>
8:28 am - Sunday September 25, 2022

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኑዛዜ እና የሊቀመንበሯ ፈተና! (በግዛው ለገሠ)

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኑዛዜ እና የሊቀመንበሯ ፈተና!

በግዛው ለገሠ

አንዳንዴ አብይ ባያወራ፣ ዝም ብሎ ሥራውን ቢሰራ፣ ችግኝ ቢተክል እና ውሃ ቢያጠጣ፣ ቢገነባ ይሻለዋል ብዬ አስባለሁ። ያመልጠዋል። አንዳንዴ ደግሞ ቀላል የሚባል ማምለጥም አይደለም።
ከወራት በፊት ለኦሮሞ ሕዝብ ስላለው መቆርቆር ተጠረጠርኩኝ ብሎ በቀድሞው ኢሕአዴግ ዘመን ለኦነግ መረጃ ማቀበሉን በአደባባይ መናገሩን እናስታውሳለን። አንድ ዓላማ ይታየውና ሦስት አራት መሠረታዊ ስህተቶችን በእኩለ-ቀን ይፈፅማል። ምናለ ዝም ቢል ብዬ አስባለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብይ ዛሬ ፓርላማ ፊት ቀርቦ ከምርጫ ቦርድ ሊቀ-መንበሯ ከብርቱካን ሚደቅሳ (ቡርቴ) ጋር በምርጫ ጉዳይ ያደረጉትን የስልክ ንግግር እንደወረደ ሲዘረግፈው እንደተለመደው ቅስሜን ሰብሮታል።
ነገሩ እንዲህ ነው፣ ምርጫ ቦርድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ምርጫ ማድረግ እንደማይችል ለፓርላማው ሪፖርት ሊያደርግ መሆኑን (ማደረጉን) አብይ ይሰማል። ከሁለት ወር አካባቢ በፊት መሆኑ ነው። ብግን ብሎ ቡርቴ ጋ ይደውላል።
* * *
እንደምታስታውሱት፣ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው ይራዘም ሲሉ ነበር። ምክንያታቸውም በቂ ዝግጅት ማድረግ አይቻልም፣ ምርጫ ኢንስትሩመንት እንጂ የመጨረሻ ግብ አይደለም፣ ጤነኛ እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ምርጫው ተራዝሞ ሌሎች ቀዳሚ የቤት ሥራዎቻችንን እናጠናቅቅ የሚል ነበር። አብይ ወይም ብልጽግና ፓርቲ ግን “ሞቼ እገኛለሁ!” ይል ነበር። ምርጫው የግድ መደረግ እንዳለበት በአጽኖት ደምድመው እየሰሩ እንደነበርም እናስታውሳለን። በወቅቱ ሁላችንም የመሰለን፣ “እንኳንም ዘንቦብሽ…” ተብሎ እንዳይተረትባቸው፣ ይልቁንም ሁነኛ ሕጋዊ እና ዲሞክራሲያዊ ቅቡልነትን ለማረጋገጥ ከማሰብ (ከመቸኮል)፣ እንዲሁም ለሀገሪቱ ዘላቂ እና ጠቃሚ ሁል-አቀፍ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታን አርቆ ከማለም የመነጨ ነበር።
የዛሬው የአብይ ኑዛዜ ግን ምክንያቱን ሌላ ያደርገዋል።
እናም አብይ ብግን ብሎ ቡርቴ ጋ ይደውላል፣ እንዲህ ይላታል፦ «እናንተ ምርጫውን ማሸነፍ ስለማትችሉ ምርጫው መቆም ያለበት ይመስልሻል?!»
ቡርቴ ተኮሳትራ ትታየኛለች፣ «እናንተ ያልከው ማንን ነው?!»
አብይ ይመልሳል፣ «እናንተ፣ ተቃዋሚዎችን ነዋ!»
አብይ የራሱን ንግግር ለፓርላማው ሲያብራራ፣ እርሷንም ጨፍልቆ ከተቃዋሚዎች ጎራ እንደከተታት ይናገራል።
የስልክ ንግግሩ ቀጥሏል፣ «ስላልፈለግሽ ነው ምርጫው እንዳይደረግ የምታደርጊው። የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ፓርላማው አንቺን አምኖ ያስቀመጠው ገለልተኛ ሆነሽ እንድትሰሪ ነው እንጂ፣ አንቺ የምትደግፊያቸው ኃይሎች አቅም የላቸውም ብለሽ ስታስቢ ምርጫውን እንድታራዝሚ አይደለም!»
አብይ ምን ነካው? ቡርቴን እንዲህ ሊፈርጃት የቻለበት ምክንያት ምንድን ነው? ማንንም ሳያማክር እራሱ ጋብዞ ካመጣት በኋላ፣ ምክንያቱንም ከማንም በተሻለ በገለልተኛነትም፣ በመርህ-ወዳድነትም ሆነ በብቃት የሚስተካከላት እንደሌለ በአደባባይ ሲመሰክርላት እንዳልነበረ፣ አሁን ምን ነክቶት ነው።
ኧረ ሌላም ልጨምር . . . አዲሱ የምርጫ ሕግ በነቡርቴ ተረቅቆ የቀረበ ስለመሆኑና በፓርላማ ስለመፅደቁ እራሱ አብይም፣ እራሷ ቡርቴም በአደባባይ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ብልጽግና የቀድሞ ኢሕአዴግን የፓርላማ መቀመጫ እንደተራ ንብረት ሊወርስ የቻለበትን፣ በተሻረው የምርጫ ሕግ ላይ ያልነበረን አንዲት ንዑስ አንቀጽ አዲሱ አዋጅ አካትቶ እንደመጣ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? ወይም ታስታውሳላችሁ። ሌሎች ምሳሌዎችንም መጥቀስ ቢቻልም፣ ኧረ ለመሆኑ ቡርቴን ከተቃዋሚ ጎራ የሚያስመድባት ምኗ ነው።
* * *
አብይስ እየዋሸን ነው? ወይስ በቡርቴ ላይ የምር ይህ አመለካከት ነበረው?
አብይ በቁጣ ነበር ቡርቴን የሚናገራት። ለፓርላማው እንደገለፀው፣ እንዲህ ያለ የከረረ ንግግር ከቡርቴ ጋር ያደረገው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። «እንደምታውቁት፣ ወ/ሮ ብርቱካን ለእንደዚህ ዓይነት ንግግር ሸብረክ የምትል ሴት አይደለችም።» አለ፣ አብይ ትረካውን ለፓርላማው ሲቀጥል።
ከዚያም ቡርቴ እንዲህ ብላ መመለሷን ነገረን፣ «እኔ ይህን ሥራ እና ኃላፊነት የተቀበልኩት ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ከነበረው የተሻለ ምርጫ፣ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ፣ በማንም መስፈርት የማያሳፍር ምርጫ ለማካሄድ ነው። አንተ ምርጫውን አሁን ማካሄድ አለብኝ፣ በተለመደው መንገድ የጨበራ ምርጫ አደርጋለሁ የምትል ከሆነ፣ ነገ ጠዋት ሪዛይን አደርጋለሁ! ለሥልጣን አይደለም እዚህ ያለሁት!» አለች ቡርቴ – ደምስሯ ተገታትሮ ይታየኛል።
አብይ፣ በተለይ ቡርቴን የቦርዱ ሊቀመንበር ለማድረግ ሲያመጣትና መዓዛን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆና እንድትሾም ሲያደርግ፣ የምር ለእውነተኛ የተቋም ግንባታ የሚያስብና ሀቀኛ ራዕይ ያለው አድርጌ ወስጄው ነበር። እንግዲህ ተመልከቱልኝ፣ ምርጫ ቦርድ ተቋም ነው። የራሱ የቦርድ አባላት አሉት፤ ቡርቴ ሊቀመንበሩ ነች ማለት እንደፈለገች በግል አቋሟ ምክንያት ልትዘውረው ትችላለች ብለን ማስብም የለብንም። ቢያንስ በመርህ ደረጃ የብዙ ሰዎች ስብስብ የሆነውን የምርጫ ቦርድ እንድታቋቁም ዋጋ ወደከፈለችባት ሀገር በክብር የተጋበዘች ሰው ነች። አብይ እርሷ ላይ ይህ ዓይነቱ አመለካከት አለው ቢባል እንኳን፣ ምርጫ ቦርድ የተባለውን ተቋም ወደ ግለሰብነት አውርዶታል።
ይህን ከየትም አላመጣሁትም፤ ከራሱ ኑዛዜ ነው። ያመልጠዋል አላልኳችሁም? በእርሱ ቤት የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት፣ የብርቱካንን ጥንካሬ፣ እና የምርጫውን መራዘም ትክክለኛነት በጉልህ መልኩ “ጀስቲፊኬሽን” ለሕዝብ ለማቅረብ ያደረገው ጥረት ነው። (ፓርላማውን ለማሳመንማ አይደለም ይህን የስልክ ንግግራቸውን የተረከው፤ አንደኛ ፓርላማውም ያው ብልጽግና ነው፣ ሁለተኛ ምርጫውንም ያራዘመው ፓርላማው እራሱ ነው። የሚቀጥለው ይበልጥ ያብራራዋል።)
* * *
አንባቢ ሆይ፣ እስካሁን እያነበብከኝ ከሆነ አንድ ነገር ልብ በልልኝ። አብይ እና ቡርቴ ይህን የከረረ የስልክ ክርክር በሚያደርጉበት ጊዜ በሀገራችን ቢያንስ ከ10 የማያንሱ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ሳይረጋገጥ እንዳልቀረ እገምታለሁ። ወረርሽኙ ዓለማቀፍ እንደሆነና እነ ጣሊያን ዓይነት ሀገሮች በቀን ከሺህ ሰው በላይ እየሞተባቸው እንደሆነም ለአብያችን ግልጽ ነበር። እነ ኦሎምፒክ፣ የዓለም ዋንጫ የመሳሰሉ ትዕይንቶች ሳይቀር ተሰርዘዋል። አብይ ባለፈው አራቱን የሕገመንግሥት ቀውስ መወጫ መፍትሔውች ሲያብራራ እነዚህኑ ክስተቶች (ስረዛዎች) እንደ “ጀስቲፊኬሽን” ሲዘረዝራቸው እንደነበር እናስታውሳለን።
ታዲያ ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ሰዓት ነው አብይ ቡርቴን ምርጫ ካላደረግሽ ተቃዋሚነትሽ ጎልቶ እንጂ ስጋቱ ታይቶሽ አይደለም እያለ የሚከራከራት? ወይስ አብይ አሁንም እየዋሸን ነው?
ለማንኛውም፣ በመጨረሻ አብይን ማን አሳመነው?
* * *
የቡርቴ እና የአብይ የከረረ የስልክ ክርክር ባለመግባባት ተቋጨ፤ ስልኩ ተዘጋ። ሁለቱ የተለዋወጡትን ክርክር «እስካሁን በይፋ ተናግሬው አላውቅም» ይላል አብይ፣ ለፓርላማው። እንደኔ እንደኔ ዛሬም መነገር አልነበረበትም።
ስልኩ ከተዘጋ በኋላ አብይ ስለጉዳዩ የፓርላማውን አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሠ ጫፎን ያነጋግራቸዋል። የምርጫ ቦርድን ሪፖርት አስመልክቶ እርሳቸውም ከቡርቴ ጋር በዝርዝር ከተወያዩበት በኋላ አብይን ገሰፁት። የምሬን ነው፣ “ገሰፁት” ትክክለኛው ቃል ነው።
ታገሠ ጫፎ አብይን እንዲህ አሉት፣ «ተሳስተሃል! ይቅርታ መጠየቅ አለብህ! ምርጫ ቦርድ አልችልም ያለው በምክንያት ነው። ምርጫ በአንድ ቀን፣ በአንድ ጀንበር፣ ከጠዋት እስከ ማታ የሚፈፀም፣ ብዙ አክተርስ ያሉት፣ ማሰልጠንና ማዘጋጀት የሚፈልግ፣ ሎጂስቲክስ ኢሹ ያለበት ስለሆነ ዝም ብለን ዓለም በሙሉ አልችልም እያለ ያለውን ምርጫ እኛ እንችላለን ማለት ተገቢ አይደለም።» አሉት። አብይን ገሰፁት! (በነገራችን ላይ ምርጫ የአንድ ጀንበር ጉዳይ አይደለም!)
ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ የፓርላማው አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ ስለ ወረርሽኙ እና ዓለማቀፍ ሁኔታው የተሻለ መረጃ ነበራቸው። ሌሎች ምርጫ ማድረግ አንችልም እያሉ እንደነበርም ያውቁ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትራችን ግን ገና ከታገሠ ጫፎ መስማታቸው ነው። እናም ሰሙና አመኑ፣ አምነውም ምርጫ ባይካሄድ እንዴት መንግሥት (ሥልጣን) ሊቀጥል ይችላል? ወደሚለው የሕገመንግሥት ቀውስ ምዕራፍ አመሩ።
* * *
እስካሁን ያነበባችሁት ሁሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለፓርላማ በአማርኛ፣ በቀጥታ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ስርጭት የተናገሩት ነው። የቀየርኩት ነገር ከቡርቴ ጋር የነበራቸውን የስልክ ውይይት ሲተርኩ አንዳቸው ሌላኛቸውን “አንቱ” እያሉ መጥራታቸውን ብቻ ነው። እሱም እንዲጣፍጥልኝ ብዬ ነው። የሆነ ቦታ ላይ “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር…” አለች ያሉትንም ቆርጨዋለሁ። እርግጠኛ ነኝ፣ አንተ-አንቺ ነው የሚባባሉት – እርሳቸውም ቢሆኑ “ክብርት ሊቀመንበር…” እንደማይሏት አልጠራጠርም።
እናም ቅስሜን የሰበረው፣ አብይ ቡርቴ ላይ ይህን ዓይነት አመለካከት ሊያሳድር መቻሉ፣ ወይም ለምርጫ የነበረው ጉጉት እውነታውን እስኪጋርደው የደረሰ እንደነበር በዛሬው ኑዛዜው መስማቴ አይደለም። ይልቁንም ወሬ ለማሞቅ ብሎ ግጥም አድርጎ እየዋሸን እንዳይሆን የሚለው ጥርጣሬዬ ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ለምን ብቻዬን ይከንክነኝ ብዬ አጋራኋችሁ። (ለመሆኑ አቶ ታገሠን ሰምቶ ይቅርታ ጠይቋት ይሆን?)
አበቃሁ!
Filed in: Amharic