>
5:18 pm - Sunday June 15, 7755

“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል”በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል”

እናት አገራችን ኢትዮጵያ ከ3ሺ ዘመን በላይ የሀገረ መንግስት ታሪኳና ክብሯን በሚጠሉ የውጭ ሀይሎች እና ያልዘሩት በቀል በሆኑ የውስጥ ባንዳ ልጆችዋ ሰላሟ ሲናጋ ድንበሯ ሲገፋ መኖሯ በታሪክ ሰነዶች ተዘግቦ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን በአገራችን በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ የተፈፀመው እኩይ ተግባር ለአገራችን አዲስ ባይሆንም እየተቸገርንበት ያለው ተግዳሮት በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንኳን በሰው ልጅ በእንስሳት ላይ ይፈጽማል ተብሎ የማይታሰብ ዘግናኝ ተግባር የተከሰተ በመሆኑ ነው፡፡ 

ይህን እኩይ ተግባር ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሊያወግዘው የሚገባ እና ለችግሩ መፍትሄ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊመክርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም ለሠላም፣ ለፍትህ፣ ለአንድነትና ለእኩልነት ሲታገሉ የነበሩ እና እየታገሉ ያሉ የቁርጥ ቀን ኢትዮጵያውያንን አንገት ለማስደፋት በገዢው ፓርቲ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እጅግ ያሳፍራል፤ ያሳዝናል፡፡

ለዚህም ማሳያ በኦህዴድ/በብልጽግና ፓርቲ በ 6/11/2012 ዓ.ም በተሰጠው መግለጫ ላይ በሠላማዊ እና በህጋዊ መንገድ በመስራት ላይ የሚገኘውን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ደምሮ ለመክሰስ የሄደበት መንገድ “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል” የሚለውን የአበውን ብሂል ያስታውሰናል፡፡ 

ላለፉት 27 ዓመታት የህወሓት ሎሌ ሆነው የህዝባቸውን መብት እና ክብር ሲሸጡ፤ ስንዝር ተጠይቀው ክንድ ሲሰጡ የነበሩ ካድሬዎች እንወክልሀለን የሚሉት ህዝብ ላይ ሲፈፀም ለነበረው ህጋዊ እና ሰብአዊ መብት ጥሰት መሳሪያ ሆነው የኖሩ ካድሬዎች ዛሬ ለእኩልነት፣ ለሠላም እና ለፍትህ ሲታገሉ የኖሩ ጀግኖች የመሠረቱትን ፓርቲ በህወሓት ሎሌነት መፈረጃቸው “አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፤ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የተሰኘውን የአበውን አባባል ከምንግዜውም በላይ ያስታውሰናል፡፡ እንዲሁም ያለንበትን ወቅት አሳሳቢነት ከማሳየቱም በላይ ትላንት አለቆቻቸው ሠላማዊውን ህዝብ አንገት ለማስደፋት አስቀድመው /ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኦብነግ/ የሚል ስም ለጥፈው በአሸባሪነት ከፈረጁ በኋላ አይኑ ውሃው ያላማራቸውን ዜጋ ከእነዚህ ስሞች አንዱን በመስጠት የዜጎችን ህጋዊ እና ሠላማዊ ክብርና ሰብአዊ መብት ሲጥሱ መኖራቸውን አምነው ይቅርታ ከመጠየቃቸውም በላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዶክመንታሪ ሰርተው አሳይተውናል፡፡ አሁንም በኦህዴድ/ብልጽግና ፓርቲ የተሰጠው መግለጫ ላይ የኢትዮጵያን አንድነት ከሚያናጉ ኃይሎች ከህወሓትና ኦነግሸኔ ጋር ፓርቲያችንን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መደመርና ለደረሰው የሰብአዊና የንብረት ውድመት በኃላፊነት ለመጠየቅ መሞከር “ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ይሆናል፡፡ ይህ የገዢው ፓርቲ አካሄድ የደረሰበትን ግፍና መከራ ታግሶ ሰላሙን ለማስከበር እየታገለ ያለው አዲስ አበቤ ላይ የታቀደውን ሴራ የሚያመላክት ነው፡፡

የአንድነት ኃይሉም የፋሲካዋ በግ የገናዋን እያየች ሳር እንደምትግጠው በግ ዝም ብሎ ተራውን ከመጠበቅ ይልቅ ይህን የገዢው ፓርቲ መሰሪ አካሄድ ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በእኩልነትና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የምታምኑ መላ ኢትዮጵያውያን በራሱ ድክመትና ስህተት በተፈጠረ ሞትና መፈናቀል አሰታኮ ሕግ በማስከበር ስም ኢህአዴግ ቁጥር2 /ብልጽግና/ ወደለየለት አምባገነናዊ ስርዓት እየተሸጋገረ እንደሆነ በግልጽ ልታጤኑት ይገባል፡፡ ከፍርድ ቤት ምርመራ እና ውሳኔ በፊት የፖለቲካ አመራሩ ፍ/ቤቱ ምን መወሰን እንዳለበት በቅድሚያ የፖለቲካ መመሪያ እየሰጠ መሆኑ በገሀድ እየታየ ነው፡፡ ምርመራ ተጠናቆ የፍርድ ሂደቱ አልቆ ትክክለኛ አስገዳዮች እነማን እንደሆኑ በፍርድ ሂደት ከመጣራቱ በፊት አስገዳዮቹ ህወሓት እና ኦነግሸኔ እንደሆኑ መንግስት በአደባባይ ለሕዝብ እየገለፀ ይገኛል፡፡ እንደሚታወቀው እስካሁንም ቢሆን ሕወሓትና ኦነግሸኔ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ በፈፀሙት ግፍና በደል መንግስት ሕግን የማስከበር ኃላፊነቱን ሆን ብሎ በሚመስል መንገድ ዘንግቶ ይዞ ለህግ አላቀረባቸውም፡፡ ከሰሞኑ አሰቃቂ ድርጊት ጋር በተያያዘም ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ መግለጫ ከመስጠት ባለፈ በኦነግሸኔና በህወሓት ላይ ሕጋዊ ክስ አልመሰረተም፡፡ ፍላጎትም ያለው አይመስልም፡፡ ስለዚህ ሰሞኑን የተጀመረው የሕግ ተውኔት ዋነኛ ኢላማ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኘውን የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን ምዝገባ ለመሰረዝ እና ፓርቲው በመጭው ምርጫ ላይ እንዳይወዳደር ለማድረግ መሆኑን ሕዝቡ ሊያውቀው ይገባል፡፡

በተለይ በግፍ የታሰሩ አመራሮችና አባላቶቻችን ላይ ፍ/ቤት ከመቅረባቸው በፊት በአገዛዙ መሪዎች በተለያዩ ጊዜ ውንጀላ እየተካሄደባቸው ይገኛል፡፡ ፓርቲያችንም በሕጋዊ መንገድ የተመዘገበ መሆኑን በመካድ ጠ/ሚኒስትሩ ከከፍተኛ የስራ ኃላፊዎቻቸው ጋር ባደረጉት ስብሰባ “ባልደራስ ብሎ ራሱን ያደራጀ” በሚል ፓርቲው በሕግ የተቋቋመ ሳይሆን ሕቡዕ ድርጅት አስመስለው በማቅረብ “ራስ ከሳሽ ራስ ፈራጅ” ሆነው ይገኛሉ፡፡ በአንድ ወቅት ጠ/ሚኒስትሩ “ግልጽ ጦርነት ነው የምንገጥመው” ብለው ያሉትን እያስታወስን የሰሞኑ ውንጀላ ቀደም ሲል የታሰበና የታቀደ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ህዝብ ማን ምን እንደሆነ ያውቃል፡፡ እየተሻሻለ ነው በሚባልበት የፍትህ ስርዓት ውስጥ ልክ እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ/ ዘመን ከተሟላ የፍርድ ሂደት በፊት በፖለቲካ ውሳኔ የዳኝነት ነፃነት እየተገፈፈ ነው፡፡ 

ኦህዴድ/ብልጽግና ፓርቲ በፓርቲያችን ላይ የፈፀመውን ስም ማጥፋት ባስቸኳይ እንዲያስተባብል እንጠይቃለን፡፡ ይህን ሳያደርግ ቢቀር ይህ የፓርቲያችን የአቋም መግለጫ እንደ ህጋዊ ማስጠንቀቂያ እንደሚቆጠር እያሳወቅን በተከታይም አቤቱታችንን ሥልጣን ላለው ፍ/ቤት በማቅረብ በህግ የምንጠይቅ መሆኑን እንገልፃለን፡፡

 

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ 

ድል ለዲሞክራሲ!

Tel. 09 05 00 25 25 E.mail:-    balderasethiopia@gmail.com www.balderasfordemocracy.com

Filed in: Amharic