>
5:15 pm - Tuesday May 11, 7993

«ዴሞክራሲ ከህዝብ ሰላምና ከአገር አንድነት በላይ አይደለም!!!» - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

 

«ዴሞክራሲ ከህዝብ ሰላምና ከአገር አንድነት በላይ አይደለም!!!»

– ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
(ኢ ፕ ድ)
በጌትነት ምህረቴ
ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፣የመናገርና መረጃ የማግኘት ነጻነት ከህዝብ ሰላምና ከአገር አንድነት በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሪ ገለጹ።ፓርቲው በሀገር አንድነትና በህዝብ ሰላም ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ድርድር መኖር እንደሌለበት አስታወቀ።
ኢዜማ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት በራስ ሆቴል በሰጠው መግለጫ የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፤ የማህበረሰብ ሰላምና አገር ከሌለ ስለ ዴሞክራሲ ልናወራ አንችልም።የህዝብ በሰላም የመኖርና የአገር አንድነት ጉዳይ የበላይነት ሊይዝ እንደሚችል ሚዲያው ተገንዝቦ መስራት ይኖርበታል።
አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ማህበረሰብን እርስ በርስ የሚያጋጭና የህዝብን ሰላም ችግር ውስጥ የሚከት ዘገባና ቅስቀሳ ሲሰሩ መንግሥት ዝም ብሎ ማየት አለበት ብለን አናምንም ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ማህበረሰብን ከማህበረሰብ ጋር ሊያጋጩ የሚችሉ ነገሮች ሲፈጸሙ ሁሌም ቢሆን መንግሥት ጣልቃ ይገባል ብለዋል ። የመንግሥት ትልቁ ኃላፊነት የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ እንደሆነ አመልክተዋል።
ህዝብን እርስ በርስህ ተጋደል ብሎ መቀስቀስ ከዴሞክራሲ ስርዓት ባህልና መንፈስ ጋር አብሮ የሚሄድ አለመሆኑን ገልጸው ፤ የሚዲያ ተልእኮም አይደለም፤ ዴሞክራሲ በሰፈነባቸውም ሀገራት እንዲህ አይነቱ ተግባር የሚታሰብ አይደለም ብለዋል።ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ቅስቀሳ ሲፈጸም ዝም ብሎ የሚመለከት የዴሞክራሲ ስርዓት በዓለም ላይም እንደ ሌለም አስታውቀዋል ።
የመናገር፣ የመጻፍና የመሰብሰብ መብቶች በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደ ትልቅ እሴት የሚታዩ መሆናቸውን ያመለከቱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ እነዚህ እሴቶች ከሰው ልጅ መኖር፣ ሰላምና ከአገር አንድነት ጋር ውድድር ቢቀርቡ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በፍጹም የበላይነት ሊይዙ አይችሉም ሲሉ አረጋግጠዋል።
ኢዜማ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በእለቱ ባወጣው መግለጫ፤ ያለ ሀገርና ሰላም ፖለቲካም ሆነ ዴሞክራሲ ትርጉም የላቸውም ብሏል ።በሀገር አንድነትና በማኅበረሰባችን ሰላም ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ድርድር መኖር እንደሌለበትም አመልክቷል።
ለዘላቂው የሀገር አንድነት እና ሰላም ከዴሞ ክራሲያዊ ፖለቲካ መኖር፤ ከፍትህ መኖር፤ ከዜጎች እኩልነት መከበር…ወዘተ ጋር በጥብቅ የተቆራኙ መሆናቸውን እናምናለን ያለው ፓርቲው፤ ሁሉም የሀገራችን ዜጎች ይህን ፈታኝ ጊዜ በትእግስት፣ በማስተዋልና በጥንቃቄ እንዲሻገሩት ጥሪ አቅርቧል። የሀገራችንን አንድነት እና ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሁላችንም ያለብንን ኃላፊነትና ድርሻ የመወጣት ግዴታ አለብንም ሲሉ ገልጸዋል።
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ምክንያት ሁላችንም ኀዘን እና የልብ ስብራት ውስጥ እንዳለን ግድያውን ተከትሎ የደረሠው የበርካታ ዜጎቻችን ሞትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ኀዘናችንን እጅግ መራር አድርጎታል ብሏል።
የአርቲስቱ ግድያ እና እሱን ተከትሎ በብዙ ዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት እጅግ አሳሳቢ፣ አሳፋሪ እንዲሁም በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሊወገዝ የሚገባውና በሀገራችን በምንም ዓይነት ሊደገም የማይገባው ድርጊት እንደሆነም አስታውቋል።
በተለይም በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ሕዝብን በማስተባበር አደጋ ከመድረሱ ቀድሞ የማክሸፍ ሥራ በመሥራት፤ አንዴ ከተፈጠረ ደግሞ በፍጹም ቁርጠኝነት ሀገርን እና ሰላማዊ ሕዝብን ከጥቃት መከላከል የፀጥታ አካላት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ተግባር እንደሆነ ጠቁሟል።
በአንድ ወቅት አርቲስት ሃጫሉ “ኢትዮጵያችን በብዙ የማንነት ቀለማት ኅብር የተዋበች ሀገር ናት”። ሲል መናገሩን ፓርቲው ጠቅሶ፣ ኢትዮጵያዊነታችን በልዩነት ውስጥ የተጋመደ አንድነት መሆኑ ሃቅ ሆኖ እያለ የዘውግ ማንነት እና የሃይማኖት ልዩነቶችን እየመዘዙ በሀገር አንድነት ላይ አደጋ መጣል ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንደሚከተን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ግልፅ መሆኑን አመልክቷል ሲል መግለጫው አስታውቋል።
በቅርቡ የተከሰተው የንፁሃን ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ እና በረጅም ጊዜ ድካም የተገነቡ ሀብቶች ውድመት ያለፉት 27 ዓመታት የተዘሩት የሀሰት ትርክቶችና የአገዛዝ ቅሪቶች እንጂ የኢትዮጵያውያን እሴቶች አለመሆናቸውን በመግለጫቸው አመላክቷል።
መንግሥት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ እና የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ጉዳይ ባስቸኳይ አጣርቶ ፍትህ እንዲያገኙ፤ የሀገርን ህልውና እና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቁን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ሽግግር እውን ለማድረግ የሚያስችል የባለድርሻዎች ውይይት ሳይውል ሳያድር እንዲጀመር እና ሚዲያዎች የሀገሪቱን ሕግና የሙያውን ሥነ-ምግባር ጠብቀው እንዲሠሩ አሳስቦ፤ ሥነ ምግባርን አክብረው በማይሰሩት ላይ የሚመለከተው አካል ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደለበት በመግለጫው አብራርቷል።
የውስጥ ልዩነቶቻችንን በሠለጠነ ፖለቲካ አሰታርቀን እንደሀገር የተደቀኑብንን ተደራራቢ ፈተናዎች በፅናት ማለፍ ካልቻልን ከማንወጣው የከፋ አዘቅት ውስጥ ገብተን እንደምንዳክር መረዳት ይኖርብናል ያለው መግለጫው ፤ የሕግ የበላይነትን በማክበር፣ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት በመተባበር እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አሁን ካለንበት ውስብስብ ችግር ወጥተን ሀገራችንን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጋራ እናሻግር ሲል ለኢትዮጵያዊያን ጥሪ አቅርቧል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2012
Filed in: Amharic