>

የሀውልት ጥብቅና፤ አዲስ ነገር ከመፍራት ወይስ የመነጋገሪያ ጭብጥ ከማጣት? (ያሬድ ሀይለማርያም)

የሀውልት ጥብቅና፤ አዲስ ነገር ከመፍራት ወይስ የመነጋገሪያ ጭብጥ ከማጣት?

ያሬድ ሀይለማርያም
ከቤተመንግስቱ ደጃፍ የቆመው የፒኮክ ሀውልት ለምን ትኩረት እንደሳበ ይገባኛል። እኔን ግን ያን ያህል አያሳስበኝም። ለእኔ ዋናው አሳሳቢ ነገር ከቤተመንግስቱ ደጃፍ የቆመው ሀውልት የየትኛው እንስሳ ይሁን የሚለው ሳይሆን ቤተመንግስቱን የተቆጣጠረው የፖለቲካ ኃይል ባህሪ ምን ይሁን፣ አገሪቱን የሚመራበት ቅኝት ምን ይመስላል፣ የፖለቲካ መህዳሩን በምን ደረጃ አስፍቶታል፣ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ እና ለዴሞክራሲ እሴቶች መጎልበት ያለው ግምት እና የሚሰጠው ከብደት ምን ያህል ነው፣ ለዜጎች ክብር እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ያለው ቀናዊነት እና ቁርጠኝነት በምን ይገለጻል፣ ዝርፊያኔ ይጠየፋል ወይ የሚሉት ናቸው እኔን የሚያሳስቡኝ።
 ከአንበሳ ሀውቶች እና ምልክቶች ጀርባ ምን አተረፍን? ቤተመንግስቱ የሰው አውሬዎች ምሽግ ሆኖ መኖሩ ተረሳ ወይ? በአንበሳ ሀውልቶች የተከበበው ቤተመንግስ ውስጥ የነበሩ የሰው አውሬዎች የፈጁትን ሕዝብ እረስተን ደጃፉ ላይ ስለሚቆም ሀውልት አይነት ሙግት መግጠማችን እና ጥብቅናም መቆማችን ምን ይሉታል።
ካስፈለገ ቤተመንግስቱ ብዙ በሮች ስላሉት የአንበሳንም፣ የጭላዳ ዝጀሮንም፣ የጦጣንም፣ የጅብንም፣ የቀይ ቀበሮንም፣ የግመልም ሆነ ሌላ እንስሳ ሀውልት እንደ ምሳሌነታቸው ማኖር ይቻላል።
መጀመሪያ ለመልካም ስራዎቻቸው ሀውልት የምናቆምላቸው መሪዎች እንፍጠር፣ ቤተመንግሥቱ ሰው ሰው ይሽተት። ግፍ፣ ተንኮል እና መከራ የሚደገስበት ሳይሆን መልካም አገራዊ እራይ የሚጠነሰስበት፣ ቅንነት፣ ፍቅርና ፍትህ የሚፈልቁበት ይሁን። በአንበሳ ምስል ዘመን በርሃብ፣ በድህነት እና በክፋ አገዛዝ አናቷን እየተመታች ያቀረቀረችው አገራችን ካቀረቀረችበት ቀና ብላ ዜጎቿ ከሰው እኩል በክብር የሚቆሙባት፤ ኢትዮጵያምጠብቅክብርና በሥልጣኔ ከሌሎች አገሮች ተርታ የምትቆምበት እንድትሆን እንረባረብ። ሌላው እዳው ገብስ ነው። ሀውልት የስሜት መግለጫ ነው። እንደሚገነባው ሁሉ ፈራሽም ነው። ነገ ደግሞ ሥልጣን የሚይዙ ሰዎች የጦጣን ሀውልት ይመርጡ ይሆናል። መዘንጋት የሌለበት ያገሬ ሰው እንኳን ፒኮክን ሌላ አውሬም ማልመድ የሚችል፤ መንግሥትንም ማቅበጥና መታገስ የሚችል፤ ግፈኞችንም 44፣ 17፣ 27 አመት የሚታገስ የበዛ ጨዋ መሆኑ።
እና ባጭሩ ፒኮኳን ለቀቅ አድርገን ጥሩ መንግስታዊ ሥርዓት ለመገንባት ወገብን ጠብ ማድረግ ይሻላል።
Filed in: Amharic