>

ድንቅ ጥበብ ጎለጎታ !!! (ቴዎድሮስ ካሳሁን)

ድንቅ ጥበብ ጎለጎታ !!!

ቴዎድሮስ ካሳሁን
 አምላካችን ዓለምን ያዳነው በዘሩ አልያም በቀለሙ ሳይሆን በደሙ ፈሳሽነት ነው!
እዩት ይሄን ጠቢብ ሸራው እስኪደማ
በቀይ እየወጋ በደም እየሳለው
እንጨት አመሳቅሎ ዳግም ክርስቶስን ጨርቁ ላይ ሰቀለው።
ቀራኒዮ ሆነ የወጠረው ሸራ
ጎሎጎታ ሆነ የወጠረው ሸራ
አሁን እስኪመስል ስቃዩ እያስፈራ
አሁን እስኪመስል ስቃዩ እያስፈራ።
ደም ከደም አረገው አበዛበት ጣር
ቡሩሹን አሹሎት እንደጎኑ ጦር
እየወጋ ሳለው በጣም ጨቀነበት ገብረክርስቶስም ክርስቶስ ላይ ከፋ
የቆዳው አይነቱ በደም ተከልሎ ዘሩ እስከሚጠፋ
እየወጋ ሳለው እየሳለ ወጋው
ዘሩ እስከማይለይ መልኩ ዝም ብሎ
መልኩ ዝም ብሎ ደሙ እስከሚናገር
የትም ያለ ፍቅር እንዳይኖረው ሀገር
እንዳንለው ፈረንጅ እንዳንለው ጥቁር እንዳንለው ቀይ
በመስቀል ላይ ሞቶ ያየውን ስቃይ
በቆዳ በቀለም እንዳናሳንሰው
በደሙ ተሰቅሎ ሰው ያዳነውን ሰው።
ከቀናት ባንዱ ዕለት ሰዎች ሲማገቱ በቀለሙ ጉዳይ ሲከራከሩበት
በተመፃዳቂ የምሁር አንደበት
በአንዱ አፍ ሲጠቁር ባንዱ አፍ ሲነጣ
መታገስ አቃተው ሰዓሊው ተቆጣ
ስሜቱ ገንፍሎ በቡርሽ ጫፍ ወጣ
ሀሳቡን የሚገልፅ ቀለም እስከሚያጣ
ሸራላይ ሰቀለው እንጨት አመሳቅሎ
አልወጣልህ አለው ፍቅርን ስሎ ስሎ
ስሎ ስሎ ስሎ ፍቅርን ስሎ ስሎ
በሳለው እየወጋ በደማው እየቀባ
ክርስቶስ ደሙ እንጂ ዘሩ አልተሰቀለም
እንጨቱ ላይ ያለው እውነት ይሄ አይደለም
እያለ እስኪናገር የስዕሉ አንደበት
ገብረክርስቶስም ለክርስቶስ እሚሆን ቀለም እስኪያልቅበት
በነጩ ሸራ ላይ እስከአሁን እሚወርድ ደም አፈሰሰበት።
ቀለም ቀይ ቀለም የደም ቀለም የጥላ ቀለም
የሁሉ ነው እንጂ የማንም አይደለም
ፍቅር ዘር አይደለም ።
ለሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ የተፃፈ
ታኅሳስ 2001
Teddy Afro
Filed in: Amharic