>

ከአራት ኪሎ እስከ ባህርዳር...!!!  (ሀብታሙ አያሌው)

ከአራት ኪሎ እስከ ባህርዳር…!!! 

ሀብታሙ አያሌው

ሌላውን ሁሉ ትርክት ተወው ዋናውን ጥያቄ ብቻ የሰኔ 15ቱን እንብርት ተመልከት።  ጀነራል ተፈራ ማሞ በሚዲያ ቀርቦ ከወራት በፊት ይሄንኑ ቃል በቃል አውርቷል። አሁን በጽሑፍ ያንኑ መልሶ ለመድገም ለምን እንዳስፈለገው በፍፁም ባይገባኝም። ትዝብትና እይታዬን በተመለከተ ግን ጥቂት ለማለት እወዳለሁ ።  ቀደም ሲል በጀነራል አሳምነው ላይ በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ እዛው በአዴፓ ውስጥ “እብድ ነው” እስከማለት የደረሰ ዘመቻ እንደተካሄደበት፤ የፌደራል መንግስቱም የአማራ ልዩ ኃይል መጠናከር ስጋት ሆኖት አሳምነውን ሲያዋክብ እንደነበረ ጀነራል ተፈራ መተንፈስ ያልፈለገበት ምክንያት ፈፅሞ አልገባኝም።
አራት ኪሎ ቤተመንግስት ከተደረገው ግምገማ በኋላ ሰኞ እና ማክሰኞ  ባህርዳር እንዲቀጥል የፀጥታ ኃይሎችም እንዲሳተፉበት ከተባለው ግምገማ ጀርባ ጀነራል አሳምነው ከስልጣን እንዲነሳ የፌደራል መንግስቱም በከሚሴ፣ አጣዬና  በቅማንት ጉዳይ አጣራሁት ባለው ጉዳይ ባዘጋጀው የዘር ማጥፋት ክስ በአቃቤህግ  ብርሃኑ ፀጋዬ ትዕዛዝ ዘብጥያ ሊያወርዱት ተዘጋጅተው እንደነበረ ሊተርክ አልወደደም።
ይህ ብቻ አይደለም ከእንግሊዝ አገር በልዩ ግብዣ ተጠርቶ የኦሮሚያ ልዩ አይል አባላትን የኮማንዶ እና የክልሉን ደህንነት መዋቅር በማደራጀት፤ ኋላም ከሪፐብሊኩ ጋርድ፤ ከደህንነትና ከመከላከያ የተውጣጡ የጃዋር ጠባቂዎችን አሰልጥኖ ተልኮውን በአግባቡ ተወጣ የተባለው ግለሰብ በፌደራል መንግስት ትዕዛዝ ባህርዳር ገብቶ የደህንነት ተቋሙን ሲያደራጅ እንደነበረ፤  በአማራ ክልል አመራሮች መካከል አንዱ ሌላኛውን በአሉባልታ እየገላመጠ አውራጃዊነት ተጠንስሶ እንደነበረ ጀነራል ተፈራ እያወቀ ባላየ ማለፉ  በፍፁም ሊገባኝ አልቻለም።
ከሰኔ 15ቱ በፊት የአዴፓ አመራሮች በአውራጃ ተቧድነው በተለይም በአቶ ደመቀ መኮንን  እና በዶ/ር አምባቸው መካከል ሳይቀር የነበረውን የተካረረ ፀብ ሊያነሳው አልፈለገም።  ከቤተመንግስት ልዩ ጥበቃ በፀብ ተባረረ ተብሎ ወደ ክልሉ መጥቶ የጀነራል አሳምነውን ይሁንታ በማግኘት አሰጣኝ ሆነ ከዚያ ከግድያው በኋላ ተሰወረ ብሎ ነገረን።  ቀጥሎም ከተሰወረበት ድሬዳዋ ተያዘ ከተባለ በኋላ እንደገና በስህተት ነው ተብሎ ደብዛው የመጥፋቱን ጉዳይ ጨረፍ አድርጎ ከማለፍ በቀር ወደ ጉዳዩ መግባት አልፈለገም።
ጀነራል አሳምነው ወደ አባይ ማዶ ሲሻገር ” ነገሩ አብቅቷል ብዬ ሪፖርት አደረኩ”  ከማለት በቀር ኦፕሬሽኑን እንዳለው እሱ ከተቆጣጠረው ጀነራል አሳምነው በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ ሊመረመር ሲገባ መግደል ለምን አማራጭ ተደረገ ? በማን እና እንዴት ተገደለ ? ጀነራል ተፈራ ይህንንም ሊነካካው አልፈለገም።
በወንጀሉ ምንም እጃቸው የለም ያላቸውን በልዩ ኃይሉ ውስጥ በተለይ በአጣዬ፣ ደራ፣ ከሚሴ የኦነግን ወረራ ያከሸፉ የልዩ ኃይሉ አመራሮች ዛሬም ድረስ ታስረው የቆዩበት ምክንያት ለምን እና በማን ትዕዛዝ ነው ?  በመምህርነት ተመድቦ የስለላ ስራ ሲሰራ ነበር የተባለው ግለሰብስ የት ደረሰ ?  ይህ ግለሰብ ፌደራል መንግስቱ ዋና ማስረጃዬ ነው ብሎ ወደ ባህርዳር አምጥቶ እሱ የጠቆማቸውን ሁሉ ለቅሞ ሲያስር የአማራ ክልል አመራር የፌደራል መንግስቱ የመረጃ ምንጭ የተባለው ይህ ሰው በግድያው አቀናባሪነት መረጃ አገኘሁበት ብሎ አስረዋለሁ ሲል ፌደራል መንግስቱ አልሰጥም በሚል የተፈጠረው ግብግብ የት ደረሰ ??
ጀነራል ተፈራ እንደ አንድ ግለሰብ ገብስ ገብሱን ተናገረም ፃፈም ይሄን ሁሉ ውስብስብ ጉዳይ ግን ያልተፈታ ፈፅሞ ሊዳፈን የማይችል ጊዜ የሚጠብቅ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።  ለማንኛውም ወቅቱ በዚህ ንትርክ የሚገባበት ስላልሆነ  እንጂ ከአራት ኪሎ ባህርዳር የነበረው ውስብስብ ሴራ በዚህ የሚቋጭ አይሆንም።
ሌላው ጀነራል ተፈራ ባህርዳር የነበረውን የግድያ ሁኔታ የፌደራል መንግስቱ “መፈንቅለ መንግስት” ብሎ ነግዶበታል በማለት የጠቀሱ ሲሆን  የባህርዳሩን ግድያ ድንገት በስሜት የተካሄደ እንጂ ለመንግስት ግልበጣ የተሰናዳ እንዳልሆነ አብራርተዋል።  በዚሁ አጋጣሚ በአዲስ አበባ ኢታማዦር ሹሙ ለምን በማን ተገደሉ ? ግድያውስ እንዴት ተዳፍኖ ቀረ ?  እንዴት የሚጠይቅም የሚፅፍም  ጠፋ ??  ጊዜ ይፍታው።
ብቻ በምንም ይሆን በምንም ምክንያት የአማራ ክልል ህዝብ ዶ/አምባቸውን  ጀነራል አሳምነውን፣ አቶ ምግባሩን፣ አቶ እዘዝን  … በርካቶችን አጥቷል።  የጉዳት ሁሉ ጉዳት ደርሷል።  በመጓተት ሌላ ጉዳት እንዳይመጣ ማረም እንጂ ተቧድኖ መፈራረጁ የትም አያደርስም።  በመጨረሻም ጀነራል ተፈራ የተናገራት ለሃሳቤ መቋጫ ትሁን።
                            *     *      *
“በመጨረሻም እኔ እንደ ወታደር የሚታየኝን ለማብራራት ሞክሬለሁ። ፖለቲከኞቹ ግን ለውጡ ፈጣሪዎቹን ወደመብላት ስለምን ተሻገረ? የሚለውን ጥያቄ እንዲመልሱልኝ በአደባባይ እጠይቃለሁ” 
—-
ዶ/ር አምባቸው መኮንን ፣ ጀነራል አሳምነው ጽጌ፣ አቶ ምግባሩ ከበደ =  በጋራ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ የቆሙለት ዓላማ ምን ነበር ??  ምላሹን ከአንደበታቸው !!
Filed in: Amharic