረግ የምርጫ ቅስቀሳ ንቅዘት ብቻውን ይገልጸዋል ወይ? 
 • የወያኔ አገዛዝ በዝርፊያ ያደለባቸውንና በአገር ላይ በተፈጸሙ ከፍተኛ የኢኮኖሚ/የፋይናንስ ወንጀሎች ሊጠየቁ ከሚገባቸው ነጋዴ ተብዬዎች ለምርጫ ገንዘብ መሰብሰብ የወንጀል ፍሬ ተጠቃሚ የመሆን ግብረአብረነት አይደለም? 

የወቅቱ የኢሕአዴግ አለቃ ይህን የሚያደርገው ምርጫ ስለሌለው ነው፤ ተገዶ ወይም ‹ትልቁን አገራዊ ሥዕል› በማየት ነው የምትሉ ወገኖች ካላችሁ ምድርም ብቻ ሳይሆን ሰማይም ይታዘባችኋል፡፡ ራሳችሁን አታታሉ፡፡ የአገር ህልውናን ከመፈታተን፣ ነባር ተቋማትን በተጠና መልኩ ከማፍረስ የበለጠ ምን ትልቅ አገራዊ ሥዕል አለ?

ጥያቄው በአገዛዙ አለቆች እጅ ተነስቶ በኪሳቸው ከቤሳ እስከ አእላፋት ብር መግባቱ ሳይሆን ለአገራዊ ሀብት ግዙፍ ዝርፊያ አመቺ የሆነ እና ውሸትን ተቋማዊ አድርጎ እውነት ቦታ እንዳይኖረው የሚያደርግ÷ለትውልድ መጥፎ ምሳሌ የሚሆን አስጸያፊ ልማድ የሚተክል ሥርዓት መዘርጋቱ ላይ ነው፡፡ በዚህ መለኪያ ኢሕአዴግ እንደ አገዛዝ÷ የተፈራረቁት አለቆቹም እንደ ግለሰብ አምባገነኖች፣ንቅዘትና ቅጥፈትን በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ገንዘብ ያደረጉና ተመዝነው የቀለሉ ናቸው፡፡

Filed in: Amharic