>

በግፈኞች የሚዘንቡ የደም ዕንባዎችን ለማስቆም!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

በግፈኞች የሚዘንቡ የደም ዕንባዎችን ለማስቆም!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

* “… ከ100ሚሊዮን ብር በላይ ድንቁና ኳርተር ወስደውብኝ ፍ/ቤት ስመላለስ እራሡ ድንቁ ሰርቃኛለች ብሎ ቃሊቲ አስገባኝ። እዛ ታስሬ ስኖር ካናዳ 12000 ዶላር የማከራየውና ዋና መኖሪያየ ተወረሱብኝ።
አአ 22የነበረኝን ቤትና ቅንጡ መኪናየን አሸጠኝ። ቦሌ ለም ሆቴልና መገናኛ ካንዱ ወዳንዱ እያዞሩ መሬት ሰጥተውኝ መጨረሻ
ላይ ወሠዱብኝ።አብጄ ነበር። አሁን ቢገድለኝ ይግደለኝ ልናገር ብየ ነው። ሁሉም ተቋማት ውስጥ ሰው አለው..ቢጨንቀኝ አባ ገዳወች ጋ
ደብረዘይት ሄድኩ ። እሳቸውም እሱ እኮ መንግስት ነው ያስገድልሻል እረፊ አሉኝ።”
“ህንጻውን ከገዛኝ በኋላ በደረቅ ቸክ ሙሉ ህንጻየን(ስታዲየም የሚገኘውን ሪፍት ቫሊ ህንጻ) አስገድዶ ወሰደብኝ። የትም ብሄድ
ሁሉም ላይ ሰው አለው። …” የህንጻው ባለቤት።
ሰሞኑን የአገዛዙ ሚዲያ ዋልታ ቴሌቪዥን አቶ ድንቁ ደያስ የተባለን ግፈኛ ግፎችና ዝርፊያዎች በተከታታይ በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡ ትናንትና ምሽትም ክፍል ሁለትን አቅርቧል፡፡ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ሌሎች በአቶ ድንቁ ደያስ የተዘረፉ ተበዳዮች ስለቀረቡም ቀጣይ ክፍሎች እንደሚኖሩ የዝግጅቱ አቅራቢ አስታውቋል!!!
እኔ ግን እላለሁ አገዛዙ ለራሱ የፖለቲካና የሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ ሲል ለሕዝብ ያሰበ መስሎ ይሄንን አደረገ እንጅ በወንጀለኛው ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርትበት ባላደረገበት ሁኔታ እና ወንጀለኛው ይሄንን ሁሉ ዝርፊያና ግፍ በዜጎች ላይ እንዲፈጽም ያስቻሉት እንደ የቀድሞዋ የጉምሩክና የገቢዎች ሚንስትር የአሁኗ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አበቤ እና የቀድሞው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ያሉ ባለሥልጣናት ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ባልተደረገበት ሁኔታ አገዛዙ ይሄንን እያደረገ ያለው ለሕግ የበላይነትና ለፍትሕ በማሰብ፣ ለሰለባዎችና ለተበዳይ ዜጎች ሰብአዊና የዜግነት መብት ጥብቅና በመቆም ፈጽሞ ሊሆን አይችልም!!!
በዚህች ሀገር ሲዘረፉ የኖሩት እነኝህ በጣት የሚቆጠሩ ወገኖች ብቻ አይደሉም፡፡ በየስፍራው በርካቶች አሉ ተቆጥረው አያልቁም፡፡ ሀገር በወንበዴዎች መዳፍ ውስጥ እንዳለች እያወቁ “እሠራለን!” ብለው ከውጭ ወደ ሀገራቸው ገብተው ንብረታቸውን ያፈሰሱ ሲዘረፉ ኖረዋል እነ ወ/ሮ አስቴር ቀጸላ ብቻ አይደሉም፡፡ በርካቶች በተፈጸመባቸው ዝርፊያና ግፍ አብደዋል፣ ተገድለዋል፣ ቆሽታቸው አሮ ሞተዋል፣ የደረሱበት ጠፍቷል ወዘተረፈ.!!!
ባሕር ዳር ማን ነበረ ስሙ ተዘነጋኝ ከውጭ መጥቶ ጣና ዳርቻ ላይ ያለ የሌለ ንብረቱን አፍሶ የገነባውን ግዙፍና ዘመናዊ ቅንጡ ሪዞርት አገዛዙ ወርሶ ለአላሙዲን ሰጥቶበት ቢዘል ቢፈርጥ ምንም ማድረግ ሳይችል ቀርቶና መፍትሔ አጥቶ ቆሽቱ አሮ ለሞት የተዳረገውን የወንበዴዎች ሰለባ ወገናችንን መጥቀስ ይቻላል!!!
ስንት አለ ለወሬ ሳይበቃ በደሉን ሕዝብ ሳያውቅለት በሰው ሀገር ደም ተፍቶ አፍርቶ ያመጣውን ሀብት ንብረት በወንበዴው የመከላከያ ሠራዊት ጄኔራሎች፣ በአገዛዙ ባለሥልጣናትና በአገዛዙ አጋር ባለሀብቶች ተዘርፎ ውልቁን የቀረ!!!
ዳያስፖራው ግን ምን እየተሠራ እንዳለና በሀገሪቱ ሕግ እንደሌለ እያየና እየሰማ ዛሬም አገዛዙ ለመዝረፍ “ኑ እና ኢንፈስት አድርጉ!” እያለ እያማለለ ሲጠራቸው እየተክለፈለፉ ይመጣሉ በፊተኞቹ የደረሰባቸው ግፍና ዝርፊያ ደሞ በእነዚህም ላይ ይደርሳል፡፡ ከዚያም የሚያብደው ያብዳል የሚሞተው ይሞታል፡፡ እንደገና ደግሞ የሰማው ሲሔድ ያልሰማው ሲመጣ ሀገር በወንበዴዎች እንደተያዘችና የግፍ አውድማ እንደሆነች ይሄው እዚህ ደርሳለች!!!
ከዚህም በኋላ ሀገር እንዳለው ሰው “ሀገሬ ገብቸ ኢንቨስት በማድረግ ሀገሬንና ወገኔን እጠቅማለሁ!” ብለህ የምታስብ የዋህ ዳያስፖራ ካለህ እነዚህን ወገኖች ዓይተህ ተቀጣ!!!
የገባኸውም የተዘረፈብህን ትተህ የያዝከውን ይዘህ ነፍስህን ለማትረፍ መውጫህን ፈልግ!!! መንግሥት በሌለበት ሀገር ሠርቶ ማደር፣ ወጥቶ መግባት፣ ፍትሕ ጠይቆ በቅጡ መዳኘት ወዘተረፈ. የሚባሉ ነገሮች የሉም!!!
ይሄንንም ያህል ልክ መንግሥት እንዳለበት ሀገር እየኖርን ያለነው በእግዚአብሔር ቸርነትና በሕዝቡ ጨዋነት ነው እንጅ እንደ ወንበዴው አገዛዝማ ቢሆን ሀገሪቱ ገና ድሮ ፈራርሳ ነበር!!!
ይሄ ሕዝብ ለአቅመ ሐሳብ ከደረሰና ከዚህም በኋላ በለከት የለሽ ትዕግሥቱ መቀጠሉ ጭራሽኑ ሀገር ሊያሳጣው እንደሚችል ከተገነዘበ ማድረግ ያለበት ነገር አንድና አንድ ነው!!!
እሱም አንድነት ኖሮት ጉልበት አግኝቶና ተስማምቶ በአገዛዙ ላይ እንዳያምጽ በዘር በሃይማኖት የሚከፋፍሉትን ነገር እርግፍ አድርጎ ጥሎ ሆ! ብሎ በአንድነት በመነሣት ይሄንን ነቀርሳ የወንበዴዎች አገዛዝ ጠራርጎ እንጦርጦስ ማውረድ ብቻ ነው!!! ካልሆነ ሀገርም ሕይዎትም ምንም ነገር አይኖርህም ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ሁሉንም ነገር ታጣለህ!!!
Filed in: Amharic