>

የአብይ ሕልምና የእኔ… ቅዠት...!?! (በፍቃዱ ሞረዳ)

የአብይ ሕልምና የእኔ… ቅዠት…!?!

በፍቃዱ ሞረዳ

    የእነአብይ አህመድ የለዉጥ ነፋስ አቧራ ሲያስነሳ በነበረበት ሰሞን በሀገራችን ሰማይ ሥር በአየር ላይ ሲንሳፈፉ የነበሩ ወርቃማ ሐሳቦችንና መፈክሮችን አንጋጠዉ በማየት በተስፋ ተሞልተዉ ከነበሩት ዜጎች መሀከል አንዱ ነኝ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ወገኞቼ በምርቃና እንደጦዙት ባይሆንም፡፡  ከእነዚያ የሀገሩን አየር ሞልተዉ የነበሩት በጎ ሐሳቦችና መፈክሮች ዉስጥ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዉ ነፋሱ ይዟቸዉ በሮ ከዳመናዉ በላይ አንዳች ዉስጥ የሸጎጣቸዉ ቢሆንም እንኳን፣ በቀጭን የተስፋ ክር ላይ ጅዋጅዌ ከሚጫወቱት ተስፈኞች መሐከል ነኝ፡፡
       በምርጫም ይሁን ያለምርጫ የአብይ መንግሥት አምስትም፣ አሥርም ዓመት አሁን ባለዉ ሁኔታ ሚዛኑን ጠብቆ ሥልጣን ላይ ቢቆይ ግድ ላይሰጠኝ ይችል ይሆናል፡፡ የአብይ መንግሥት በግድም ይሁን በዉድ ሥልጣን ከለቀቀ በኋላ ስለምትኖረዉ ኢትዮጵያ ሳስብ ግን ከአሁኑ ብርድ ይይዘኛል፡፡ ምክንያቱም  በመሬት ላይ ያሉና እንደቀላል የምናያቸዉ፣ ለተለያዩ ጊዜያዊ ጥቅሞቻችንና ፍላጎቶቻችን ስንል የምናለባብሳቸዉ ችግሮች ቀላል ዋጋ ላያስከፍሉ ይችላሉና ነዉ፡፡
      ዛሬ በኦሮሚያ ክልል በአንዱ ወይም በሌላ ምክንያት የዜች ሕይወት በየቀኑ ይቀጠፋል፡፡ ለአንድ መንግሥትም ሆነ መሪ የአንድ ተርታ ዜጋ ሕይወት ዋጋ አላት፡፡ ‹‹ ሀገሬ፣ ወገኔ፣ ታሪኬ፣ ጨርቄ፣ ማቄ…›› ለሚለዉም ዜጋ የአንድ ወገኑ ሕይወት ግድ ሊሰጠዉ በተገባ ነበር፡፡ ‹‹የሀገሩ ባለቤት ነዉ›› ተብሎ የሚታመነዉን ዜጋ ሕመም መታመም ካልተቻለ፣ የልቡን መሻት ማዳመጥ ካልተፈለገ…‹‹ ሀገር፣ወገን…›› ብሎ ነገር ከአደባባይ መፈክር፣ ከጉባኤ ላይ ድስኩርና ከመሸታ ቤት ድንፋታ በላይ ምንም ሌላ ሚዛን አይደፋም፡፡
   ዛሬ ልጅ ከፍቶት ዱር በገባ ልጃቸዉ ዳፋ እናትና አባት በጥይት በሚሞቱባት፣ አንዲት ምስኪን እናት በአራት ልጆቿ ፊት ያለአንዳች በቂ ምክንያት የምትገደልባት፣ ሕፃናት ተማሪዎች ታፍነዉ የገቡበት የማይታወቅባት…የታጠቀ የመንግሥት ኃይል የድሀ ቤት በእሳት እያቃጠለ በደስታ የሚጨፍርባት… ሀገር ናት ያለን፡፡ ሰበቡ ምንም ይሁን ምን፣በማንም ይፈፀም በማን በእነዚህና መሰል በአደባባይ በሚታወቁ ጉዳዮች ላይ በይፋ ስሜቱን ( ደስታም ይሁን ሀዘን) የሚገልፅ በየደረጃዉ ያለ መሪ እያየንና እየሰማን አይደለም፡፡
   ጊዜያዊ ጥቅም ወይም ተስፋ ያስመረቀነዉ የወረት ደጋፊ፣ የካድሬነት እንጀራ ካነቀዉ እርግማን ለፋፊ ( አንዳንዱም የለየለት ወፈፌ ነዉ)  እና በመሀል ሆኖ ወይም በባለሥልጣናቱ እግር ሥር እየተልኮሰኮሰ  ጭራዉን ከሚቆላ ቀጣፊ ( ሥልጣን አነፍናፊ) የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጩኼት በስተቀር አፍጥጦ ካለዉ እዉነት ጋር በአደባባይ የሚጋፈጡ መሪዎች የት አሉ?
     እያንዳንዱን ችግር፣ ‹‹ የጀዋርና የልደቱ ታንትራ ፣ የኦነግና የወያኔ ሴራ፣ የግብፅና የኮሮና ሥራ …ነዉ›› እያሉ  መግለጫ ማዉጣት፣ የፕሮፓጋንዳ ‹‹ ዶክሜንተሪ›› በመሥራት ጥላቻን መንዛት መፍትሔ አይሆንም ሲባል ያለምክንያት አይደለም፡፡ ያኔ ጠዋት የለዉጥ ኃይሎች የነገሩንና የገቡት ቃል ይኼን አይደለምና ነዉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን በሰበብ ዉስጥ የመሸጎጥ ጨዋታን ለዓመታት ለምደነዋልና ነዉ፡፡ ከዚያ ልምዳችን ያገኘነዉ ትርፍ ጥፋት እንጂ ልማት አይደለምና ነዉ፡፡
      እኔና ብዙዎቹ ወዳጆቼ ‹‹ወያኔ›› የሚባል ድርጅት አንወድም፡፡  ከዛሬዎቹ የዶክተር አብይ ደጋፊዎች የአብዛኞቹ እምነትና የድጋፍ ሰበብ  ሰዉዬዉ የወያኔን እብሪት ‹‹ ያስተነፍሳል››፤ ስግብግብነቷን ‹‹ልክ ያገባል›› የሚል ነዉ፡፡ ይህ የእኔም ስሜት ነዉ፡፡ ግን በስሜት ብቻ በመገፋት በሚወሰድ እርምጃ የወያኔን ለዓመታት የተገነባ ተፅዕኖ በአንድ ሌሊት ወይም በአንድ ዓመት መናድ እንደማይቻል መቀበል የግድ ነዉ፡፡
 ወደንም ጠላንም ወያኔ ዛሬም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ትልቅ አደጋ ነዉ፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ የወያኔን ገደብና ነዉር የለሽ ሚና ለመቀነስ የተሄደበት መንገድ ወያኔን ጠቀመዉ እንጂ አልጎዳዉም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በትግራይ ዉስጥ ሊቋረጥ ደርሶ የነበረዉ ትንፋሽዋ እንደገና እንዲያንሰራራ አግዟታል፡፡
 ዛሬ በአማራና በትግራይ ክልል ድንበር ላይ ካሉት የታጠቁ ሚሊሺያዎች አንዱ ወፈፌ ወደአንዱ ወገን ተኩሶ የሌላዉን ሚሊሺያ ነፍስ ቢያጠፋ ዉጤቱ  እንደሶሻል ሚዲያ ሆያሆዬና እንደቢራ ቤት አንቺ እንኮዬ ቀላል አይደለም፡፡ ትዕግስትና ኃላፊነትን ይጠይቃል፡፡
  ጫካ ያለዉ የኦነግ ኃይል እንደየዋህዎች ግምት በአንድ ሰሞን ወታደራዊ ዘመቻ ድባቅ መመታት የሚችል አልሆነም፡፡ ይልቁንስ ዕድሜ ለሥርዓቱ የበታች አካላት ይሁንና በየጊዜዉ ወጣቱን በሰበብ አስባቡ ሆድ እያስባሱና እያስጨነቁ ወደጫካ እንዲሄድ በማድረግ የአማፂዉን ኃይል ይበልጥ እያጠናከሩት መሆኑ ያፈጠጠ ሀቅ ነዉ፡፡ የለዉጡ ኃይል ከአንገቱ በላይ ለመታጠብ ሞከረ እንጂ የተቀረዉ አካሉ ከቀድሞ ጭቅቅቱ ጋር እንዳለ ማሳያ የሚሆኑ አያሌ ሀቆች አሉ፡፡  ተቃዋሚን እንደጠላት፣ እንጀራቸዉን ሊበላባቸዉ እንደመጣባቸዉ አዉሬ አድርገዉ ያያሉ፡፡ ስለዚህም ይወነጅላሉ፤ ያሳስራሉ፤ ያስገድላሉም፡፡ የላይኞቹ ሰዎችም ነገሩን እያወቁ ‹‹ብንናገራቸዉ በርግገዉ ወደተቀናቃኝ ጎራ ይገባሉ›› በሚል ስጋት ከእነችግራቸዉ ያዘላቸዉ፣ መከታ የሆናቸዉ ይመስላል፡፡
    በአጠቃላይ የለዉጡ ሕልም ፍሰት አንድ ቦታ ላይ በእርግጥ ፈሩን ስቷል፡፡ የአብይ መንግሥት ሰሞኑን በፌዴሬሽን ምክር ቤት የታዘዘለትን የዕድሜ ማራዘሚያ እንደብቸኛ መድኃኒት ወስዶ አሁን በያዘዉ መንገድ እንዲቀጥል የሚመክሩትና የሚያበረታቱት ወገኖች ካሉ እነርሱ ጠላጹ እንጂ ወዳጁ አይደሉም፡፡የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስጦታ በታሪካዊነቱ ተቀብሎ በጎን ግን ንግግር የሚጀመርበትን ጉዳይ ቆም ብሎ በጥልቀት ማሰብ ይገባል፡፡
  ባሕላዊና ሃይማኖታዊ፣ እንዲሁም ሥልጡን የቅራኔ መፍቻ ብልሃቶችን ተጠቅሞ እንደገና በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ከወያኔም፣ ከኦነግም ሆነ ከሌላዉ ጋር፡፡ ኃይልን ተጠቅሞ የሕግን ልዕልና ማስከበር የመንግሥት ዓይነተኛ ተግባር ነዉ፡፡ ነገር ግን ፣ኃይል ብቸኛዉ የችግር መፍቻ ቁልፍ አይደለም፡፡ሆኖም አያዉቅም፡፡ በይፋ የሚታዩ ችግሮችና ሥጋቶች አይደበቁ፡፡ በሀገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ‹‹ያገባናል›› የሚሉ ባለድርሻዎች ፣ የስቪክ ተቋማት፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ድርጅቶች የተሳተፉበት የመነጋገሪያ መድረክ በተሎ ይፈጠር  ዘንድ ቅዱስ ቅዠቴ ነዉ፡፡
   አበዳን! የኢትዮጵያን ሥር የሰደደ ዉስብስብ ‹‹ የቡዳ ፖለቲካ›› ከጠመንጃ አፈሙዝና  ከአራዳ ልጅ የብልጠት ጨዋታ ከሚመነጭ መፍትሔ መፍታት አይቻልም፡፡ ምናልባት በተለመደዉ የታሪክ አዙሪት ዉስጥ ለመቆየት እንኳን ዕድል ልናጣ እንችላለን፡፡ አብይ አህመድን አከብረዋለሁ፡፡ ብዙዎቹ የጧት ሕልሞቹ ተስፋን ዘርተዉብኛል፡፡ እነዚያ ሕልሞች በአፈታት ችግር ቅዠት ሆነዉ እንዳቀሩ እሰጋለሁ፡፡ ግን…  አሁንም በቂ ጊዜ አለ፡፡የሁሉም ቅንነት ከተጨመረበት፡፡ቅን እንሁን፡፡
Filed in: Amharic