>
8:05 pm - Wednesday June 7, 2023

የታጋቹ ማስታወሻ  ( በእውቀቱ ስዩም)

የታጋቹ ማስታወሻ 

( በእውቀቱ ስዩም)

ቦዘኔነት ማለት አካልህ ተገቢውን ስራ መስራት አቁሞ አእምሮህ ደግሞ በማያገባው ስራ ሲጠመድ ነው   !  አሁን፤ የሄለን በርሄን የሙዚቃ  ቪድዮ እያየሁ  “ ቪድዮው ውስጥ ያለው ጎረምሳ የተሸከመውን  አሳ አጥምዶት ነው ወይስ ከሸዋ ሱፕር ማርኬት ሸምቶት ?” እያልኩ ማሰብ ነበረብኝ?
እሱ ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው
ስንቱን ጉድ ይችላል ቀሳ የወጣ ሰው!
ስሙኝማ፤ ባለፈው ጎረቤቴ የሆነ ፈረንጅ ፓሪ ደግሶ ወፈ ሰማይ ጎረምሳና ኮረዳ ሰብስቦ  ይቀውጠዋል፤ ቤቴ ውስጥ ሆኘ፤ የመስኮቴን ሽንሽን መጋረጃ ገለጥ አድርጌ አያለሁ  ፤ በልጅነቴ አጎታችን ሊጠይቀን መጥቶ  ዶሮ ወጥ ሲቀርብለት በር ላይ ቆሜ ንፍሮ እየበላሁ  የማየው አይነት አስተያየት !
የደጋሹ ጎረቤቴ ግቢ  በህብረቀለማም ፊኛዎች አጊጧል ፤  በፍልጥ ክምር ላይ  እሳት ይንቀለቀላል  ፤ ተጋባዦች የሆነ ነገር ይጠብሳሉ፤ ይበላሉ፤ ይጠጣሉ፤ ይደንሳሉ፤ አልፎ አልፎ ርችት ሁሉ ይተኩሳሉ፤ ይሄን ሁሉ አዱኛ  እጅ እጅ ከሚለው ኑሮየ ጋር ሳወዳድረው  አልቅስ አልቅስ አለኝ  ::
 ጊዜ አልፈጀሁም፤  ደጋሹን ጎረቤቴን ጠራሁትና ቅወጣውን ባስቸኳይ እንዲያቆም አለበለዝያ ፖሊስ እንደምጠራ ነገርኩት!
በከተማችን  የኮሮና አስቸኩዋይ  ጊዜ አዋጅ መሰረት አንድ ሰው ከአምስት በላይ ሰው የተሳተፈበት ፓሪ ከደገሰ ወንጀል ነው፤እና ይህንን ወንጀል የጠቆመ ሰው ደጋሹ ለጭፈራ የተጠቀመባቸውን  እቃዎች መውረስ ይችላል፤
  ጎረቤቴ ምንም አልመለሰም::አንገቱን ደፍቶ በረጅሙ ተነፈሰ፤ ሌላ ጊዜ ቢሆን  “ ሂድ አንካሳ ዶሮ ሳትቀድምህ አቃጥር ሊለኝ ይችል ነበር”
የጊዮርጊስ  ፍሎይድን  ግድያ ተከትሎ ከተከስተው አመፅ በሁዋላ ግን  ነገሮች ተቀይረዋል፡
 ፖሊሶችማ በጣም ከማፈራቸውና ከመፀፀታቸው የተነሳ ጥቁሮችን ለመካስ እማያደርጉት ነገር የለም ፤ባለፈው አንዱ ፖሊስ ከግሮሰሪ እቃ ይዠ ስንገዛገዝ  አይቶ  ሊፍት ሰጠኝ፤ጭራሽ ጋቢናው ውስጥ አስቀምጦ fuck the police የሚል የድንፋታ ዜማ (ሂፓፕ) ሳይቀር ከፈተልኝ ፤
ቤቴ በር ላይ ስንደርስ ፤የሆነ  ማስታወሻ ስጦታ ነገር ሊሰጠኝ ፈልጎ የመኪናውን ኪስ በረበረ፤  የሚሰጠኝ ነገር ቢያጣ  “ ላንዳንድ ነገር ትሆንሃለች  ያዛት” አለና አንድ  ትርፍ ካቴና ሰጠኝ ::
“ ምን ያረግልኛል? ” አልኩት፡፡
“ፍቅረኛ የለህም?”
“ እኛ አገር ፍቅረኛ በቀለበት እንጂ በካቴና አትታሰርም  “አልኩት ፈርጠም ብየ!
“   በህይወትህ አንዴ እንኳ ካልጋህ ጋር ያሰረችህ ሴት የለችም?” አለ ፈገግ ብሎ፤
ዝም አልኩ፤
“  እስቲ በደንብ ለማስታወስ ሞክር  “ አለኝ፤
አሰብ አደረኩና፤
“  ይገርምሃል ! እናቴ፤  በልጅነቴ በእንቅልፍ ልቤ  እየወደቅሁ ስለማስቸግራት   በአሮጌ መቀነት ካልጋው ጋር  ታስረኝ ነበር” አልኩት::
ወደ ደጋሹ ጎረቤቴ እንመለስ  ፤  ወደ ጉዋደኞቹ ተመልሶ ትንሽ ተመካከረ ፤ ከዚያ ከሁለት ሴቶች ጋር ተመልሶ መጣ ፤የመጀመርያዋ በስሱ  ሞቅ ብሏታል:: እምብርቷን  ይፋ ያወጣ ልብስ ለብሳለኝ  ፤ ምናልባት    እምብርቷ  አካባቢ የነበረውን ጨርቅ ቀደው ማስክ ሰፍተውላታል፤ ሁለተኛይቱ ድንቡሽቡሽ ያለች  ላቲን ቢጤ ናት፤  ሰማያዊ ረጂም ቀሚስ አድርጋለች፤ ስድስት ጫማ ርቄ ሳልሳ ባስደንሳት ብየ ተመኘሁ !
“ I think we should  let him join us .He looks lonely and horny ‘  ስትል ሰማሁዋት ::
“ ፓሪው ውስጥ እንቀላቅለው፤ ብቸኝነት ቀንድ አስበቅሎታል”  ለማለት የፈለገች መሰለኝ
 ደጋሹ ጎረቤታችን ትንሽ አተኩሮብኝ ሲያበቃ “  “ልትቀላቅለን ትችላለህ?” ሲል ጠየቀኝ::
እኔ እምፈልገው ይሄን ነው!
ይሄን ነው
ይሄን ነው! !🕺
ጠብቁኝ ! የክት ማስኬን አድርጌ  መጣሁ ”
Filed in: Amharic