>
5:01 pm - Wednesday December 3, 9310

መግደል ሲኖር መገደል አለ...!!!  (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

መግደል ሲኖር መገደል አለ…!!!

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ

  ቃላት ያጥራል፤ እንቅልፍ ይነሳል፤ እጅግ ያሳዝናል፤ ዛሬ ከትላንት የማይማር ትውልድ፤ ትላንት የስንት ንፁሃን ደም በከንቱ ፈሰሰ፤ በማያውቁት ነገር፤ በዘራቸው ብቻ ተመንጥረው፤ ብስለት በጎደለው እንⶽጭ መንጋ ጭዳ ሆኑ። ብዙዎቹ ለግድያ የተሰለፉት ኅፃናት ናቸው፤ በልተው አልጠገቡም፤ የረባ መጫምያ የላቸውም፤ ለምን እንደሚገድሉ፤ ለምን የሰው ንብረት እንድሚያወድሙ በቅጡ አልገባቸውም።
 ለእነሱ የግድያ ደውል በቂው ቃል “ነፍጠኛን አጥፋ” የሚለው ነው። አብዛኞቹ፤ ማንበብ እና መፃፍ አይችሉም። እነሱ፤ ሲገድሉ ግን፤ እንደሚገደሉም ግንዛቤ ውስጥ እንኳን አይከቱም። አዎ ትላንት ከገዳዮቹ መሃል የተገደለ አለ። ዛሬም፤ የኦሮምያ ክልል ፖሊስ የነገረን፤ ከሞተው ከ 50 በላይ ዜጋ፤ ንጹሃንን ለመግደል ንብረት ለማውደም ከወጣውም በርካታ ወጣት አለበት፤ ሊገድል ወጥቶ የተገደለ፤ ሃሳቡን በነፃነት ለመግለጽ ወጥቶ፤ የተገደለ፤ ቤታቸው ተቀምጠው፤ በጉዳዩ ውስጥ ምንም የሌሉበት፤ ኦሮሞ ባለመሆናቸው፤ እንዲሁም አማራ በመሆናቸው ብቻ የተገደሉ ሁሉ በጥቅሉ ሟች ተብለው ተዘግበዋል።
የሚያስዝነው፤ ግን ግደል እያለክ የምታንቧርቀው፤ ከእሳቱ ሸሽተህ ርቀህ ነው። ከትግሉ እሳት፤ ፈርተህ እና ሸሽተህ፤ ሃገርህም የነበርክ ጊዜ በፍርሃት ተሸብበህ እና ተደብቀህ፤ ዛሬ፤ ስደት ላይ ሆነህ የጀገንክ ነህ። በሟች ደም የምትነግድ፤ ሕሊና ቢስ፤ ምቹ ወንበርህ ላይ ተቀምጠህ፤ አሜሪካ፤ ጀርመን፤ አውስትራልያ፤ እንግሊዝ፤ ካናዳ፤ ወዘተ ሆነህ፤ የጥላቻ ከበሮህን የምትደልቅ፤ የሞት ታምቡርህን የምትመታ ፈሪ ነህ። “ጭራህን” እግርህ ውስጥ ቆልፈህ ነው፤ ፈርተህ ከሃገር የወጣኸው፤ ዛሬ ግን የሶሻል ሚድያ ጀግና ነህ፤ ንፁህ ዜጋ ሲገደል ላንተ ድል ነው፤ አንተ የምትቀሰቅሰው፤ ምስኪን የድሃ ልጅ ሲገደል፤ ፎቶውን ለጥፈህ ብር ትሰብሰብበታለህ። አንድ ቀን አስበኸው የማታውቅ፤ ቁርስ በልቶ ምሳውን የማይደግም የድሃ ልጅ ነው የምታስገድለው፤ እንዲገድል የምትገፋፋው አብዛኛው ወጣት ተስፋ የቆረጠ ነው፤ አጠገብህ ሊያናግረህ ቢመጣ፤ የሰከንድ እንኳን ትኩረት አትሰጠውም። እንዲገድልልህ ስትፈልግ፤ ለአንተ እኩይ እርኩስ መንፈስ ማርኪያ ስትፈልግ ግን ታጀግነዋልህ፤ እንዲገድል የውሻ ፊሽካህን ትነፋለታለህ፤ ሲገደል (ሲሞት) ደግሞ ትነግድበታለህ።
 አንተ ልጅህን በምዕራብ ሃገር ሰላማዊ ትምህርት ቤት ትልካለህ፤ አንተም ሚስትህም በሰለጠነ ሃገር በሰላም ትኖራላችሁ፤ ይህን ለፍቶ አዳሪ ሕዝብ፤ በድህነት የሚኖር ሕዝብ ግን ደም ታቃባለህ። የሰው ሃገር በስደት ትኖራለህ፤ አንተ በማትኖርባት ሃገር፤ ምናልባትም፤ በአሁኑ ስዓት ዜጋ ባልሆንክበት ሃገር፤ ከትውልድ ትውልድ ከኖረበት ሃገር “ክልሌ ነው እና ውጣ” ትላለህ። ፈሪ በመሆንህ ግን፤ እቦታው ተገኝተህ አትልም፤ ፈሪ በመሆንህ ቆሜበታለሁ ለምትለው ዓላማ እንኳን ፊት ለፊት አትጋፈጠም። መግደል ብቻ አይደለም ማስገደልም ተሽናፊነት ነው። የሃጫሉ መገደል ያሳዝናል፤ ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ልብ ይሰብራል። ደንቆሮ በመሆንህ፤ ግን የዚሀን የሕዝቦች ድምጽ የነበረን ወጣት አሳንሰህ፤ “የኦሮሞ ብቻ ልታደርገው ትፈልጋለህ”። ቢገባህ፤ ሃጫሉ እንኳን ከኦርሞነት፤ ከኢትዮጵያዊነት በላይ ነው። የጮኸው ለፍትህ ነው፤ ፍትሕ አለም አቀፋዊ ነው። አንተ ጠበህ፤ ይህን ግዙፍ ወጣት አታጥበው፤ አንተ አንሰህ ይህን ግዙፍ ወጣት አታሳንሰው። እድሜ ልክህን በአቤቱታ ትኖራለህ እንጂ፤ አንተ እንደምትመኘው፤ ኢትዮጵያ ታድጋለች እንጂ አትፈርስም።
 በውስጥህ ሰላም የለህም፤ አማራን ስላስገደልክ፤ ውስጥህ ሰላም አያገኝም። ሰላም የማይኖርህ ፈሪ እና ልምጥምጥ ስለሆንክ ነው፤ በሌላው ሞት ጀግና ልትሆን አትችልም። አንተ ትግልን የምታውቀው በፎቶ እና በቪድዮ ነው፤ ስደት ነው የሶሻል ሚድያ ጀግና ያደረግህ። የሚያስዝነው፤ እንዳንተ ዓይነት የአስተሳሰብ ድኩማን ከሰው ተርታ መቆጠሩ ነው። በርግጠኝነት እነግርሃለሁ፤ ግድል ብለህ የላካቸው ወጣቶች መካከል ብዙዎች ይገደላሉ፤ ምስኪን ወላጆቻቸውን ግን ለደቂቃ እንኳን አታስባቸውም። በልጆቻቸው ሬሳ ነግደህ ከምትሰብሰበው የደም ግንዘብ ሳንቲም አትሰጣቸውም። እንዳንተ ዓይነት የተረገሙ ፈጡሮች ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አይገባቸውም። ጤናማው ዜጋ ከወሬ ባሻገር አንተን መሳይ አረመኔ አስገዳዮች፤ ወደ ፍትህ ለማምጣት ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው፤ ሃገራችን ሰላም ልታገኝ የምትችለው።
Filed in: Amharic