>

 አውዳሚነት ይውደም!!! (መስከረም አበራ)

የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሲኒማ ቤት ማፍረስ  የምኒልክን አሻራ ከአዲስ አበባ የማጥፋት ኦነጋዊ የአውዳሚነት አባዜ ነው!!!

መስከረም አበራ
ተገቢው ነገር መንግስት ቅርስ ጠባቂ፣ህብረተሰብ  ተባባሪ መሆኑ ነበር።በእኛ ሃገር እውነታው ተገላቢጦሹ ነው። እዚህ ሃገር የመንግስት ስልጣን ላይ ከመቀመጥ ጋር አብሮ የሚመጣ የማፍረስ አባዜ ሳይኖር አይቀርም።የደሃን ቤት በክረምት ማፍረስ፣ቅርስ እየፈለጉ ማፍረስ፣ሃገር የቆመችበትን የሚይታይ ማያያዣ ማፍረስ፣የወጣት ገላ በጥይት ማፍረስ ወዘተ።
ማፍረስ የማናለብኝነት መገለጫ ነው! በማታ ማፍረስ ደግሞ ተንኮል፣የፖለቲካ አሻጥር፣በቀን በብርሃን የማይገለጥ የፖለቲካ አላማ የማያጣው ነገር ነው።ቀን ኮሮና ያሳሰበው መስሎ አፉን አፍኖ ህሙማንን ሲጠይቅ የዋለ ከንቲባ ማታ የሚሰራው ማፍረስ ከሆነ  ከኮሮና የባሰው ቫይረስ አሁንም በደጃችን ነው።ይህ ከኮረና የባሰ ቫይረስ ማስመሰል ነው!
 የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሲኒማ ቤት ማፍረስ  የምኒልክን አሻራ ከአዲስ አበባ የማጥፋት ኦነጋዊ የአውዳሚነት አባዜ ነው። ክፉ ወረርሽኝ  ገብቶ ሃገር በሚሸበርበት የጭንቅ ወቅት በሌሊት ግሬደር አጓጉዞ ቅርስ ማፍረስ የነታከለን ኦነግ ወለድ ህመም ጥልቀት ያሳያልት እንጅ ሌላ ትርጉም የለውም። ትምህርቱን አቋርጦ ኦነግን ፍለጋ ከቦረና እስከ ወለጋ የተላጋ ከንቲባ ነገ ደግሞ በምኒልክ ሃውልት ላይ ድማሚት ይተኩሳል !
 የገረመኝ ደግሞ “ሲኒማ ቤቱ በአሁኑ ሰዓት ምንም እየሰራ አይደለም ፣ጥቅም የለውምና መፍረሱ ችግር የለውም” የሚል ክርክር ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሳይቀር መምጣቱ ነው። እንደው ለመሆኑ የፋሲል ግንብ፣የአባ ጅፋር ቤተመንግስት፣የአክሱም ሃውልት በአሁኑ ወቅት የየትኛው ሚኒስተር መስሪያ ቤት ቢሮ እያገለገለ ስለሆነ ነው  በማታ በግሬደር ያልፈረሰው?  አውዳሚነት ይውደም!!
Filed in: Amharic