ሕውሃትን በተመለከተ ለመንግስት የማቀርበው ጥያቄ፤ የወንጀል ተጠርጣሪ ወይስ የፖለቲካ ባላንጣ?
ያሬድ ሃይለማሪያም
የመንግስት ባለሥልጣናት ሰሞኑን ስለተፈጸመው ግድያ እና እልቂት አስመልክቶ በየቀኑ በሚሰጧቸው መግለጫዎች ሁሉ ተጠያቂዎች አድርገው ከሚገልጿቸው አካላት መካከል አንዱ እና ዋነኛው ወያኔ እና ባለሥልጣናቶቹ ናቸው። በአጫሉ ግድያም ሆነ ከዛ በኋላ በተከሰቱት ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች ወያኔ እጇ እንዳለበት ተገልጿል። ለመንግስት የማቀርበው ጥያቄ ታዲያ ህውሃት እና ባለሥልጣናቶቹ እንዲህ አይነት አገርን የማተራመስ እና የሽብር ተግባር ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳላቸው በመረጃዎች ከተረጋገጠ እነዚህ ግለሰቦች በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ምን እየተሰራ እንደሆነ አብራችው ብትገልጹልን ጥሩ ነው?
• እንደ ድርጅት ህውሃት በዚህ አይነት የሽብር ተግባር ላይ እስከተሰማራ ድረስ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ድርጅቱን ሕጋዊ እውቅና መንፈግ እና እቀባ መጣል አይገባም ወይ?
• አመራሮቹ እና አባላቱ በተጠቀሱት ወንጀሎች ላይ ባላቸው የወንጀል ተሳትፎ ልክ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ በስም ተዘርዝረው ተጠቅሰው፤ ልክ የቀድሞው የደህንነት ሹም ላይ እንደተደረገው የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣት አይገባም ወይ? አንድ ጌታቸውን መያዝ ከባድ ለሆነበት መንግስት ደባቂዎቹንም አብሮ መክሰስ የት ያደርሰዋል ቢባልም ሁሉንም በሌሉበትም ቢሆን ክስ መስርቶ በፍርድ ቤት ጥፋተኝነታቸውን ማረጋገጡ መንግስት ክልሉን ለመቆጣጠር ለሚያደርገው ጥረት (ካለ) አያግዝም ወይ?
• በመላ አገሪቱ ያሉ እና ህውሃት በባለቤትነት በሚያንቀሳቅሳቸው ንብረቶች፤ እንዲሁም የድርጅቱ ባለሥልጣናት እና አመራሮች የሚያንቀሳቅሷቸው ንብረቶች እና የባንክ ሂሳቦቸቸውም ላይ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እገዳ መጣል አይቻልም ወይ?
•ከህውሃት ጋር ቀጥተኛ የጥቅም ግንኙነት ያላቸው እና ድርጅቱ አገርን ለማፈራረስ፣ የንጹሃን ዜጎችን ደም ለማፍሰስ እና ሕዝቡን ለማሸበር በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ የተግባር ተሳትፎ እና ድጋፍ በሚሰጡ ተቋማትን እና ግለሰቦችንስ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?
እነዚህን ጥያቄ ለማንሳት ያስገደደኝ እስካሁን መንግስት በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ደጋግሞ ሲናገር ሕውሃትን እና አመራሮችን ግን በመግለጫ ከማውገዝ እና ከመዝለፍ ባለፈ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ማሰቡንም ሆነ ምን እየሰራ እንደሆነ ግልጽ የሆነ ነገር ስላልሰማው ነው። ህውሃትን ልክ እንደ ግብጽ ወይም አልሻባብ የመሰሉ የውጭ መንግስታት እና ቡድኖች እንዲሁ በመግለጫ እያወገዙ መቀጠል የት ያደርሳል? ህውሃትን በሕግ የማንበርከኩ ሥራ እንዲህ ቀላል ባይሆንም ትግራይን ያቀፈች ኢትዮጵያን ማስቀጠል ከተፈለገ ሂደቱን ከላይ በተጠቀሱት እርምጃዎች ከወዲሁ መጀመር ይገባል።
መንግስት በሁሉም የአገሪቱ ግዛት የሕግ የበላይነትን የማስፈን ፍላጎት እና አቅም ያለው መሆኑንም ማሳየት ይኖርበታል። ስለ ህውሃት ሲወራ ልክ እንደ አንድ በክፉ የሚነሳና እራሱን የቻለ ሉዓላዊ ጎረቤት አገር አስመስሎ ማቅረቡ ትግራይን ለሕውሃት ሙሉ በሙሉ የመተው አዝማሚያ ይመስላል። በአንድ ወንጀል ተሳትፎ ያላቸውን አካላት ሁሉ አብሮ ማቅረቡ ከፍትሕ እና ሕግን ከማስከበርም ባለፈም ትልቅ የፖለቲካ ፋይዳ አለው።