>

ከኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጋር ወደፊት!!! (በተረፈ ወርቁ )

ከኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጋር ወደፊት!

በተረፈ ወርቁ


 

  • እንደ መንደርደሪያ/ምክንያተ-ጽሕፈት

 

ባሳለፍነው ሳምንት አንድ ነጭ ፖሊስ አፍሪካ አሜሪካዊውን ጎልማሳ ጆርጅ ፍሎይድን በጠራራ ጸሐይ አስፋልት ላይ አጋድሞ በጉልበቱና በክርኑ ተጭኖ ለሞት እንዲያበቃ ያደረገበት፣ በዓለም ዙሪያ የተሰራጨው ኢ-ሰብአዊና አሰቃቂ የሆነ ቪዲዮ በአሜሪካና በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ አፍሪካ አሜሪካውያን ‘‘Black Life Matters’’ በሚል በቀድሞ ዘመን የትግል መርሕአቸው ኃይል የተቀላለቀበት የበቀል ርምጃ እየወሰዱ እንዳሉ በመገናኛ ብዙኃን በስፋት እየዘገቡ ነው፡፡

የዛሬ 60 ዓመት አካባቢ የጥቁር ሕዝቦች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ በሕግ ቢታወጅም በአሜሪካ የሚኖሩ ጥቁሮች አሁንም በአገራቸው የዜግነት መብታቸው ሙሉበሙሉ አልተጠበቀላቸውም ማለት ይቻላል፤ መድልዖው አሁንም አላቆመም፡፡ በዚህ የሚቆጩ ጥቁሮች አሁንም ትግላቸውን አላቆሙም፡፡ ሆኖም በቅርብ ጊዜ ዕውቅናን እያገኘ የመጣው “የጥቁርም ሕይወት ይገባዋል” (Black Lives Matter – BLM) እንቅስቃሴ ታሪካዊውን የ60ዎቹን ነውጥ አልባ የሰብአዊ መብቶች ትግል ወደሌላ አቅጣጫ እየወሰደው እንዳሉ የሰሞኑ ክሥተቶች እያሳየን ነው፡፡

በዛሬው አጭር መጣጥፌ- ይህንን ሰሞኑን በአሜሪካ በጆርጅ ፍሎይድ ላይ የተፈጸመውን የዘረኝነት ጥቃት ክሥትት መሠረት አድርጌ- ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና የመብት ጥያቄን በማስተባባር ረገድ ትልቅና አኩሪ የሆነ ታሪካዊ ስፍራ ያለውን የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናን እና እንስቃሴን በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

 

  • ኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ምንድን ነው?

 

ኢትዮጵያኒዝም- እንደ ጽንሰ ሐሳብ ሲተነተን በመላ ዓለም የሚኖሩ አፍሪካዊያን/ጥቁር ሕዝቦች ንቅናቄና ጥምረት መገለጫ ነው፡፡ የጥቁሮች አንድነት የፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ዕድገት መሠረት ነው በሚል እምነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢትዮጵያኒዚም መንፈሳዊ ነፃነት፣ በራስ መተማመን፣ ለራስ ክብር መስጠት፣ ራስን መቻል፣ የዉጭ ጭቆናን መቋቋም፣ ዓለማዊ ሕይወት በመንፈሳዊ ሕይወት ማነጽን፣ የተጨቆኑ ሰዎች በጋራ እንዲተባበሩ፣ የሰብአዊ መረዳዳትና እርስበርስ መተሳሰብን ያጨቀ ሰፊ አስተምሮት ነው፡፡

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና የአፍሪካዊያን/የጥቁር ሕዝቦችን ታሪክ፣ ባህል፣ መንፈሳዊና ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለማጣመር ያለመ በመሆኑ በፀረ ቅኝ አገዛዝ፣ በፀረ ባርነትና በፀረ ዘረኝነት ላይ የተደረጉ ተጋድሎዎችም የዚሁ አስተሳሰብ ፍሬ ተደርገው ይታያሉ፡፡

 

  • የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና በአፍሪካ አሜሪካውያን መብት ትግል ታሪክ

 

ኢትዮጵያኒዝም ከአፍሪካውያን፣ ከአፍሪካ አሜሪካውያንና ከመላው የጥቁር ሕዝቦች የነጻትና የመብት ትግል እንስቃሴ ታሪክ ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት እንዳለው የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ፡፡ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና የተፈጠረው፤ በሃይማኖትና በፖለቲካ የጭቆና ቀንበር ውስጥ ወድቀው፤ እንዴት ነፃነታቸውን ለመቀዳጀት እንደሚችሉ ሲያስቡና ሲያሰላስሉ በነበሩ፤ ከአፍሪካ በባርነት የተጋዙ ጥቁር/አፍሪካ-አሜሪካውያን ነው፡፡

የፍልስፍናው ንድፈ-ሐሳብ፤ መንፈሳዊነትን ከሰው ልጆች ነፃነት ጋር ያጣመረ፣ ያቀናጀና ያስተሳሰረ ነው፡፡ ኢትዮጵያኒዝም የተጀመረው በ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ገደማ አካባቢ ቢሆንም፤ ከ1776 የአሜሪካ የነፃነት ትግልን ተከትሎ እያየለና እየተስፋፋ የመጣ ነው፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን በተለይም ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ዜናው ከተሰማው የዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያኒዝም በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ተጠናክሮ ዘልቆአል፡፡ በመንፈሳዊ ዓለም የተሰማሩ በአሜሪካና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ቄሶችም ፍልስፍናው እንዲስፋፋ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ የነፃነት አፍቃሪዎችም፤ ‘‘አፍሪካ ለአፍሪካውያን ትገባለች!’’ የሚለውን የፓን-አፍሪካን መሪ መፈክር ያስተጋቡት የኢትዮጵያኒዝም የነጻነት መንፈስ በፈጠረባቸው ወኔና ቅንአት ነው፡፡

ይህ ኢትዮጵያኒዚም የፈጠረው የነጻነት መንፈስና መነቃቃትም አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ቀንበር አላቆ ልጆችዋ በነጻነትና በእድገት ጎዳና እንዲገስግሱ የሚያልመውን የፓን-አፍሪካኒዝምን ፍልስፍና ወለደ፡፡ የታሪክ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ የጋናው ፕሬዚዳንት ኩዋሜ ንኩሩማህ ከአፍሪካ መሪዎች መካከል ግንባር ቀደም ፓን አፍሪካኒስት የነበሩ ሲሆን፣ ማርከስ ጋርቬይ፣ ጥቁር አሜሪካዊው ማልኮም ኤክስ፣ እንዲሁም ደግሞ ዊሊያም ኤድዋርድ ቡርግሃርድ ዱ ቦይስ ከአፍሪካ ውጭ የሚኖሩ የንቅናቄው አመንጪዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ አቀንቃኞቹ አንዲት አፍሪካን የመፍጠር ዓላማ ነበራቸው፡፡ በመላው ዓለም በነጮችና በጥቁሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተካከል፣ ፍትሐዊ ያልሆነው የሀብት ክፍፍል እንዲቀርና አፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳዳሪነቷ አድጎ በቂ ተፅዕኖ ለማድረግ የምትችልበት ዕድል እንዲፈጠር ያለመ ዓላማ ነበራቸው፡፡

የኢትዮጵያኒዚምና የፓን-አፍሪካን ቅደመ ተከተልና ትሥሥርን ለአሁኑና ለመጪው ትውልዶች ለማስተላለፍ ሲባልም ዛሬ በአዲስ አበባ፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ የታላቁ ፓን አፍሪካኒስት ዶክትር ኩዋሜ ንክሩማህ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ በንኩርማ ሐውልት ስርም፤ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ተቀርጾ ይገኛል፡፡ ይህ መንፈሳዊ ጥቅስም ለአፍሪካና ለአፍሪካ አሜሪካውያን ኢትዮጵያዊነት- የመንፈሳዊ ነፃነት፣ የራስን ፖለቲካዊናና ኢኮኖሚያዊ ተፈጥሮአዊ አቅምን የሚገልጽ መንፈሳዊ እውነት አድርገው ተጠቅመውበታልም፡፡

በመሠረቱ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ብዙ መሥዋዕትነት ተከፍሎበት የተገነባ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ እ.አ.አ. በ1896 በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ አመራር ኢትዮጵያ በዐድዋ ጦርነት በተስፋፊ ኢጣሊያ ላይ የተቀዳጀችው ድል በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ይማቅቁ ለነበሩ ሕዝቦች በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጥላ ሥር ሆነው የማይቀረውን የነፃነት ብርሃናቸውን ያዩበት ሕያው ተስፋቸው ነበር፡፡

ይህንን ድል ተከትሎም የደቡቡ አፍሪካ ዘረኛ ነጮች በ1906 የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና እንደ አደገኛ የኢትዮጵያ ፕሮፖጋንዳ አድርገው ስለቆጠሩት፣ ሕግ አውጥተውና ፍልስፍናውን አንቋሽሸው ‘ኢትዮጵያኒስቶችን’ ማሰርና አልፎ አልፎም መግደል ጀመሩ፡፡ ቀጥለውም የኢትዮጵያኒዝምን እንቅስቃሴ እንደ አደጋና እንደ ሽብር አሰፋፊ ቆጥረው የወታደር ኃይላቸውን አጠናከሩ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ርምጃቸው፤ በ1906 የዙሉ እንቅስቃሴን ቀጥሎም የባንባታና በኒያሳላንድና በሌሎችም አካባቢዎች የፀረ- አፓርታይድን ተቃውሞን ፈጽሞ ሊገታው አልቻለም፡፡

ኢትዮጵያኒዝም በዓለም መድረክ ያስገኛቸው ለውጦች ብዙ ናቸው፡፡ በደቡብ አፍሪካ፤ የአፍሪካን ናሽናል ኮንግሬስ ያቋቋሙት በኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ጥልቅ እውቀት የገበዩ የደቡብ አፍሪካ ቄሶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ ፕሬዝዳንት ጆን ላንጋቢሌሌ ዱቤ፤ በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናቸውና አቁዋማቸው ታስረው ከተፈቱ በሁዋላ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ ፕሬዝዳንት ሁነዋል፡፡  የስማቸው ቅፅል ስምም፤ ‘‘ግልፅ ኢትዮጵያዊ’’ ማለትም ሁልጊዜ ለአደጋ የተጋለጠ ይባል ነበር፡፡

ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ፤ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ፤ እንደ ናይጀሪያ እና ጋና፤ በፈረንሳይ ስር የነበሩ እንደ ካሜሮን ያሉ ሀገሮች የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና በመጠቀም ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር አገናኝተው ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ኢትዮጵያኒዝም ሁነኛ ስልት አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡

በኬንያ እነ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬኒያታ ሳይቀሩ ‘‘አፍሪካ ለአፍሪካዊያን’’ የሚለውን የፓን አፍሪካ ፅንሰ ሐሳብ ተከትለው እሰከ 1960 ዓ.ም. ድረስ ተጠቅመውበታል፡፡ የራስ ተፈሪያኒዝም ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴም በካሪቢያን ሀገሮች የመነጨውና የተስፋፋውም ከዚሁ ከኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጋር ተያይዞ ነው፡፡

ባጠቃላይ ሲታይ፤ ኢትዮጵያኒዝም በተለያየ መንገድ ቢገለፅምና የተለያዩ ሰዎችና ሀገሮች ቢጠቀሙበትም ዓላማው አፍሪካንና የጥቁር ዘርን ሙሉ በሙሉ ከቅኝ ግዛትና ከዘረኝነት ለማውጣት እንደ ችቦ መብራት ሆኖ እንዳገለገለና ግልጋሎቱን እንደቀጠለ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሐሳቤን የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት የነበሩት ታቦ እምቤኪ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የክብር ዶክትሬት ባበረከተላቸው ጊዜ-  የኢትዮጵያኒዝም መርሕ/ፍልስፍና መሠረት አድርገው ለእኛ ኢትዮጵያና ለአፍሪካውያን ካስተላለፉት ንግግራቸው በአጭሩ በመጥቀስ ላጠቃልል፡፡ 

‘‘… የዛሬው ትውልድ እጅግ በጣም ሊያጤነው የሚገባው ጉዳይ አለ፡፡ ይኼውም በአለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመንም እኛ አፍሪካውያን በአጠቃላይ ጥቁር ሕዝቦች እውነተኛ ነጻነታችንን ዕውን ለማድረግ አሁንም በርካታ እንቅፋቶች አሉብን፡፡ እንደ ቅድመ 21ኛው ክፍለ ዘመን ትግሎች ሁሉ ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመንም አፍሪካን ከዘረኝነትና ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማድረግ፤ ኢትዮጵያኒዝምን (የኢትዮጵኒዝምን ፍልስፍና/እንቅስቃሴ) በግድ መሠረት ማድረግ አለብን፤’’ ሲሉ ነበር የተናገሩት፡፡

 

ከዚህ ከፕ/ት ታቦ እምቤኪ ንግግር የምንረዳው የታሪክ እውነታ ቢኖር፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር፣ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና መሠረትና የማእዘን ራስ ድንጋይ የሆኑትን፤ ቅንነት፣ መተሳሰብ፣ መግባባት፣ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ምሕረትንና፣ መንፈሳዊነት… ወዘተ የመሳሰሉ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ትሩፋት የሆኑ እሴቶቻችንም እንደ ትናንትናው ሁሉ ዛሬም በክብር ከፍ ልናደርጋቸው ይገባናል፡፡ ከጎሳና ከዘር ልዩነትና መናናቅ ነፃ ወጥተን- በኢትዮጵያኒዝም መንፈስ/ፍልስፍና ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩልነት፣ በክብር ያቀፈች የነገይቱን ኢትዮጵያ ለትውልድ ማስተላላፍ ታሪካዊ ኃላፊነትና ግዴታም ጭምር እንዳለብን ይሰማኛል፡፡

 

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና- ፍቅርነ፣ ነፃነትን፣ ቅንነትን፣ በጎነትን፣ ተስፋን፣ መንፈሳዊነትን… ከፍ የሚያደርግ ታላቅ ፍልስፍና እና ሕያው ማንነት ነው፡፡ ከእነዚህ ከፍ ካሉ ሰብአዊና መንፈሳዊ እሴቶች አፈንግጠን፣ ራሳችንን ጠንቅቀን ሳናውቅ፤ በጥራዝ-ነጠቅና በሐሰት በተለወሱ እውቀቶች፣ በጥላቻና ጽንፈኝነት ስሜት በጨለማ የምንዳክር ከሆነ የኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪካ ትውልድ ተስፋ ልንሆን አንችልም፡፡ እንደውም ለዛሬው የአፍሪካ ትውልድ የፍቅርና የዕድገት ፀር ከመሆናችን  ባሻገር፤ ተተኪውንም ትውልድ ለባርነት ዳርገነው የምናልፍና፤ የታሪክ ተወቃሾች ሆነን ነው የምንዘከረው፡፡

ለመውጫ ያህል፤ የጥቁሮች መብት ተጋይ የነበረው፣ አፍሪካ አሜሪካዊው ማርከስ ጋርቬይ፤ the Universal African Anthem በሚለው ‘የአፍሪካ ብሔራዊ መዝሙሩ ግጥም’ ውስጥ- ኢትዮጵያና ኢትዮጵያኒዝም- የጥቁር ሕዝቦች ነጻነት እኩልነትና መብት አብሳሪ የተስፋ ጎሕ መሆኑን መስክሯል፡፡ ከአፍሪካ ብሔራዊ መዝሙር ስንኞች እንሆ በጥቂቱ፤

ኦ! ኢትዮጵያ!

ኦ! ኢትዮጵያ!

የአማልዕክት ምርጫ ሰገነት

የዝናቡ ደመና ሲሰበሰብ በማታ

ሰራዊታችን በአሸናፊነት ሲገባ በዕልልታ

ኦ! ኢትዮጵያ… ተዋጊው ጦሩን እየሰበቀ ሲመጣ

በቀይ ጥቁር አረንጓዴ ባንዴራ ሲመራ

አውቀነዋል ድል የእኛ መሆኑን

የጠላት ኃይል

ብትንትኑ መውጣቱን

ኦ! ኢትዮጵያ…

 

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ይለምልም!

ከኢትዮጵዊነት ጋር ወደፊት!

Email:- nikodimos.wise7@gmail.com

Filed in: Amharic