>

አጭር ማሳሰቢያና አጭር ትውስታ  (በእውቀቱ ስዩም)

አጭር ማሳሰቢያና አጭር ትውስታ 

 

በእውቀቱ ስዩም
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ፤ቆንጆ ቆንጆ ቃለመጠይቅ አድራጊ ጋዜጠኛ ሴቶች  በየሜዳው ማለቴ  በየሚድያው  ተበራክተዋል !!” It is a trap! “ጎበዝ ተጠንቀቁ ይህ  ነገር ለኛ ነው” ብሏል አዝማሪ ወርቄ!!
 በቆንጆ ሴት ተጠይቀህ  ስለሀገርና ስለፓርቲ ስትቀድ  ሳታስበው ልታሰምጣት  መፍጨርጨርህ   አይቀርም!  አንበሳው! ጀግናው! አይበገሬው!  መባል ውስጥ ውስጡን ሊያምርህ ይችላል፤ እና   ሳታውቀው፤ ክልልን ከክልል፤ ዞንን ከዞን ፤ዝሆንን ፤ከዝሆን የሚያጋጭ  ጦሰኛ ቃል ሊያመልጥህ   ይችላል  !! ስለዚህ   አንድ ነገር ከመናገርህ በፊት  “ይህ ሀሳቤ  ከጭንቅላቴ ነው  ወይስ ከቃጭሌ ነው የመነጨው?”  ብለህ ራስህን ጠይቅ!
ጥንታዊ ሴቶች  ተዋጊ ወንድ ይወዱ ነበር ፤ምክንያቱ ግልፅ ነው፤ በጊዜው የኑሮ ውጣውረድ በትጥቅ ትግል የታጀበ ነበር  ፤ ሴቶች  በጀግንነት ከወንዶች አንሰው ባያውቁም እንደ እርግዝና አይነት የተፈጥሮ ፀጋዎችም (ወይም እዳዎች )  የወንዱን ያህል እንዳይዋጉ  እንቅፋት ይሆኑባቸዋል::  ይህንን ሁኔታ ተዋጊ ወንድ በማጨት ያካክሱታል ፤ ጥንታዊት ሴት፤  አድኖ ወይም ቀምቶ ያሳድረኛል ፤ ወይም  ጩጩዎቼን ከነጣቂ ይታደግልኛል   ብላ የምታስበውን ጉልቤ  ወንድ  ብታፈቅር አይገርምም፤ እና  ያኔ ወንዶች ሴቶችን እሚጀነጅኑት ሊፈፅሙት ስለተዘጋጁት ጀብድ በመፎከር ነበር፤
 አሁን ዐለም  በብዙ መንገድ ቢቀየርም ጂናችን አልተቀየረም፤  ሴቶችን ለማማለል አለመጠን መጎረር ፤መፎከር ፤ ልናደርገው ከምንችለው  በላይ ቃል መግባት፤ አመላችንም ዘረመላችንም ሆኖ ቀጥሏል፤ እና ይሄን ስለማውቅ አንድ ፖቲከኛ ባንዲት ቆንጆ ሴት ቃለ መጠይቅ ሲደረግ ባየሁ ቁጥር  “ እሱ ይሁነን እንግዲህ “ እያልሁ እማልዳለሁ፤
  ከላይ ያቀረብኩ እውቀት  ከመከራ የተማርኩት ነው፤
ካነሳነው አይቀር ቃለ-መጠይቅ ድሮና ዘንድሮን እናውጋ:-

  ቃለ -መጠይቅ ድሮ:-

ጋዜጠኛ-  ቁርስህን ምንድነው የበላህ?
ወጋየሁ- ዱለት
ጋዜጠኛ- የልብስ ምርጫህ?
ወጋየሁ- ቢትልስ ሹራብ
ጋዜጠኛ-በትርፍ ጊዜህ ምን ያዝናናሃል ?
ወጋየሁ-ካርታ ጨዋታ ፤
The end!

ቃለ -መጠይቅ ዘንድሮ

ጋዜጠኛ – ዛሬ ቁርስህን ምን በላህ?
 አርቲስት –   ያው ሰው ሆነን  ስንፈጠር ፤ ሰውነታችን እንደ ሰውነት ምግብ መጠየቁ አይቀርም ፤ አርቲስት ደሞ እንደማንኛውም ሰው ምግብ ያስፈልገዋል ፤ ምን ልልህ ፈልጌ ነው፤  ለኔ   ትልቁ  ነገር ለምግብ  ሳይኖር ለህዝብ መኖር ነው ፤   ህዝብ እሚጠብቅብህን  ነገር ካበረከትክ  ቀኑን ሙሉ ባትበላ እንኩዋ የርሃብ ስሜት  አይሰማህም ፤ ወደ ጥያቄህ ስመጣ ቁርሴን የበላሁት  በቅርቡ የሚዳሰስና የሚቀመስ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበውን ጨጨብሳ ነው፤
 ጋዜጠኛ- የልብስ ምርጫህ ?
አርቲስት-  እንግዲህ ሁላችንም ወዲዚህ ምድር ራቁታችንን ነው የመጣነው ፤ ራቁታችንን ሆነን ይሄንን ምድር እንለቃለን ፤ ምን ልልህ  ፈልጌ ነው፤ ርቃኔን ይሸፍንልኝ እንጂ   የጣልያን ሱፍም ቢሆን ለመልበስ ዝግጁ ነኝ’
ጋዜጠኛ- በትርፍ ጊዜህ ምን ያዝናናሃል?
አርቲስት-በዚህ አለም ሁለት አይነት ሰዎች አሉ፤ ትርፍ ጊዜ ያላቸውና ከጊዚያቸው የሚያተርፉ፤ እኔ ከሁለተኛው ነኝ ::  ያለችኝን ትንሽ የረፍት ጊዜ የማሳልፈው  ከጉዋደኞቼ ጋር  መስቀል አደባባይ  ጉግስ በመጫወት ነው::
ጋዜጠኛ፤  ካነሳኸው  ላይቀር፤ የጉግስ ጨዋታን የፈጠረው ኢትዮጵያዊ ማን ይባላል?
 አርቲስት-  እንጃ ! የጥላሁን ጉግሳ አባት መሰለኝ::
Filed in: Amharic