
ሻለቃ ሃይሌ እንደ ጀምስ ቦንድ

(በእውቀቱ ስዩም)
< በፎቶው ላይ የምትመለከቱት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴን ለሽምግልና መቀለ በሄደበት ባንድ ጎረምሳ ሲፈተሽ ነው፤ እኔ ሃይሌ አይፈተሽ አልልም፤ ግን ፈታሹን እስቲ ሹፉት ! ፖሊስ ከመሆኑ በፊት ልብስ ሰፊ እንደነበረ ያስታውቃል ! የሃይሌን ወገብ በሜትር ለመለካት የፈለገ ነው እሚመስለው ! ርቀትህንም ክብርህም ጠብቅ ሶየ! እንዴዴዴ! ብረት ሲነካ የሚንጫጫ መሳርያ ከዘራህ ጫፍ ላይ አስረህ ካልሆነ እንዲህ እንደ አፍለኛ ፍቅረኛ ተጣብቆ መፈታተሽ አይመከርም ፤ እኔ ፖለቲካ አይመቸኝም፤ የዛሬን ብቻ ታገሱኝ !
ሃይሌ ገብረስላሴ የህወሀት ዋና ዋና ሰዎችን መግደል ከፈለገ ሽጉጥ መታጠቅ ፈንጅ መልበስ አይጠበቅበትም ፤ በጠዋት ተነስቶ አቦይ ስብሃት ጋ መደወል ብቻ ነው ሚጠበቅበት!
“ አቦይ ? ከሽምግልናው በፊት ለምን ሰውነታችንን አናፍታታም?”
“ ደስ ይለኛል! ቱታ ሉልበስ?”
“ ቁምጣ አይሻልዎትም?” ( ኧረ ሃይሌ አሽሙር ይደብራል ! )
ከዚያ ሩጫ ይጀመራል፤ መጀመርያ ሃይሌ እግር ለማፍታት ያክል ካብርሃ ካስል ተነስቶ ትንሽ ሮጥ ሮጥ ይላል ፤ አቦይ ስብሃት በማስካቸው ውስጥ እየተራገሙ ይከተሉታል፤ ከዚያ ይነሽጠውና ይሸመጥጣል፤ አቦይ ደግሞ ከመሀል አገር በመጣ ሰው ከሚበለጡ ቢሞቱ ይመርጣሉ ፤ ሃይሌ እሚለው ስም ራሱ ሃይለስላሴን ስለሚያስታውሳቸው ንዴታቸው ያንረዋል ! ያለ የሌለ ጉልበታቸውን አጠራቅመው የሌለ ሳንባቸውን ገጣጥመው ያሳድዱታል ፤ ሻለቃ ሃይሌ አዲግራት ላይ ደርሶ ዞር ብሎ ሲያይ አቦይ የሉም፤ የሆነ ቡና ቤት ገብቶ ኮካ እየጠጣ ቲቪ ሲመለከት “ የህወሃት ዋና ጭንቅላት የነበሩት የ አቦይ ስብሃት በዛሬው እለት በልብ ድካም ተሰውተዋል !” የሚል ዜና ያያል!
ሃይሌ የወንዶች ወንድ!
ሳቂታው ጀምስ ቦንድ!
ጨዋታ አምሮኝ ነው እንጂ የሽምግልናውን እንደማልቃወም ልቦናችሁ ያውቃል !