
ሐብታችንን እናስመልስ!

መምህር ታሪኩ አበራ
ጀርመን ውስጥ በኢትዮጵያ ብራና መጻሕፍት ብቻ ተመራምረው ያቋቋሟቸው መድኃኒት ፋብሪካዎች አሉ።
በሀገራቸው ዩኒቨርሲቲዎች የግዕዝ ቋንቋን እስከ PhD ድረስ የሚያስተምሩበት ምሥጢርም ይኸው ነው።†
ከ 50,000 በላይ የኢትዮጵያ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት በውጭ ሀገር ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከ11,000 በላይ የሚሆኑት በማይክሮ ፊልም ተነስተዋል (digitalized ሆነዋል)። የሄዱት በዘረፋ ነው። (አሁንም ዘረፋው አልቆመም)።
ከእነዚህ መጻሕፍትም አብዛኞቹ የፍልስፍና፣ የህክምና፣ የሥነ ምግባርና ሥነ ልቦና፣ የሥነ ከዋክብትና (ህዋ ሳይንስ)፣ የሥነ ዕጽዋት፣ የአዕዋፍና እንስሳት ምርምር ውጤቶች ናቸው።
ለምሳሌ ጀርመን ውስጥ በኢትዮጵያ ብራና መጻሕፍት ብቻ ተመራምረው ያቋቋሟቸው መድኃኒት ፋብሪካዎች አሉ።በሀገራቸው ዩኒቨርሲቲዎች የግዕዝ ቋንቋን እስከ PhD ድረስ የሚያስተምሩበት ምሥጢርም ይኸው ነው።በተለይ ምዕራባውያን በትልልቅ ሙዝየሞቻቸው ውስጥ በክብር ካስቀመጧቸው ውድ ሀብቶቻቸው ውስጥ የእኛ ብራና መጽሐፎች ይገኙበታል። በግልጽ እየተጎበኙ ገቢ ከማስገኘታቸውም በላይ ለምርምር ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
የእኛ ብራናዎች የማይገኙበት ሀገር አለ ለማለትም ይከብዳል። አብዛኛዎቹ ግን አውሮፓ ውስጥ ናቸው።

በቫቲካን (ጣሊያን ውስጥ) 1,082
በፈረንሳይ 1,034
በእንግሊዝ 850
በአየርላንድ 66
በጀርመን 820
በስዊድን 88
በሰሜን አሜሪካ 400 የብራና መጻሕፍት በሙዝየሞችና በቤተ መጻሕፍት ውስጥ በግልጽ ተመዝግበውና ካታሎግ ተሠርቶላቸው ይገኛሉ። (እነዚህ ለምሳሌ የቀረቡ ናቸው)።
ከታሰበበትና ከተሠራበት እነዚህንም ሆነ ሌሎች ቅርሶችን የማስመለስ መብቱ አለን። የእኛ መሆናቸው በግልጽ የተመዘገበና የታወቀ ስለሆነ።
(የአክሱም ሐውልትና የላሊበላው አፍሮ አይገባ መስቀ ል መመለሳቸውን ልብ እንበል… ከተሠራ የራሳችንን ቅርስ የማስመለስ መብታችን የተጠበቀ ነው)። ግን እኛ ይህ ጉዳያችን የሆነ አይመስልም። በተለይ አቅሙና እውቅናው ያለን አካላት… ከቤተ ክህነቱ ጀምሮ ዝም ብለናል።


እንግሊዞች አፄ ቴዎድሮስን ለመውጋት መጥተው መቅደላ ላይ የነበረውን ታላቅ የብራና መጻሕፍት ቤተ መዘክር ዘርፈው በብዙ ሺህ መጻሕፍትን ወሰዱ። ጣሊያኖች በሁለቱም ጦርነቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ብራና መጻሕፍትን ዘረፉ።
ሌሎች በሃይማኖት “ሚሽን” አሳበው ብዙዎችን ሰረቁ… ለምን? የእኛ መጻሕፍት የያዙት እውቀት ጥልቅነትና የሥልጣኔ ምሥጢርነት ቢገባቸው ነው)።