‹‹ሕገ-ወጥ ሕጎች እየበዙ ነው፣ ማብቃት አለባቸው!››
‹‹አንዱ በሀገርህ ላይ የመኖርህ መገለጫ ሳትሰጋህ መኖር ነው፤
ሌላ ሀገር ያለ ይመስል አልሰጋም››
ጠበቃ ተማም አባቡልጉ
በኤሊያስ ገብሩ (ጋዜጠኛ)
*****አብርሃ ደስታን በተመለከተ፣ ከጠበቃ ተማም አባቡልጉ ጋር ያደረኩት ቃለ-ምልልስ****
በስፍራው የነበሩ የተለያዩ ሰዎች የፖሊሶችን አካሄድ በመቃወም ‹‹አንወጣም፣ ሕግ- አልጣስንም፡፡ አብርሃ ነጻ ሰው ነው ብለን ስለምናምን ለእሱ ያለንን አክብሮት እና አድናቆት ለመግለጽ እናጨበጭባለን›› በማለት ከፖሊሶች ጋር ክርክር ካደረጉ በኋላ በፖሊሶች በድጋሚ ‹‹ተፈትሻችሁ ግቡ›› በሚል አለመግባባቱ እልባት ለማግኘት ችሏል፡፡
አብርሃም፣ ከችሎት በፈገግታ ታጅቦ ሲወጣ ዝናብ እየዘነበ ነበር፡፡ ሆኖም በስፍራው ከነበሩ ታዳሚዎች ሞቅ ያለ ጭብጨባ እና ድጋፍ ተሰጥቶታል፡፡ እሱም በካቴና የታሰሩ እጆቹን ትንሽ ከፍ በማድረግ ‹‹አመሰግናለሁ›› ብሏል፡፡
እኔም የአብርሃ ደስታ ጠበቃ ለሆኑትን አቶ ተማም አባቡልጉን የተወሱን ጥያቄዎችን በማንሳት ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጌያለሁ፡፡
————————————————
ጥያቄ፡- የዛሬ የአብርሃ ደስታ የፍርድ ቤት ውሎ እንዴት ነበር?
ጠበቃ ተማም፡- የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ለመስከረም 22 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ጥያቄ፡- ለምን ተሰጠ?
ጠበቃ ተማም፡- ፖሊስ ‹‹ተጨማሪ የምስክር ቃል እቀበላለሁ፤ ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ እሰባስባለሁ፤ ሰነድ አስተረጉማለሁ፡፡›› ብሏል፡፡ እነዚህ ነገሮች ባለፈውም ተብለዋል፤ በፊትም ተብለዋል፡፡ እኛ ግን ተቃውመናል፡፡
ጥያቄ፡- በምን ተቃወማችሁ?
ጠበቃ ተማም፡- በሁለት ነገር ተቃውመናል፡፡ ዛሬ የሚባሉ ነገሮች በሙሉ፣ ይሄ ልጅ ከመታሰሩ በፊት መጠናቀቅ ነበረባቸው፡፡ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በአንቀጽ 19 ላይ ‹‹አንድ ሰው ሽብር ለመስራት በቂ ምክንያት / ጥርጣሬ ካለ ..›› ይላል፡፡ ‹ሽብርን ያቋቁማል› የተባለው ጉዳይ በተራ ወንጀልነት በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ላይ አለ፡፡ ስለዚህ ይህ መሆን አለመሆኑን አጣርተው ነው አብርሃ ማሰር የነበረባቸው፡፡ ያን ለማድረግ ደግሞ የምስክር ቃለ ሰምተው፤ የሰነድ መስረጃ ሰብስበው ነው ምክንያታዊ ጥርጣሬ አደረባቸው የሚባለው፡፡ ይሄንን ምክንያት አድርገው፣ ለሁለት ለሶስት ጊዜ የጊዜ ቀጠሮ ማድረጋቸው በራሱ የአሰራር ሕገ-ወጥነትን ያሳያል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ የታሰረው ምንም ማስረጃ ሳይኖር ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው፣ የተጠረጠሩትን ይዘው፣ መረጃዎች በብርበራ የተያዙ መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ሕገ-ወጥ ነው፡፡
ጥያቄ፡- እርስዎ በዚህ ላይ ምን አሉ?
ጠበቃ ተማም፡- ይህ ሕገ-ወጥ አሰራር ነው ብዬ አመለከትኩኝ፡፡ ይሄ የሚያመለክተው፣ ምስክር የሚጠይቁት፣ ‹‹ከእነሱ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ አገኘን›› የሚሏቸው ነገሮች ከእነሱ መጀመሪያ ምንም ነገር ሳያገኙ ነው ያሰሯቸው፡፡ ይሄ ራሱ ሕገ-ወጥ ነው፡፡ ‹‹የመራራ ዛፍ ፍሬ መርዛማ ነው›› ስለዚህ ‹‹ሕገ-ወጥ ሥነ-ሥርዓት በማድረግ የሚመጣ ፍሬ በራሱ ውጤቱ መርዛማ ነው›› አልኩኝ፡፡
ጥያቄ፡- ይሄንን እርስዎ ሲሉ ዳኞች ምን አሉ?
ጠበቃ ተማም፡- ዳኛው ማስጠንቀቂያ ነው የሰጡኝ፡፡ ይሄ የተለመደ የሕግ አባባል ነው፡፡ የሥነ- ሥርዓት ሕጎች መብት ማስጠበቂያ ናቸው፡፡ እነዚህን ጥሰህ የምታገኛቸው ነገሮች በሙሉ ሕገ-ወጥነታቸውን ለማስረዳት ነው የተጠቀምኩት፡፡ ለፍርድ ቤቱም አመልክቻለሁ፡፡ ለምን? አስተሳሰሩ ሕገ-ወጥ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሽብር ተግባር ለመሰማራቸው በቂ ማስረጃ እና ጥርጣሬ ኖሮ አይደለም የታሰሩት፡፡ ያ ሁሉ የተደረገው ከታሰሩ በኋላ በቤታቸው በተደረገ ማስረጃ ነው፡፡ ይሄንን ‹‹ሕገ-ወጥነት ነው›› ስል አመለከትኩኝ፤ ለደንበኛዬም ‹‹ዋስትና ይፈቀድልኝ›› በማለት አመለከትኩኝ፡፡ ዳኛው ይሄንን ተውትና ወደእኔ ዞሩ፡፡ ማስጠንቀቂያም ሠጡኝ፡፡
ጥያቄ፡- ምን ብለው?
ጥያቄ፡- በዛሬው ችሎት አብርሃ ያለው ነገር ነበር?
ጠበቃ ተማም፡- አዎን፡፡ ‹‹ከታሰርኩ ጀምሮ ከጠበቃዬ ጋር የተገናኘሁት አንድ ቀን ብቻ ነው›› በማለት ለችሎቱ አቤቱታ አቅርቦ ነበር፡፡ ዳኛውም ‹ ከአሁን በኋላ እንደዚህ ዓይነት ቅሬታ መስማት አልፈልግም፡፡ ከጠበቃው ጋር አገናኙት፡፡ ካልሆነ እቀጣችኋለሁ›› ብለዋል፡፡
ጥያቄ፡- በዚህ መሠረት አብርሃን መቼ ያገኙታል?
ጠበቃ ተማም፡- ነገ አርብ ነው፤ አገኘኋለሁ፡፡
ጥያቄ፡- አንድ ቀን ሲያገኙት ስሜቱ እንዴት ነበር?
ጠበቃ ተማም፡- ባለፈው ለችሎት ያመለከተውን ነበር የነገረኝ፡፡ መጎሸሙን፣ መሰደቡን፣ ሰብዓዊ መብቱ መጣሱንና አስፈራተውት መፈረሙን ነግሮኝ ነበር፡፡
ጥያቄ፡- የፍርድ ቤቱ ዳኛ እርስዎን የሚያሥጠነቅቁ ነገሮች ተናግረዋል፡፡ ተገቢ ነው? እርስዎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ተሰማዎት?
ጠበቃ ተማም፡- እኔ ስለምንም ነገር አልሰጋም፡፡ ለምን እሰጋለሁ? በሰፈሬ እና በሀገሬ ነው ያለሁት፤ ምንም አልፈራም፣ አልሰጋም፡፡ ምንም ስላላደረኩኝ ልፈራ አይገባም፡፡ እንደዛ የሚያስቡ ሰዎች ናቸው በፍራት ያለባቸው፡፡ ሕገ-ወጥ ሥራ የሚሰሩ ሰዎች ናቸው መፍራት ያለባቸው፡፡ አንተን የሚያስፈራሩ ሰዎች መፍራት አለባቸው፡፡ ለምን? በእንደዚህ አይነት ጉዳይ መፍራት ለራሴ ውርደት ይመስለኛል፡፡ ማንም ጉልበተኛ ነኝ ባይ ሁሉ፣ እንደቦዘኔ ሊያስፈራራኝ በፈለገ ቁጥር ከፈራሁና ከሰጋሁ ውርደት ነው – በዚህ ዕድሜዬ! የሆነ ሀገር ሄደህ ቢሆን እኮ፣ ‹‹ከሀገራቸው ያባርሩኛል፤ እንዲህ ያደርጉኛል›› ልል እችላለሁ፡፡ በሀገሬ ግን ለምን እሰጋለሁ፡፡ በመጀመሪያ፣ ምንም ነገር አይመጣም፡፡ ሁለተኛ፣ ነውር ነው፡፡ አንተ በሀገርህ እያለህ ማንም ሊያሠጋህ አይገባም፡፡ ምክንያቱም፣ አንዱ በሀገርህ ላይ የመኖርህ መገለጫ ሳትሰጋህ መኖር ነው፡፡ ሌላ ሀገር ያለ ይመስል አልሰጋም፡፡
ጥያቄ፡- ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅለል ባለ መልኩ ማለት የምትፈልገው ነገር?
ጠበቃ ተማም፡- ለአንድ ሀገር እና ሕዝብ አብሮነት ማኅበራዊ መስተጋሩ ተጠባብቆ መኖሩ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ ሕግ መከበር አለበት፡፡ ሶስተኛ፣ ሕገ-ወጥ ሕጎች እየበዙ ነው፣ ማብቃት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ተከባብረን፣ ተረዳድተንና ተዋውቀን መኖር አለብን፡፡ ሁሉም ሰው አንዱ የአንዱን መብት እየጠበቀ መኖር አለበት፡፡