የጄኔራሎቹ ቃለ ምልልስ !
ውብሸት ታዬ
(የመጀመርያ ክፍል)
በኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ምክንያት እቤት ስንውል ጊዜያችንን በተለያዩ ጠቃሚ ነገሮች እንደምናሳልፋቸው ይገመታል፡፡ ለዚሁ ዓላማ በሚል ከዛሬ ሰባት ዓመታት በፊት በዝዋይ እስር ቤት ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ሃሳባቸውን በመጀመርያ መጽሐፌ(የነፃነት ድምጾች ላይ) ለንባብ ካበቃሁላቸው የእስር አጋሮቼ ሁለቱ ብ/ጄ/ል ተፈራ ማሞ እና ብ/ጄ/ል አሳምነው ጽጌ ናቸው፡፡
ጊዜው የቆየ ቢመስልም በወቅቱ የተነሱት ነገሮች ምን ያህል መሰረታዊ እንደሆኑ ያስተዋልኩት መለስ ብዬ ጽፎቹን የመመርመር እድል ባገኘሁበት በዚህ ወቅት ነው፡፡
በተለይ መጽሐፏን ማንበብ ያልቻላችሁ ወገኖች አጋጣሚውን ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ በጽሑፉ ርዝመት እንዳትሰለቹ በሚል የሁለቱንም ጅንራል መኮንኖች ቃለ ምልልስ በሁለት በሁለት ክፍል አቀርብላችኋለሁ፡፡ ሌሎችም ወደፊት በተከታታይ የማቀርብላችሁ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ወገኖች ሃሳብና ተሞክሮ ይኖራል፡፡ (ታዲያ ርቀታችንንና ንጽናችንን እየጠበቅን)
**********//**********
⨳“የሆነው ሁሉ ብዙሃኑን ሕዝብ ይጠቅማል ብለን ጊዜ ወስደንና አስበንበት ያደረግነው በመሆኑ፣ ከሕዝቡ ምንም ነገር መሸሸግ የለበትም ብዬ አምናለሁ፡፡›› በማለት ነበር ስለ 2001ዱ ‹‹የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ›› የሚል
ስያሜ፣ የተሰጠው ክስ ላነሳሁላቸው ጥያቄ መመለስ የጀመሩት፡፡
*“እስኪ ስለራስዎ በአጭሩ ያጫውቱኝ፤ ወደ ትግል መቼ፣ እና እንዴት ገቡ? ከእነማን ጋር ነበሩ? የትግል ሜዳ ልዩ ትውስታዎችዎ ምንድናቸው?” አልኳቸው፡፡
⨳የትግል እንቅስቃሴዬ የተጸነሰው በ1967 ዓ.ም ነበር፡፡ በወቅቱ የትውልድ አካባቢዬ በነበረው ላስታ አውራጃ ውስጥ የደርግን መምጣት ተከትሎ፣ ዓላማቸው የተለያየ ሆኖም ተመሳሳይ መገለጫ ያላቸው የዐመፅ እንቅስቃሴዎች ይካሄዱ ነበር፡፡ ብርሃነመስቀል ረዳ በአየር መንገድ ላይ ጥቃት የሰነዘረውም ያኔ ነበር፡፡ ደርግ ደግሞ ጉዳዩን
ከሥሩ መርምሮ ከመፍታት ይልቅ ጦር ላከ፡፡ ዕድሜያችን 10 ዓመት የሞላ ልጆች ሳንቀር ጫካ ገባን፡፡…”
*‹‹እና ከዚያ ግዜ ጀምሮ በረሃ ነበሩ?››
⨳‹‹አይ …ያ የተደራጀ እንቅስቃሴና ሕዝባዊ ዓላማ ያነገበ ዐመጽ አልነበረም፡፡ ወደ ትግሉ የገባሁት በ1976 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኢህዴን/ በሚባለው ድርጅታችን ሥር፣ ከሁሉም ብሔረሰቦች የመጡ ኢትዮጵያውያንን አቅፈን እንታገል ነበር፡፡››
*“እስኪ ከታዋቂ ባለሥልጣናት ውስጥ ለዚህ አባባልዎ ማስረጃ የሚሆኑ የተወሰኑ ይጥቀሱልኝ?” ጨዋታው እየሳበኝ ሄደ፡፡
⨳አቶ አዲሱ ለገሰ (የጭሮ ተወላጅ ኦሮሞ)፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ /ሲዳማ/፣ አቶ ያሬድ ጥበቡ (ጌታቸው ጀቤሳ በሚል የበረሃ የትግል ስም ይታወቃል፤ አማራና ኦሮሞ)፣ ታምራት ላይኔ /ጉራጌ/ እና ኩማ ደመቅሳ፣ አቶ አባዱላ ገመዳና ሌሎችም ነባር የኢህዴን ታጋዮች ናቸው፡፡”
*“ክቡር አቶ አባዱላ እና አቶ ኩማ የኢህዴን አባላት ነበሩ? መቼ ነበር የተቀላቀሉት?”
⨳“እንደሚታወቀው ሻዕቢያ ማርኳቸው ለረዥም ጊዜ ቆይተዋል፡፡ ከባድ የጉልበት ሥራ እና ምሽግ ያስቆፍሯቸው ስለነበር ወደ ኢህዴን በድርድር እንዲመጡ በተደረገበት ወቅት… በነገራችን ላይ ከእኛም ይቀድማሉ… የተሻለ አድካሚ
እንቅስቃሴዎችን የመቋቋም ልምድ አዳብረው ነበር፡፡ በእርግጥ ይህ የምሽግ ቁፋሮና የጉልበት ሥራ በሌላ በኩል ወታደራዊ አቋማቸውን አደብዝዞት የላብአደር ባህሪ አላብሷቸው ነበር፡፡ አንዳንዶች ‹ኤርትሮ-ማሲ› ይሏቸው
ነበር፡፡”
*“ምን ለማለት ነው?”
⨳“ኤርትሮ-ኤርትራ ለማለት ሲሆን ‹ማሲ› ደግሞ መማስ ለማለት ነው፡፡ የኤርትራን ምሽግ መቆፈር ወይም መማስ የሚል ቀልድ ቢጤ ነው፡፡… ትግሉ የተለያዩ ስኬቶችን እያስመዘገበ ቀጠለ፡፡ በእርግጥ ውስጣዊ ችግሮችና ራስን ችሎ
የመቆም ጥያቄዎችም መነሳት ጀመሩ በኋላ…”
*“እስኪ ስለዚህ ራስን የመቻል ጥያቄ ይንገሩኝ ምን ነበር?” አልኳቸው ወደ ሌላ ነጥብ ሳይገቡብኝ፡፡
“የህወሓት የበላይነትን የማሳየትና ያላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ነበር መንስኤው፡፡ ለድርጅታችን የሚላኩ ደብዳቤዎች ሳይቀሩ በህወሓት ይጠለፉ ጀመር፡፡ 1978 ዓ.ም አጋማሽ ነው፣ ይህ ሁኔታ የኢህዴንን አመራር እንኳ ለሁለት ከፈለው፡፡ ያሬድ ጥበቡ፣ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሠ እና ዑስማን የተባሉት አመራሮች ጣልቃ ገብነቱን ሲቃወሙ፤
ታምራት ላይኔ፣ ኃይሌ ጥላሁን፣ ታደሰ ካሳ /ጥንቅሹ/ ለህወሓት ተከራከሩ፡፡ ጉዳዩ ጣልቃ ገብነት ሳይሆን ውዥንብር እንዳይከሰት ለመከላከል የተደረገ ነው አሉ፡፡ በኋላ በ1981 ዓ.ም ዳንሻ ላይ የአቅጣጫ ለውጥ የተደረገበት ስብሰባ ተጣራ፡፡ አወያዮቹ መለስ፣ ስዬ፣ ተወልደ፣ አለምሰገድና ዓባይ ነበሩ፡፡…”
“… ኢህዴንም 81 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ‹መስመር ማጥራት› የተባለውን ጉባኤ ዋግ ውስጥ በመጥራት፣ 20 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተመረጡ፡፡ ቅድም የጠቀስኩልህ አቶ ኩማ፣ አባዱላ እና ኢብራሂም መልካም የኮሜቴው አባላት ሆነው
ተመረጡ፡፡ ከጉባኤው በኋላ ክረምት ላይ ኢህአዴግ ተመሠረተ፡፡”
*“ኦህዴድ የተመሠረተው ደራ ላይ ነው የሚባለው እውነት ነው?” ለማጥራት የፈለኩት ግምት ስለነበር ያነሳሁት ጥያቄ ነው፡፡
⨳“በኢህዴን ውስጥ የነበሩትን የኦሮሞ ተወላጆች በዚያው ዓመት ክረምት ላይ አሰባስበው የመሠረቱት ትግራይ ላይ ነው፡፡ ደራ የሚባለው ወደ ኦሮሚያ ክልል ጠጋ ተብሎ ምሥረታው ይፋ የሆነበት ነው፡፡”…ቀጣዩን ክፍል ነገ አቀርብልዎታለሁ