>
5:18 pm - Friday June 14, 9715

"ዘውጌኝነት" እና "ዘውግ-ዘለልነት"…? (በፍቃዱ ሀይሉ)

“ዘውጌኝነት” እና “ዘውግ-ዘለልነት”…?

በፍቃዱ ሀይሉ

 

ለብዙዎቹ ችግሮቻችን ፍቱን መድኃኒት አድርጌ የምወስደው፣ ጉዳዩን በዘመን ቁመት እና በዓለም ሕዝቦች ታሪክ አግድም መመልከት ነው። ዓለም በበቂ ሁኔታ የምንማርባቸው ስኬቶች እና ውድቀቶች አሏት። ዘውጌኝነት፣ ብሔርተኝነት እና ዜግነት የመሳሰሉትም የብቻችን ጉዳዮች አይደሉም። ዓለም በየፈርጁ የዳከረችበት እና እየዳከረችበት ያለ ችግር ነው። ስለዚህ ጥያቄውን በቅጡ ለማበጃጀትም ይሁን፣ አዋጭ መልስ ለመፈለግ ከሰው ልጆች እንደአንድ የሚያደርገንን ታሪክ የምናውቀውን ያክል ማሰስ ያስፈልጋል። ይህን ከጠቆምኩ በኋላ ወደ የበኩሌን ለመሞከር ወደ አጀንዳዬ እዘልቃለሁ።
የዘውግ ብሔርተኝነት ምንድን ነው?
የዘውግ ብሔርተኝነት (ethnonationalism) የአንድ ዘውግ (ethnic) ቡድን ነጻ አገር እንዲመሠርት ወይም ከመገንጠል ወዲህ ያለውን የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ለማስቻል የሚደረግ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ነው።
የዘውግ ማንነት በኢትዮጵያ ልማዳዊ አሠራር በወላጆች ማንነት ነው የሚወሰነው። እናትና አባታቸው ከተለያዩ ዘውጎች የተወለዱ ዜጎች በተለምዶ የአባታቸውን የዘውግ ሐረግ ነው የሚወርሱት። ዜጎች በአንድ ክልል ተወልደው፣ የአካባቢውን ቋንቋ፣ ባሕልና ወግ አውቀው ቢያድጉም ከአካባቢው ዘውግ የተለየ ዘውግ ካላቸው ወላጆች ከተወለዱ የአካባቢው ዘውግ አላቸው አይባልም። ማለትም፣ ለምሳሌ በኦሮሚያ ከአማራ ልጆች ተወልደው ያደጉ ልጆች በዘውግ ብሔርተኞች እንደኦሮሞ አይቆጠሩም። በሕግ የመምረጥ እና መመረጥ መብት ቢኖራቸውም በልማድ ተቀባይነት የማግኘት ዕድላቸው ግን አነስተኛ ነው። ነገሩን ይብስ ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ በሌሎች ማኅበረሰቦች መሐል የሚያድጉ ልጆች ከአደጉበት ማኅበረሰብ ይልቅ ዘውጋቸውን ከወላጆቻቸው በደም ለመውረስ የመፈለጋቸው ልምድ ነው፡፡
የዘውግ ብሔርተኝነት ንቅናቄዎች ከዘር (race) ንቅናቄዎች ጋር በትይዩ ሊታዩ ይችላሉ። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ያሉ ዘውጎች በፊት ቅርፅና የቆዳ ቀለም ሊገለጽ የሚችል ልዩነት ባይኖራቸውም (የዘር ልዩነት ባይኖርም)፣ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ግን ተቀራራቢነት አላቸው። ሁለቱም “በማንነታችን ምክንያት የመብት እና ዕድል አድልዎ ይደረግብናል” ይላሉ። የሚገጥሟቸውም ተግዳሮቶችም ተቀራራቢነት አላቸው፤ ለምሳሌ ያክል ‘Black Lives Matter’ (የጥቁር ነፍስም ዋጋ አለው) በሚለው የጥቁሮች ንቅናቄ ላይ ‘All Lives Matter’ (የሁሉም ሰው ነፍስ ዋጋ አለው) ነው መባል ያለበት እንደሚሉት ሁሉ፣ በኛም አገር ለምሳሌ ‘Because I am Oromo’ (ኦሮሞ ስለሆንኩ) እንዲህ ደረሰብኝ በሚለው ፈንታ ‘Because I am Ethiopian’ (ኢትዮጵያዊ በመሆኔ) ነው መባል ያለበት የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።
አሁን ‘ኢትዮጵያዊነት’ ምንድን ነው?
‘ኢትዮጵያዊነት’ (‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት›) የሚባለው አሁን የወል፣ አስማሚ ትርጉም የለውም። ሆኖም ‘ብሔር’ የሚለው የግዕዝ ቃል ‘አገር’ የሚል ትርጉም አለው በሚል “ብሔሬ ኢትዮጵያ ነው” በማለት የዘውግ ማንነታቸው በኢትዮጵያዊነት መግለጽ የሚፈልጉ አሉ። በዚያ ላይ ቤተሰቦቻቸው ከሁለት ዘውግ የተወለዱ ሰዎች ራሳቸውን በኢትዮጵያዊነት ለመግለጽ መፈለጋቸው ኢትዮጵያዊነትን እንደ አቃፊ ወይም ደግሞ አማራጭ ማንነት መቀበላቸውን ያሳያል።
ይሁን እንጂ ከነዚህ ውጪ ኢትዮጵያዊነትን እንደዜግነት ሳይሆን ራሱን እንደቻለ ማንነት የሚመለከቱት በተለይ አዲስ አበቤዎች፣ በርካታ የአማራ እና በደቡብ ክልል የሚገኙ ብሔረሰቦች በተለይም ጉራጌዎች ናቸው። ከነዚህ ውጪ ያሉት ቀዳሚ ምርጫቸው አለመሆኑ የሚያሳየው ‘ኢትዮጵያዊነት’ን እንደማንነት የማይቆጥሩት ዜጎች መኖራቸውን ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከሉላዊነት (globalization) ባሕርያት ጋር የሚመሳሰልባቸውም ነገሮች አሉ። ሉላዊነት በኃያላን አገራት በተለይም በአሜሪካ የኢኮኖሚ መሪነት የተመሠረተ የዓለም አገራት ትስስር ነው። ኢትዮጵያዊነትም ከሰሜን ኢትዮጵያ በአቢሲኒያ ተመሥርቶ ወደደቡብ እና ምሥራቅ የተስፋፋ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ነው። ሉላዊነት ኃያላኑ አገራት የኢኮኖሚ እና ቴክኖሎጂ የበላይነታቸውን ተጠቅመው የራሳቸውን ማንነት በአቅመ ደካሞቹ አገራት ላይ የሚጭኑበት (hegemonic) ግንኙነት ነው ይላሉ፤ ብዙዎች ሉላዊነትን ከአሜሪካዊነት ጋር ዕኩል ያደርጉታል። በተመሳሳይ፣ ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያውያንም ኢትዮጵያዊነትን ከአቢሲኒያዊነት ጋር ዕኩል ያደርጉታል። አቢሲኒያውያን የአገር መሥራችነት እና ቀዳሚ የመሣሪያ ማግኘት ዕድላቸውን ተጠቅመው የሰሜኑ ሕዝብ ከሌላው የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት ዘርግተዋል በማለት።
የዘውግ ብሔርተኝነት እና የአሁኑ ‘ኢትዮጵያዊነት’ – አንድነት እና ልዩነት
ሁለቱም ፖለቲካዊ ንቅናቄዎች ናቸው። ዘውገኝነት በቋንቋ፣ ባሕል እና ወግ መመሳሰል (አንድ ዓይነትነት /homogeneity/ አላልኩም) ወይም የማይመስሉትን በማግለል ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊነት ግን የወደዱትንም የጠሉትንም በጠቅላይነት ላይ የተመሠረተ ነው። የዘውግ ብሔርተኞች ለዘውግ ጥቅም የግዛት አንድነትን አሳልፈው ሊሰጡ ይችላሉ፤ የኢትዮጵያዊነት አራማጆች ደግሞ የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ የዘውጎች ቡድን ጥቅም አሳልፈው ሊሰጡ ይችላሉ።
በተቀባይነት ደረጃ የዘውግ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት ዕኩል ወዳጅም፣ ጠላትም አለው። ነገር ግን በተለይ ብዙኃን ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት ገጠር አካባቢ ዜጎች ራሳቸውን በወንዛቸው ወይም በዘውጋቸው መጥራት ይመርጣሉ። የዘውግ ብሔርተኝነትን አምርረው የሚቃወሙት የኢትዮጵያዊነት አራማጆችም ለዘውግ መወገንን የሚጠየፉት ምንጩ ከአቢሲኒያ ያልሆነ ወግ አጥባቂነት ሲመለከቱ ነው በሚል ይተቻሉ። በሌላ አነጋገር ‹ኢትዮጵያዊነት› የሚመርጠው (ወይም የሚጠየፈው) እና የማይመርጠው (ወይም የማይጠየፈው) ዓይነት የዘውግ ወገንተኝነት አለ ማለት ይቻላል።
እርግጥ ነው፣ የዘውግ ብሔርተኞች እና የኢትዮጵያዊነት አራማጆች የሚያመሳስላቸው አንድ ትልቅ ቋንቋ አለ፤ ይኸውም “ዘውጌኛነት” ራሱ ነው። ምንም እንኳን ‘ኢትዮጵያዊነት’ን ብቻ የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ልሒቃን ኅብረብሔራዊነትን ነው የምንሰብከው ቢሉም ኢትዮጵያውያንን እንደዘውግ ስብስብ እንጂ ከዘውግ ፍልስፍና አፈንግጠው በተለየ ርዕዮተ ዓለም እንደ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አይመለከቷቸውም። (ወይም በአንዳርጋቸው ፅጌ አጠራራር “ዘውግ ዘለል” አተያይ የላቸውም፡፡) ለዚህም ይመስላል ሁሉንም የዘውግ ቡድኖች ማሸነፍ የሚችል “ከዘውጌኛነት” የተሻገረ ስኬታማ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ያልተቻለው። የገዢው ፓርቲ ግንባር በኅብረብሔራዊ ፓርቲነት በአዲስ አበባ ሲንቀሳቀስ፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ግን የብሔር ፓርቲ ሆኖ ነው የሚንቀሳቀሰው። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ የዘውጎቹ፣ በየአካባቢያቸው ተቀባይነት ሲያገኙ፤ ኅብረብሔራዊ ነን የሚሉት አብዛኛው ተቀባይነታቸው በከተማ እንዲሁም በአማራ እና በደቡብ ክልል ነው። ስለዚህ ሁሉንም የሚያስማማ ብሔራዊ ንቅናቄ ከዬት ይምጣ?
ረዥሙ አብዮት”
ንዑስ ርዕሱን የተዋስኩት “The Long Revolution” ከሚለው የእንግሊዛዊው ሬይመንድ ዊሊያምስ መጽሐፍ ነው። ሐሳቡ ዓለማችን ረዥም እና የማያቋርጥ የለውጥ ጉዞ ላይ መሆኗን የሚተርክ ነው። ኢትዮጵያም የዚሁ የሰው ልጅ ከድቅድቅ ድንቁርና ወደ ዕውቀት ብርሀን የሚያደርገው ጉዞ ውስጥ የራሷ ድርሻ አላት። ጥንታዊ ሥልጣኔዎቻችን እና ዕድሜ ጠገብ ትውፊቶቻችን የዚህ ረዥም ጉዞ አካል ናቸው። ይሁን እንጂ ፈጥነን፣ ከአሸናፊው የዓለም ክፍል ዕኩል መራመድ ባለመቻላችን እና ራሳችንን ባለማጣጣማችን ምክንያት ኋላ ቀር ሆነናል። በተለይም በዕድሜ ከኛ ዕኩል እና የዘገየ ሥልጣኔ ባለቤት የሆኑ አገራት ነገሥታቱ የሕዝቦቻቸውን ነጻነት ባከበሩበት ፍጥነት የኛዎቹ ባለማክበራቸው ምክንያት (እንግሊዝ በ1215 ነው ለመጀመሪያ ግዜ የንጉሦቿን ሥልጣን የሚገድበውን ‘ማግና ካርታ’ ያወጀችው።) እና አድሎአዊ አሠራሮችን በግዜ ባለመቅረፋቸው አገራችን የሚያፈቅሯት ብቻ ሳይሆን የሚጠሏትንም ዜጎቿን አቅፋ እንድትኖር አስገድዷታል።
የረዥሙ የሰው ዘር የነጻነት ጉዞ ዓላማ ደግሞ ዜጎች አገራቸውን እየጠሏትም ቢሆን መብትና ነጻነታቸውን እንድታከብርላቸው እና እንድታስከብርላቸው ማድረግ ነው። ይህ የሚሆንበት ሁለት ምክንያት አለ። አንደኛው፣ አገረ-መንግሥታት የተፈጠሩት በሕዝብና መንግሥት ውል ነው። የውሉ ሐተታ ደግሞ መንግሥታት የዜጎችን መብት፣ ነጻነትና ደኅንነት ይጠብቃሉ፤ በምላሹ ከዜጎች ምንዳ ይሰፈርላቸዋል። ይህ ውለታ የማይሻር ነው። ሁለተኛው ምክንያት፣ አገራት ለዜጎቻቸው ነጻነት ይኖራሉ እንጂ፣ ዜጎች ለአገሮቻቸው ሕልውና ነጻነታቸውን አይገብሩም። ነጻነት የሰው ዘር የመጨረሻ ግብ ነው።
የዓለምም ይሁን የአገራችን ታሪክ የሚያረጋግጥልን ፍጥነቱ ከቦታ ቦታ ይለያይ እንጂ የሰው ልጅ ወደነጻነቱ የሚያደርገው ጉዞ ስኬታማ ነው። በዓለማችን መንግሥታት በዜጎቻቸው ላይ የሚያደርሱት ጭቆና፣ በጦርነት የሚያልቁ ሕዝቦች ቁጥር፣ በማንነት የመገለል መጠን ከመቶ ዓመታት በፊት ካለው ዛሬ በጣም የተሻለ ነው። ይህ ተስፋ ሰጪ የሰው ልጅ የነጻነት ጉዞ ድል እያስመዘገበ እዚህ የደረሰው እያንዳንዱ (የዘውግም ይሁን ዘውግ ዘለል) ትግል ውጤት ስላመጣ ነው። አሁን በኢትዮጵያ የሚደረገው ትግል፣ ውጤቱ የሚወሰነው የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ለዜጎቿ ነጻነትን ለማቀናጀት ባላት ፈቃደኛነት ልክ ነው። ይህችን ለዜጎቿ ነጻነት የተመቸች አገር የፈጠርን እንደሁ የታሪክ ባለቤቶቹ (እና ተመስጋኞቹ) በኅብረብሔራዊነት የግዛት አንድነቷን ያስጠበቁት ብቻ ሳይሆኑ፣ አድሎና ማግለሏን የተቃወሙት እና ስርዓተ ፍልስፍናዋን የሚያስቀይሯትም ዘውገኞች ጭምርናቸው፡፡
የነገ ‘ኢትዮጵያዊነት’ ምን ዓይነት ይሁን?
ቀደም ብለን በተመለከትናቸው የዘውጌኝነት እና የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ንቅናቄዎች ውስጥ ያልተስተዋለው፣ ሁለቱም በተለያየ መንገድ የሰው ልጅ ረዥም የነጻነት ተልዕኮ አካል መሆናቸው ነው። ስለዚህ፣ በገለልተኛ ዓይኖች፣ እንደተቀናቃኝ ሳይሆን ተመጋጋቢ ወይም ሚዛን ጠባቂ ንቅናቄዎች መቆጠር ይኖርባቸው ነበር። እርግጥ ነው ሁለቱም ብሔርተኝነቶች “ዘውግ ዘለል” ባለመሆናቸው አንዳቸው ሌላኛቸውን ዒላማ በማድረግ ብቻ ነው ለማበብ የሚሞክሩት፡፡ ይህ ተመጋጋቢ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ የንቅናቄዎቹ መሪ ልኂቃን አንዱን የሌላኛው ጠላት በማድረግ የደጋፊና ተከታዮቻቸውን ቁጥር በመነጣጠቅ ስልተ አካሔድ በቁጥር ለመበርከት ይሞክራሉ።
በደጋግ ቃላት አሽሞንሙነን፣ ሁላችንም የምንስማማበት ‘ኢትዮጵያዊነት’ የምንለውን የምር መፍጠር ካስፈለገን ግን የእስከዛሬውን የሁለቱንም ወገን ዘውጌኛ ፍልስፍናችንን መከለስ ይኖርብናል። ‘ኢትዮጵያዊነት’ እንደስከዛሬው በዘውግ/ብሔር ማንነት ሳይሆን በዜግነት ብሔርተኝነት (civic nationalism) መቃኘት አለበት።
‘የዜግነት ብሔርተኝነት’ የምንለው የሚፈጠረው የፓስፖርት ዜግነታችን ለወጉ ያክል ‘ኢትዮጵያዊ’ ስለሚል ብቻ አይደለም። የዜግነት ብሔርተኝነት በዘር/ማንነት ላይ የተመሠረተ ማግለል የሌለበት ስርዓተ ማኅበር ነው። “የብሔርተኝነቱ የመርሕ ዋልታዎችም ነጻነት፣ መቻቻል፣ ዕኩልነት እና ግለሰባዊ ነጻነት ናቸው።”
“‘የዜግነት ብሔርተኝነት’ በቋንቋ፣ ወይም በባሕል አይገለጽም። ይልቁንም በፖለቲካዊ ተቋማቱ እና ዜጎች በተስማሙበት እንዲሁም ተቋማቱ በቆሙበት መርሖዎች ነው የሚገለጸው። የዚህ ብሔርተኝነት አራማጆች እሴታቸውን ለመጋራት በራቸው ለሁሉም ክፍት ነው።” (Anna Stilz, 2009)
ይህ ዓይነቱ ብሔርተኝነት እንዴት ሊመጣ ይችላል?
የዜግነት ብሔርተኝነት ባሕርያት፦
☞ ዜጎቹን የሚያስማማ ሕገ መንግሥትና ሕግጋት እንዲሁም የሕግ የበላይነት ያለው፣
☞ ማንኛውም ሰው (የየትኛውም ዘውግ ተወላጅ) ሕግጋቱን በመቀበሉ ብቻ የስርዓተ ማኅበሩ አባል የመሆን ዕድል የሚሰጠው፣
☞ መንግሥቱ ብዝኃነትን በሚያስተናግድ መልኩ የተዋቀረ፣
☞ የስርዓተ ማኅበሩ አስኳል ግለሰቡ የሆነ ነው።
ይህን መሰል ስርዓተ ማኅበር ለመገንባት መንግሥትን መቀየር ብቻ ሳይሆን ዜጎችንም ማዘጋጀት፣ ማብቃት ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ በቤተ ዘመዳዊነት ስሜት በገዢ መደቦች በተፈፀሙ ታሪካዊ በደሎች እና መድሎዎች የተፈጠሩ ቁርሾዎችን እና ታሪካዊ አረዳዶችን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የሚከተሉት ላይ መሥራት ይገባል፦
1ኛ) ትምህርት
የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ መሐይምነት ነው – የግለሰብ እንዲሁም የማኅበረሰብ መሐይምነት፡፡ በተግባር የተደገፈ፣ ዓለምን በማወቅ ላይ የተመሠረተ ስርዓተ ትምህርት ዓይናችንን ይገልጥልናል። ነግር ግን ትምህርት በመደበኛው መሥመር ብቻ ሳይሆን በሲቪል ማኅበረሰቦች የማንቃት (awareness) ሥራ ወደ ማኅበረሰቦች የሚሰርፅ ነገር መሆኑም የማይታበል ሐቅ ነው። ከሲቪል ማኅበረሰቦች ጎን ለጎን መገናኛ ብዙኃንም የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ናቸው። መገናኛ ብዙኃን ዓላማቸው ለሕዝብ መረጃ መስጠት፣ ማስተማር እና ማዝናናት ነው።
ስለሆነም ዜጎችን በዜግነት ብሔርተኝነት ለማነጽ መደበኛ ትምህርት ቤቶች፣ ሲቪል ማኅበረሰቦች እና መገናኛ ብዙኃን በነጻነት እንዲያብቡ ማድረግ ያስፈልጋል።
2ኛ) ዴሞክራሲ
ዴሞክራሲን ከሌሎች ስርዓቶች ሁሉ የተሻለ የሚያደርገው “ሕዝባዊ ተሳትፎን” መፍቀዱ ነው። በተለይ በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ በሥሙ ዜጎች እንደሚጭበረብሩበት ሳይሆን፣ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ሕዝቦች በምርጫ ብቻ ሳይሆን በምርጫዎች መካከል የሚሳተፉበት ዕድል ይሰጣቸዋል። በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሕግጋት እንዲወጡ፣ መንግሥት ከተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች በወጡ ተወካዮች እንዲመሠረት፣ የብዙኃን አመራር፣ የድሀጣን መብት እንዲከበር፣ ወዘተ… ዋስትና ይሰጣል። ስለሆነም፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ለሲቪክ ብሔርተኝነት ግንባታ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
3ኛ) ብልፅግና
የዓለማችንንም ይሁን የአገራችንን ነጻነትና ኅብረት በማፅናት በኩል የሀብት ማፍራት እና በፍትሐዊነት የማከፋፈል ጉዳይ እምብዛም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚገባውን ትኩረት የተሰጠው አይመስለኝም፡፡ የጉራጌ ማኅበረሰብን መመልከት ለዚህ ጉዳይ ጠቃሚ ነው። ጉራጌዎች በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች በመሰራጨት ሀብት ያፈራሉ፣ ለዚህም ይመስላል ብዙ የጉራጌ ተወላጆች ራሳቸውን በዘውግ ከመግለጽ በተጨማሪ ከነባሩ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ጋር ብዙም ሲጋጩ የማይታዩት፡፡ ‹የዜግነት ብሔርተኝነት› ግለሰቡን የስርዓቱ ማዕከል ያደርጋል እንዳልነውም፣ ጉራጌዎች በሌሎች የዘውግ ስብስቦች መሐል ግለሰባዊነት በአኗኗር ዘዬአቸው ይከተላሉ፡፡ ይህ ግን ባሕላዊ እሴቶቻቸውን አላዳከመባቸውም። እንዲያውም ከቁጥራቸው ማነስ በተቃራኒ ባሕላዊ እሴቶቻቸው (ለምሳሌ ምግባቸው እና ጭፈራቸው) የኢትዮጵያ ታዋቂ እሴቶች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል። ይህ ስኬት በዘውግ ቡድኖች መካከል ግጭት ሳይፈጥሩ የዜግነት ብሔርተኝነትን እንዴት ማምጣት እንደሚቻል ያሳያል።
የነጻ ገበያ እና የሀብት ማፍራት ነጻነቶች ለዜጎች በተረጋገጡ ቁጥር የአገራችን ሕልውና እየፀና እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ያለው የዘውግ አጥር በፈቃደኝነት እየተሰበረ እና በጋራ ተጠቃሚነት ስሜት መስተጋብራቸው – ቀደም ብለን በጠቃቀስናቸው ሕጋዊነት፣ መቻቻል፣ ዕኩልነት እና ግለሰባዊ ነጻነት – የተመሠረተ እና ጠንካራ (ጤናማ) ይሆናል።
Filed in: Amharic