>
6:27 pm - Saturday November 27, 2021

ኢትዮጵያ የታላቁ የኅዳሴ ግድብን ውኃ ሙሌት መጀመሯን በይፋ ገለጸች! (ይታገሱ አምባዬ)

ኢትዮጵያ የታላቁ የኅዳሴ ግድብን ውኃ ሙሌት መጀመሯን በይፋ ገለጸች!!!

ይታገሱ አምባዬ
DW

የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ምኒስትር ስለሺ በቀለ የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት መጀመሩን አረጋገጡ። የአውሮፓ የኅዋ ኤጀንሲ ንብረት የሆነችው ሴንቲኔል-1 የተባለች ሳተላይት ይፋ ያደረገቻቸው ምስሎች ትክክለኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የታላቁ የኅዳሴ ግድብን ውኃ ሙሌት መጀመሯን በይፋ አረጋገጠች። በግድቡ ውኃ መከማቸቱን የሚያሳዩት የሳተላይት ምስሎች ትክክለኛ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ምኒስትር ስለሺ በቀለ እንዳረጋገጡ የግድቡ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ምኒስትር ስለሺ በቀለ “የግድቡን ተፈጥሯዊ የግንባታ ሂደት በጠበቀ መልኩ የውኃ ሙሌቱ እየተከናወነ ነው” ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።
የአውሮፓ የኅዋ ኤጀንሲ ንብረት የሆነችው ሴንቲኔል-1 የተባለች ሳተላይት ይፋ ያደረገቻቸው ምስሎች ከግድቡ ጀርባ ከወትሮው የበለጠ መጠን ያለው ውኃ መጠራቀም መጀመሩን አሳይተዋል።
የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በግብጽ እና በሱዳን የውኃ እጥረት ሊፈጥር ይችላል የሚለውን ሥጋት በብሪታኒያው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የከባቢ አየር ለውጥ ተመራማሪ “ምክንያታዊ አይደለም” ሲሉ አጣጥለዋል።  በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የከባቢ አየር ለውጥ ጥናት ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ኬቭን ዊለር ግድቡን ለመሙላት የሚያስፈልገው የውኃ አመጠን ከአጠቃላይ የወንዙ ፍሰት አኳያ አነስተኛ ነው ብለዋል።
ኬቭን ዊለር “የመጀመሪያው ሙሌት ከግድቡ ጀርባ የውኃ ክምችት የሚጨምርበት ወይም ውኃ ከፍ የሚልበት ጊዜ ነው። መጠኑ እጅግ በጣም ትንሽ ነው። 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ብቻ ነው። ይሁንና በቦታው የወንዙ አማካኝ የፍሰት መጠን 49 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ገደማ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“የውኃ እጥረት ይፈጠራል የሚለው ማንኛውም ሥጋት በዚህ ወቅት አሳማኝ አይደለም። በሚቀጥሉት በርካታ አመታት ድርቅ ከተከሰተ በእርግጥ ያ ሥጋት ይሆናል። አሁን የሚቀርበው ሐሳብ ግን በናይል ተፋሰስ እየተፈጠረ ካለው የኃይል ሚዛን ለውጥ እና እንቅስቃሴ የሚመነጭ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ግብጽ ግድቡ ለገበሬዎቿ እና 100 መቶ ሚሊዮን ዜጎቿ ሕልውና አደጋ ይሆናል ስትል በተደጋጋሚ ሥጋቷን ገልጻለች። ኢትዮጵያ ከግብጽ እና ሱዳን ከአንዳች ሥምምነት ሳትደርስ የግድቡን የውኃ ሙሌት ብትጀምር በሶስቱ አገሮች መካከል ያለውን አለመግባባት ወደ ከፋ ውጥረት ይገፋዋል ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በግድቡ ላይ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በአሸማጋይነት የተሳተፉባቸውን ጨምሮ ለአመታት የዘለቁ ድርድሮች ቢደረጉም እስካሁን መፍትሔ አልተገኘም። የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት በታዛቢነት የተቀላቀሉበት የመጨረሻው ድርድር እንደ ቀደሙት ውጤት አልባ እንዳይሆን አስግቷል። የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ምኒስትር ስለሺ በቀለ በመጨረሻው ድርድር መግባባቶች ቢኖሩም የመጨረሻ ስምምነት ላይ አለመደረሱን በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ ላይ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ለሁለት ሳምንታት ገደማ ያደረጉት ድርድር ባለፈው ሰኞ ያለ ውጤት ተበትኗል። ኢትዮጵያ “ያልተለወጠው የግብጽ እና የሱዳን አቋም እንዲሁም የተጋነነ ፍላጎት ድርድሩ ከውጤት እንዳይደርስ ዕክል ፈጥሯል” ብላለች።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲው ኬቭን ዊለር  “በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ቢያንስ የግድቡን የመጀመሪያ የውኃ ሙሌት በማከናወን አቋሟ እንደጸናች ትገኛለች። ግድቡን ውኃ መሙላት በሚጀምሩበት በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ከስምምነት ከደረሱ ከዚያም በኋላ ድርድራቸውን ይቀጥላሉ” ሲሉ ቀጣዩ የድርድር ሒደት ምን ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሶስቱ አገሮች በድርድሩ የደረሱበትን ለአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀ መንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በተናጠል እንደሚያቀርቡ ኢትዮጵያ አስታውቃለች። ሱዳን “ሚዛናዊ እና ፍትኃዊ” ያለችውን የሥምምነት ረቂቅ ለአፍሪካ ኅብረት ማስገባቷን የአገሪቱ የመስኖ እና የውኃ ሐብቶች ሚኒስቴር ትናንት ማምሻውን አስታውቋል። መስሪያ ቤቱ “ሱዳን የኅዳሴ ግድብ ድርድር የመጨረሻ ሪፖርት የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ፕሬዝዳንት ለሆነችው ደቡብ አፍሪካ አቅርባለች” ብሏል።
ምንጭ :- DW
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ
Filed in: Amharic