>
5:13 pm - Sunday April 19, 0820

ከህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ!!!


ከህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ!!!

ድምጺ ወያኔ

 

* በአገርና ህዝብ ላይ ለደረሰውና ለሚደርሰው ጥፋት ብቸኛው ተጠያቂ 
የአራት ኪሎው አምባገነን ኣሃዳዊ ቡድን ነው!
 
የአገራችን ህዝቦች በዘመናት ትግላቸው ያስመዘገቧቸው ፖለቲካዊ፣ አኮኖሚያዊና ማህበራዊ ድሎች አራት ኪሎ በተሰባሰበው አሃዳዊ ሃይል ተነጥቀዋል፡፡ አምባገነናዊው አሃዳዊ ቡድን የጀመረውን ሃገርን የማፈራረስና ህዝቦችን የማጋጨት የፖለቲካ ድራማ አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡
መላ የአገራችን ህዝቦች ለይስሙላ ሰላም፣ ፍቅር እና ዕርቅን አየሰበከ ወደ ስልጣን ኮርቻ የተፈናጠጠው ሃይል ከነርሱ ህልምና ፍላጎት ውጪ በመሄድ ላይ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ ጥገኛው ቡድን ከውስጥና ከውጭ ባገኘው ድጋፍ እየታገዘ ስልጣኑን ለማደላደልና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓቱን በማፍረስ በምትኩ አሃዳዊ ስርዓት ለመትከል በሚወስዳቸው እርምጃዎች ገና ከጠዋቱ ከህዝቦች ጋር መጋጨት እና ግፍ መፈፀም ሲጀምር ህዝቡም የሰጠውን ያልተቆጠበ ድጋፍ በመንሳት ተቃውሞውን ማሰማት ቀጥሏል፡፡ አሃዳዊው ቡድን ለዚህ ተቃውሞ የሰጠው ግፍና ጭካኔ የተመላበት ምላሽ ህዝቡን ይበልጥ ወደ ተቃውሞ እየገፋው ከመሄዱ ባሻገር በቅርቡ በተካሄደው የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አረመኔያዊ ግድያ ቁጣው ወደ ላቀ ደረጃ በመድረስ ጥገኛውን ሃይል ገለል በልልን በማለት ላይ ይገኛል፡፡
የትግራይ ህዝብ በድርጅቱ ህወሓት መሪነት ገና ከጠዋቱ አሃዳዊው የአራት ኪሎ ቡድን የሚወስዳቸውን ህገወጥና ፀረ ህገመንግስት እርምጃዎች በመቃወም አደባባይ በመውጣት ድምፁን አሰምቷል፡፡ ለህገ መንግስታዊ ፌዴራላዊ ስርዓቱ መከበር በፅናት በመቆሙ ቀድሞውንም የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ሲነዛበትና ከወገኖቹ ጋር ለማዳማት ሲሴርበት የቆየውን የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ጥገኛው ሃይል ከውጪ ሃይሎች ጋር ሳይቀር በመተባበር የተለያዩ ሴራዎችን ቢጎነጉንም አያንዳንዷን ሸር በትዕግስትና በትክከለኛ መስመር ላይ በፅናት በመቆም ሲበጣጥስና ደህንነቱንና ህልውናውን ሲከላከል ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት አሃዳዊዉ ሃይል ምርጫን በህገወጥ መንገድ አስተላልፎ  ላልተወሰነ ጊዜ ስልጣን ላይ ለመቆየት በህዝቦች ላይ ግፍና በደል በመፈፀም ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት የትግራይ ህዝብም ሆነ የመላ የአገራችን ህዝቦች ትግል ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ “ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንዲሉ ቀደም ሲል በምዕራብ ኦሮሚያና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በኋላም የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ የተነሳውን ተቃውሞ ለማፈን ኢንተርኔትና ስልክ ያቋረጠው እንዲሁም ኦ ኤም ኤን የተሰኘውን የግል ቴሌቪዥን የዘጋው ቡድን በማናለብኝነት  የህዝቦች ድምፅ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩትን የትግራይ ህዝብ ልሳኖች – ድምፂ ወያነ ትግራይ፣ የትግራይ ቴሌቪዥንና ቻናል 29ን – በመዝጋት ለትግራይ ህዝብና መንግስት ያለውን ንቀትና ጥላቻ በድጋሚ አረጋግጧል፡፡ ግልገል አምባገነኖች ከታሪክ ለመማር ፍላጎት የላቸውም እንጂ እንኳንና ዛሬ በፋሽሽታዊው ደርግ ዘመንም እንደ ድምፂ ወያነ ትግራይ ያሉ የህዝብ ልሳኖችን ለማፈን የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም፡፡ ይልቁንም እነዚያ የህዝብ ልሳኖች በአሃዳውያን መቃብር ላይ የህዝቦችን ድል ማብሰራቸው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡
የዚህ አሃዳዊ ቡድን ቁንጮ አገሪቱን ከቀውስ ወደ ቀውስ እያሸጋገረ በህዳሴ ግድብ ላይ በድርድር ስም የፈፀመውን ክህደት ለመደበቅና ያለ ገደብ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርገው ጥረት ከመላ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተለይም ከኦሮሞ ህዝብ ያጋጠመውን ተቃውሞ ለማክሰም የትግሉን ፈርጦች ማጥፋትና መሪዎቹንም እስር ቤት ማጎር ዕለታዊ ተግባሩ ሆናል፡፡ በማጭበርበርና በጌቶቹ ድጋፍ የሰላም የኖቤል ሽልማት ባገኘ ማግስት አጠናክሮ የቀጠለበት አምባገነናዊነት ገደቡን አልፎ መላ የአገራችን መንደሮችና አበይት የዓለማችን ከተሞች አደባባዮች በተቃውሞ ሰልፎች መጨናነቅ ጀምረዋል፡፡ በአምባገነናዊው ቡድን ፀረ ህዝብ ተግባራት ምክንያት የሰላማዊና ህጋዊ ትግል መድረኮችና በሮች ተዘግተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ህዝቦችና ፖለቲካዊ ምህዳሩ ሰፍቷል ብለው ወደ አገርቤት የገቡ ፖለቲካዊ ሃይሎች መብታቸውን ለማስከበር ሌሎች አማራጮችን እንዲያማትሩ እየተገፉ ይገኛሉ፡፡ ጥገኛው ሃይል ኮሮናን መከላከል ቀድሞውንም አጀንዳው እንዳልነበረ የታወቀ ነው፡፡ ኮረናን ለመከላከል ምርጫን አሸጋግሬአለሁ የሚለው ይህ ቡድን ህዝቦች በቁጣ አደባባይ ወጥተው ይበልጥ ለቫይረሱ እንዲጋለጡ ከማድረጉም በላይ ወረርሽኙን ለመከላከል ለህዝብ ወቅታዊ መረጃ በማድረስ ተግባር ላይ ሲረባረቡ የነበሩ ሚድያዎችን ሳያመነታ ዘግቷቸዋል፡፡ በየወቅቱ በሚፈጥራቸው ቀውሶች ሳቢያ የንፁሃን ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸውና ንብረታቸው በአሳዛኝ ሁኔታ እንዲወድም አድርጓል፡፡ በተቀነባበረው አገርና ስርዓት የማፍረስ ሴራ ምክንያት ለሚደርሰው ጥፋት ብቸኛው ተጠያቂ የስልጣን ጥሙን ለማርካት ሲል በህዝብ ላይ ውንብድና የፈፀመው አምባገነኑ አሃዳዊ ቡድን ነው፡፡
የተከበርከው የትግራይ ህዝብ!
በደምህ ያረጋገጥከውን ብሄራዊ ክብርህን ላለማስደፈርና ህልውናህን አደጋ ላይ ለመጣል ያሰፈሰፉ አሃዳዊ ሃይሎችን ለመመከት በሁሉም መስክ ተደራጅተህ እየተንቀሳቀሰክ ትገኛለህ፡፡ በገፉህ ቁጥር ከመውደቅ ይልቅ ይበልጥ እየጎለበትክና እየጠነከርክ በመሄድ በፍፁም እንደማትንበረከክና ለአምባገነናዊ ስርዓት እንደማታጎበድድ፤ ይልቁንም ጠላቶችህን እንደየአመጣጣቸው እያሳፈርክ የሰማዕታትን አደራ ከግብ እንደምታደርስ፤ ለዚህ የተከበረ ዓላማ መሳካት ከሚዋደቁ ህዝቦች ጋር ክንድህን አስተባብረህ እንደምትታገል በይፋ አውጀሃል፡፡
በህገመንግስቱ ድንጋጌ መሰረት ክልላዊ ምርጫህን አሳታፊ፣ ግልፅ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በወቅቱ በማካሄድ የራስህን እድል ራስህ ለመወሰን ያለህን መብት ለማስከበርና በክልል ደረጃ ያንተን ተቀባይነት ያገኘ መንግስት ለመመስረት ያለህን ቁርጠኝነት በተግባር በማረጋገጥ ላይ ትገኛለህ፡፡ በክልል ደረጃ ድህነትን ለመቅበርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥረትህን አጠናክረሃል፡፡ የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና ስራ አጥነትን ለመቀነስ እየተረባረብክ ከዚሁ ጎን ለጎን ሰላምና ፀጥታህን ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ጠላቶች ለመጠበቅ ያለ እረፍት በመስራት ላይ ትገኛለህ፡፡ በድርጅትህ፣ በመንግስትህና በባለሙያዎች የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን በማክበር ራስህን ከኮሮና ወረርሽኝ ለመጠበቅ ውጤታማ የመመከት ገድል ፈፅመሃል፡፡ ከወንድም የኤርትራ ህዝብ ጋር ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፤ ግንኙነቶች የሁለቱን ህዝቦች የጋራ ጥቅም ወደሚያረጋግጡበት ደረጃ እንዲደርሱና ግልፅ እንዲሆኑ በመርህ ላይ ቆመህ አበርትተህ ታግለሃል፤ ውጤትም አስመዝግበሃል፡፡ በትግልህ ያስመዘገብካቸውን መብቶች ላለማስነጠቅ ብቻ ሳይሆን  አምባገነናዊና አሃዳዊ ሃይሎች በማንኛውም መስክ የሚሸርቡትን ሴራ ለመመከትና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓቱን ከጥፋት ለመታደግ ከመሰል ሃይሎች ጎን ተሰልፈህ በቁርጠኝነት ለመታገል ዝግጁነትህን ይበልጥ አጠናክር፡፡ ጥገናው ሃይል ማንኛውንም የጥፋት እንቅስቃሴ ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል በተግባር አረጋግጧልና ለወሳኝ ፍልሚያ በከፍተኛ በተጠንቀቅ እንድትቆም ድርጅትህ ህወሓት ጥሪውን ያቀርብልሃል፡፡ በሚሰነዘርብህ ጥቃት እንድትከፋና ሌላ አማራጭ እንድታማትር ከየትኛውም አቅጣጫ የሚገፉህን ሃይሎች በፅናት በመታገል ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ሆነህ የጀመርከውን የህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ግንባታ ከጥፋት ለመታደግ አሁንም በፅናት ታገል!
የተከበራችሁ የአገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች!
ለዘመናት ባደረገነው ትግልና መስተጋብር የመሰረትናት ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊት አገራችን በመበታተን ቋፍ ላይ ትገኛለች፡፡ በለውጥ ስም ስልጣን ላይ የወጣው አሃዳዊ ቡድን ስልጣኑን ለማራዘም በማሰብ እርስበርሳችን እንድንባላ ለማድረግ በተንኮል ተነስቷል፡፡ የሰላምና የእድገት ተምሳሌት መሆን የጀመረችው አገራችን ሰላሟን ተነጥቃ ወደ ውድቀት እያመራች ትገኛለች፡፡ አምባገነኑ አሃዳዊ ቡድን በሚፈፅማቸው ግፎችና የማደናገር እንቅስቃሴዎች ሳትዘናጉ ትግላችሁን በማጎልበት ማንነታችሁንና ህልውናችሁን ለማስከበር በሁሉም የአገራችን ማእዘናት ለምታደርጉት ፍትሃዊ ተጋድሎና ለምትከፍሉት መስዋዕትነት የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት ያላቸውን ክብር ይገልፃሉ፡፡ ዛሬም  እንደወትሮው ሁሉ ለዲሞክራሲ፣ ለፍትህና ለብሄራዊ መብታችሁና ክብራችሁ በተለያዩ መንገዶች በምታደርጉት ፀረ አሃዳውያን ተጋድሎ ሁሉ ከጎናችሁ በፅናት እንደምንቆም በድጋሚ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡ ይህንን አስከፊ ዘመን እንደተለመደው በጋራ ትግላችን ተሻግረን ለድል እንደምንበቃ ጥርጥር የለንም፡፡
የተከበራችሁ በውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን!
 አገራችን አሃዳውያን ሃይሎች በለውጥ ስም በፈጠሩት ፀረ ህገመንግስት እንቅስቃሴ በቀውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ትናንት የናንተን ድጋፍ ለማግኘት በተዋቡ ቃላት የሸነገላችሁና አገሪቱን እኔ አሻግራታለሁ በማለት ቃል የገባላችሁ ሃይል ቃሉን በልቶ ዞሮ መግቢያ አገራችሁን በመበታተን አፋፍ ላይ አድርሳታል፡፡ መላ የአገራችን ህዝቦች ይህንን ግፈኛ ቡድን በመቃወም ትግላቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ፡፡ የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በተለያዩ የውጪ ሃገራት አበይት ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ታሪካዊ ወቅት አገራችሁን ከጥፋት ለመታደግ ፀረ አሃዳውያን ድምፃችሁን በጋራ ማሰማት ይጠበቅባችኋል፡፡ ህወሓትና መላው የትግራይ ህዝብ በትግል አጋርነት ከጎናችሁ እንደሚቆሙ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡
የተከበርከው የአለማቀፉ ማህበረሰብ!
 አገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ አስከፊ ቀውስ እየገባች ትገኛለች፡፡ አገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ አሻግራታለሁ በማለት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ የቆየውና ዓለምን አደናግሮ የኖቤል ሽልማት የተቀበለው መሪ ስልጣኑን ለማደላደል ሲል የተቃውሞ ሃሳብ ያላቸውን ሁሉ ማሳደድ፣ መግደልና ማሰር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ በፈፀማቸው አሰቃቂ ግፎች በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ተቃውሞ የደረሰበት ይህ አሃዳዊ ሃይል በኮሮና አሳቦ ምርጫን ላልተወሰነ ጊዜ በማራዘም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ደንታ ቢስነቱን አረጋግጧል፡፡ ሰሞኑን የተፈጠረውን ቀውስ ተንተርሶ የኢንተርኔትና ስልክ መስመሮችን በመዝጋትና የዜጎችን ድምፅ የሚያስተጋቡና ህዝቡ ከኮሮና ራሱን እንዲጠብቅ በየሰዓቱ መረጃ የሚያደርሱትን ሚድያዎች  በማፈን ወደ ፍፁም አምባገነንነት ተሸጋግሯል፡፡ በዚህ ከቀጠለ አገሪቱ ወደ ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ እንደምትገባ የታመነ ነው፡፡ በመሆኑም የከፋ ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉበት ፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈለግ ዘንድ የበኩላችሁን ተፅዕኖ እንድታደርጉ ዛሬም በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
               ዘላለማዊ ክብር ለጀግኖች ሰማዕታት!
                     የህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
                          ሓምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም.
                                                                   መቐለ
Filed in: Amharic