>
5:13 pm - Friday April 20, 7838

የሱፍያ–ሰልፍያ ጋጋታና የኢትዪጵያ ሙስሊሞች እጣ ፈንታ!(ሞሀመድ ጀማል አህመድ)

የሱፍያ–ሰልፍያ ጋጋታና የኢትዪጵያ ሙስሊሞች እጣ ፈንታ!

ሞሀመድ ጀማል አህመድ
የኢስላም አስተምሮ የሚቀዳው የአላህ ቃል ከሆነው ቅዱስ ቁርዓንና ከነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) የለት ተለት አስተምሮ (የተግባር፣ የንግግር ወዘተ) ከሆነው ሱና (ሀድስ) ነው።  ነብዮ መሐመድ (ሰዐወ) አስረክበውን የሄዱት ከነዚህ ሁለት ታላላቅ መፀሀፎች በሚቀዱ ህጎች የሚተዳደረውን አንድ ድን “ኢስላምን” ብቻና ብቻ ነው። ነብያችን ካለፉ ማግስት ጀምሮ የተፈጠሩና እስከ ዛሬም ድረስ እየተፈጠሩ ያሉ የኢስላም ሴክቶች ሁሉ ዱንያዊ ጥቅምና ዝና በመሻት የተፈጠሩ ናቸው። ወንድም አብዱልጀሊል ካሳ እንዳብራራው በሀገራችን የገባውም ነብዩ መሐመድ አስተምረውንና ትተውሉን ያለፉት “ኢስላም” እንጅ ሱፍያ ወይም ሰለፍያ የሚለው አይደለም። አሁንም ቢሆን ሱፍያ ወይም ሰለፍያ የሚባሉት ባዕድ ቅጥያዎችን በድኑ ላይ ቀጥለው የሚጠቀሙት 5%  እንኳ  የሚሆነውን ሙስሊም የማወክሉ የፓለቲካ አጀንዳ ተቀባይና ከመንግስት ጋር የጥቅም ትስስር ያለቸው ከተሜ ሙስሊሞች ናቸው። በግምት 95% የሚሆነው ሙስሊም የልጁን ስም ሶፍያና ሰይፉ ብሎ ካወጣ እንጅ በሱፍያና ሰለፍያ የተፈረጀ ሀይማኖት የለውም አያቅም። አስረግጨ መናገር የምችለው 95% በላይ ለሚሆነው ኢትዪጵያውያን ድኑ ምንም ቅጥያ የለለበት “ኢስላም” ብቻና ብቻ ነው።
በሀገራችን “የሱፍያ ሰለፍያ”  “የመጤና ነባር” ዜማ ጮህ ብሎ መዘመር መቀንቀን የጀመረው በዋናነት ከ1983 በህዋላ ነው። እነ ሀጅ መሐመድሳኒ የመሳሰሉ ተላላቅ አሊሞች ሙስሊሙን ሲያገለግሉ ሲካድሙ የነበሩት ሳይከፋፍሉ ኢስላም በሚል እንጅ ሱፍያ ሰለፍያ በሚል አንጃ ፈጥረው አልነበረም። እነዚህ የመከፋፈል አጀንዳዎች በመንግስት የደህንነት ክፍል ተዘጋጅተው ለመጅሊስ የተሰጠው በቅርቡ ከ1983 በህዋላ ነው። መንግስት ሆን ብሎ ሙስሊሙን ከፋፍሎ ለመግዛት የፈጠረውን አጀንዳ በጥቅም የታወሩና የደነቆሩ ወይም የተሸወዱ የመጅሊስ አመራሮች ለመንግስት ተባባሪ በመሆን ክፍፍሉና መፈራረጁ መሬት እንድይዝ አድርገዋል። ህወሃት መራሹ ኢህአደግ አይሁዱዊ ፕሮፌሰር ኃጋይ ኢርሊችን የመሳሰሉ መሰረታዩ የኢስላም ጥላቻ ያላቸውን ፀሃፍያን በመቀጠር ክፍፍሉ የሊትሬቸር መሰረት እንድይዝና በሀገሪቱ ፓሊሲም የተቃኘ እንድሆን አድርጓልል። አሁን እራሱን ሱፊ ነኝ እያለ የሚጠራው አናሳ በከተሜ የተሰበሰበ ቡድን ዋና የህወኃት ፓሊሲ ፈፃሚና የሙስሊሙ መምቻ ሁኖ ቆይቷል። ይህ ቡድን አለምን አረዳዱና በአመንክዮ እጅግ የደከመ ስለሆነ ሌሎችን የማሳመን አቅሙ በእጅጉ የወረደ ቡድን  ነው።
ስለሆነም ይህ ቡድን (እራሱን ሱፍያ ብሎ የሚጠራው) ጥቅሙን ለማስጠበቅ  3 ዘደዎች ይጠቀማል።
1) እራሱ ትናንት የመጣ መጤ ሆኖ ሳለ እራሱን ነባር እስልምና እያለ ይሰይማል። ሌሎችን በመጤነት ይከሳል። እራሳቸውን ሙስሊም ብለው ኢስላምን አስተምረው ያለፉ ኡለሞችን የሱፍያ ቀሚስ በማልበስ በስራቸው ሲኩራራ በስማቸው ሲመጀንባቸው ይታያል።
2) የህዝበ ሙስሊሙን መሰረታዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠት ከመንግስት ደህንነቶች ጋር በመሞዳሞድ ተቀናቃኝ ብሎ ያሰበውን አካል ይመታል ያስመታል። ይህ አካል ላለፉት 8 አመታት መጅሉሱን በመቆጣጠር ዋና ስራው ይህ ነበር። ይህ ቡድን ከደህንነት ጋር ሆኖ አንዋር መስጅድ ላይ ቦንብ ያስጣሉ ሱፍያ የሚላቸውን የራሱን ወገን ሸህ ኑሩን ያስገደለ ነው። አሁንም የፌደራል መጅሊሱን ቁልፍ ቁልፍ ቦታ በመቆጣጠር “ለዶ/ር አብይ ደውየ እናገራለሁ” እያለ እንደ ህፃን ልጅ ማስፈራራት የሚፈልግ ነው።
3) ልክ መንግስት ጋር በሚሞዳሞደው መልኩ ሙስሊም ካልሆኑ ወገኖች ጋር በመተባበር ተፎካካሪ ያላቸውን ሙስሊሞች ለማፈን ይሞክራል። የሙስሊሙን መሰረታዊ ጥቅሞች አሳልፎ በመስጠት የቡድንና የግል ጥቅሙን ያስከብራል። ሌላውን በአፍራሽና በፀረ–መቻቸል ጎራ በመመደብ ሙስሊም ካልሆኑ ወገኖች ጋር ተቻችየ ወይም ችየ የምኖረው እኔ ብቻ ነኝ ይላል።  ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖችን ተበባበሩኝ እንጅ እናንተን የሚያስከፋ ነገር አልናገርም አልሰራም ብሎ ቃል ኪዳን ያሰረ MoU የተፈራረመ ቡድን ነው።  ይህ ቡድን በአባቶቻችን ገድል የሚነግድ ጥቀመኛ አንጃ ነው። ቡድኑ ሰሞኑን “ነጃሽ” የሚለውን ስም አታንሱብኝ ያለውም ለዛ ነው።
 ይህ እራሱን ሱፍያ ብሎ የሚጠራው አንጃ በቀደምት አሊሞች ስራ ከመመካትና በስማቸው ከመመጀን የዘለለ ለህዝበ ሙስሊሙ የሚሰራው ነገር የለም አቅሙም ፍላጎቱም የለው። በአስተምሮም ሆነ በመስጅድ መድረሳ ግንባታ የለበትም። እራሱም አይሰራ ሰውም አያሰራ። ይህ ቡድን በእድሚያቸው የጃጁ፣ ምንም እንኳ በደረሰንት ሀይማኖታዊ እውቀት ቢኖራቸውም በዘመናዊ ት/ት ቤት በር ያላለፉ በአማርኛ መፃፍና ማንበብ የማይችሉ፣ ከቴክኖሎጅ የራቁና አለም በምን አይነት የስልጣኔ ደረጃ ላይ እንዳለች የማያገናዝቡ አዛውንቶችን ጀለብያና ኩፍያ አልብሶ ሱፍያ ብሎ ፊት ለፊት በማቅረብ ህዝበ ሙስሊሙን ይበዘብዛል። መንግስትን ይሸውዳል።
ማጠቃለያ
ከዚህ በህዋላ 95% የሚሆነው ሙስሊም በራሱ እጣ ፈንታ ሊወስን ይገባዋል በሙስሊሞች ሊተዳደር ይገባዋል። ትናንት ለፓለቲካ አላማ በወጣ ስም እራሱን ሱፍያ ወይም ሰለፍያ የሚለው አካል በፍፁም ህዝበ ሙስሊሙን ሊወክል አይችልም። ሱፍያ ወይም ሰለፍያ የሚለውን  ስም የሚጠቀም ሁሉ የራሱን ጥቅም ለማስከበር የተደራጀ የአነሳ ሊህቃን የጥቅም ስብስብ መሆኑን መንግስትም ሆነ ህዝበ ሙስሊሙ ሊገነዘብ ይገባል። እራሱን ሱፍያ ወይም ሰልፍያ ብሎ መጅሊስ አመራር የሆነ አካል ቦታውን ለሙስሊሞች ሊያስረክብ ይገባል።
እኔ በበኩሌ ሱፍያም ሰለፍያም አይደለሁም። እራሱን ሱፍያ ወይም ሰለፍያ ብሎ የሰየመ አካል ወኪሌ ሊሆን አይችልም። እኔ ሙስሊም ነኝ ድኔም ነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) ያስተማሩት ምንም ቅጥያ የለለው ኢስላም ብቻና ብቻ ነው።
ለመላው ሙስሊም ማህበረሰብ መልካም ዒድ አል ፈጢር ብያለሁ!
Filed in: Amharic