>
5:13 pm - Monday April 18, 9132

አግራሞት ጭረው ካለፉ የሳምንቱ ኮቪድ-19 ተያያዥ ዜናዎች በጥቂቱ!!! (ሳምሶም ጌታቸው)

አግራሞት ጭረው ካለፉ የሳምንቱ ኮቪድ-19 ተያያዥ ዜናዎች በጥቂቱ!!!

 

 

ሳምሶም ጌታቸው
 ማዳጋስካር:- የ45 ዓመቱ የማዳጋስካር ፕሬዝደንት ራጆሊና ሀገራቸው የኮሮና ቫይረስን ሙሉ በሙሉ መፈወስ የሚያስችል ተዓምራዊ መድኃኒት እንዳላት የሚያሳውቅ ሚስጥራዊ ደብዳቤ ከሆነ ሰው እንደደረሳቸው አስታውቀዋል። ፕ/ቱ መድኃኒቱ ከዕፅዋት የሚቀመም መሆኑን ከመናገር ባለፈ ስለ ዕፁ ዓይነትና ዝርዝር ነገሮችን አልገለፁም። ሆኖም ግን በመድኃኒቱ ፈዋሽነት እንደሚተማመኑና ሙከራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ያስታወቁ ሲሆን፤ ሀገራቸው ማዳጋስካርም በመድኃኒቱ ብቃት የዓለምን ታሪክ እንደምትቀይር እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል ተብሏል።
ሩዋንዳ:- የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ለመከላከል ችሎት በቪዲዮ መጀመሯ ተነግሯል። በከተማዋ በአንድ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ ፍርድ ተጠባባቂ ተጠርጣሪዎች በማስክ አፍና አፍጫቸውን ሸፍነው፣ እጃቸው በካቴና ታስሮ ክፍሉ ውስጥ ወዳለ አንድ የቲቪ ስክሪን አፍጥጠዋል። ቤት ተወስኖ መቀመጥ በሚለው መመሪያ መሠረት ፍ/ቤቶች ሁሉ የተዘጉ ቢሆንም፣ አዳዲስ ወንጀሎች ግን መፈፀማቸው አልቆመም። ስለዚህ ነባር ክሶች መፍትሔ ሳያገኙ ፍ/ቤቶች በተዘጉበት ሌሎች አዳዲስ ክሶች መደመራቸው የኋላ ኋላ የስራ መደራረብ ጫና በመፍጠር የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያመጣ በማሰብ ችሎት በቪዲዮ መሰየም ማስፈለጉ ተነግሯል።
ቻይና :- ምርጥ ዕቃ እያስመሰለችና እያብለጨለጨች በምትሰራቸው መናኛ የህክምና ቁሳቁሶች የተነሳ፣ ብዙ ሀገራትን ሿሿ እየሰራች መሆኑ እየተነገረ ነው። በፈረንጆቹ ማርች ወር አጋማሽ ላይ የደች ጤና ሚኒስቴር ከቻይና የተገዙ ከ6 መቶ ሺህ በላይ ማስኮች ተገቢው ጥራት እንደሌላቸው ስለተደረሰበት ከየተሰራጩበት በፍጥነት እንዲሰበሰቡ ጥሪ ተደርጓል። በተመሳሳይም ስፔም ከቻይና የገዛቻቸው ከ60 ሺህ በላይ የመመርመሪያ ኪቶች ሀገሯ ከደረሱ በኋላ ስትመረምራቸው ተፈላጊው የጥራት ደረጃ የሌላቸው መሆናቸውን አረጋግጣ ክፉኛ ተበሳጭታለች። ስሎቬኪያም በበኩሏ ከቻይና የገዛቻቸው ከ1 ሚሊየን በላይ የህክምና ቁሳቁሶች የጥራት ደረጃቸው የዘቀጠ መሆኑን ደርሳበታለች ነው የተባለው። በነገሩ የተናደዱት የሀገሪቱ ጠ/ሚ ኢጎር ማቶቪች “አንድ የሚረባ የለውም በሙሉ ከቆሻሻ ጋር ወደ ወንዝ የሚወረወሩ ብቻ ነው” ብለዋል። በተመሳሳይም ባለፈው ወር ላይ ጆሴፍ ቦሬል የተባሉ አንድ የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት “አውሮፓ መንቃት አለባት [የተከተሰተውን ወረርሽኝ] በመልካም አጋጣሚነት በመጠቀም አህጉር ዓቀፍ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እየጦዘ መሁኑን መረዳት አለብን። “ቻይናም በየድርጊቷ ከአሜሪካ በተለየ እሷ ብቻ የደግ መጨረሻ፣ እሷ ብቻ አስትማማኝና ኃላፊነት የሚሰማት፣ እሷ ብቻ ዓለም ዓቀፍ አለኝታ መሆኗን በተግባር ከሚታየው ውጭ ያለ ይሉኝታ እየሰበከች ነው” ሲሉ ቻይናን ኮንነዋታል። አየርላንድም ከቻይና ከገዛቻቸው ብዛት ያላቸው ቁሳቁሶች ውስጥ ከ35.2 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ዋጋ ያላቸው፣ ፈፅሞ በጥቅም ላይ ሊውሉ እንደማይችሉ በመግለፅ አስፈላጊው ማብራሪያ እንዲሰጣት የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፋለች። [ነገሩ ሁሉ ዕንቆቅልሽ ሆኗል። የበለፀጉ ሀገራት በአንድ በኩል ቻይናን እንደ ጭራቅ የመሳል ዘመቻቸውን እያካኼዱ  በሌላ በኩል ደግሞ የቻይናን የቴክኒክ፣ የቁሳቁስና የልምድ ዕገዛ መጠየቃቸው ነገሩን ሁሉ ግራ አጋቢ አድርጎታል።]
አይስላንድ:- የተባለችው ትንሽዬ አውሮፓዊት ሀገር ከጠቅላላው 364,413 ሕዝቦቿ ውስጥ 10%ቱን የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርጋ ከተመረመሩት ሰዎች ግማሹ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ይህም ውጤት አጠቃላዩን የሀገሪቱን አማካይ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ያመላክታል ነው የተባለው። አስገራሚው ነገር ሁሉም ሰዎች ምንም ዓይነት የህመም ምልክት ያልታየባቸው ሲሆን፤ ሀገሪቱ በሕዝብ ብዛቷ አነስተኝነት፣ ከሌሎች ሀገራት ርቃ መገኘቷኗ ሳይንስ በእጅጉን የሚከበርባትና የሚተገበርባት በመሆኗ ቫይረሱን ለመከላከል በጣም የተሻለ ዕድል አላቸው ከሚባሉ ሀገራት ተርታ ከፊተኞቹ ነበረች ነው የተባለው። ሆኖም ግን የተገኘው ውጤት ከተገመተው በተቃራኒ መሆኑ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ስኬታማነት አሳሳቢ አድርጎታል ነው የተባለው።
 ታይላንድ:- የ67 ዓመቱ የታይላንድ ንጉሥ ራሳቸውንና ሃያ (20) ዕቁባቶቻቸውን ይዘው ኳራንታይን ከገቡበት ጀርመን ሀገር ከሚገኝና ሙሉውን ለብቻቸው ከተከራዩት ቅንጡ ሆቴል ወጥተው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተነግሯል። ንጉሡ ኮቪድ-19ን ለመከላከል በሚልና በቅርቡ “ንጉሣዊ አገዛዝ አንፈልግም!” በሚል በሕዝባቸው የተነሳባቸውን ተቃውሞ በሰበቡ ለማምለጥ፣ ሃያ ዕቁባቶቻቸውን ይዘው ከቆዩበት ሆቴል በመውጣት ወደ ታይላንድ የተመለሱት በዓመታዊ የንጉሣዊ ክብረበዓል ላይ ለመሳተፍ ነው ተብሏል።
ንጉሡ ወደ ሀገራቸው ከመመለሳቸው በፊት ያቀኑት ዋናዋን ሚስታቸውን ንግሥቲቷን ወዳስቀመጡበት ወደ ስዊዘርላንድ ከተማ ዙሪክ ሲሆን፣ በዚያም ጥቂት ቆይታ አድርገው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ከአገልጋዮቻቸው መካከል 119ኙ በኮሮናቫይረስ ተጠቅተው ሊሆን የሚችል ግምት በመፈጠሩ ቀድመው ሀገር ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል ተብሏል። በሀገሪቱ አጠቃላይ 2,423 የቫይረሱ ተጠቂዎች የተለዩ ሲሆን፤ 32 ሞት እና 940 ያገገሙ ተመዝግበውባታል።
     
ፈፅሞ ሳንዘናጋ፣ ከልክ በላይም ሳንጨነቅ መረጃዎችን እንመርምር፣ መመሪያዎችን እናክብር። አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፣ እጃችንን እንታጠብ።
Filed in: Amharic