>
5:30 pm - Thursday November 2, 1522

ፈናፍንታምነት (ከይኄይስ እውነቱ)

ፈናፍንታምነት

ከይኄይስ እውነቱ

ፈናፍንት፤ ከተፈጥሮ አኳያ የሚሰጠው ትርጕም እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ዐጓጕል፣ ከኹሉ አለኹ የሚል፣ ጉደኛ÷ ጉዳም፣ ነውር፣ ጸያፍ፣ የሚያስጠላ ማለት እንደሆነ ታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ› መጽሐፋቸው ተርጕመውታል፡፡ ይህ ዐጓጕልነት ለሰው ጠባይም ሊቀጠል ይችላል፡፡ ከሁሉ አለኹ የሚል ሰው ፈናፍንታዊ ነው፡፡ አቋም መያዝ ባለበት ጉዳይ በነፈሰበት የሚገኝ ፈናፍንታዊ ነው፡፡ የግል ጥቅሙን እያየ የሚገለባበጥም ፈናፍንታዊ ነው፡፡ ባገር ጉዳይ ትኩስ ወይም በራድ ያልሆነ÷ በሁለት ልብ የሚያነክስ አገዛዝ ፈናፍንታዊ ነው፡፡ ለእኔ በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ወዲህ ያለው አገዛዝ ፈናፍንታዊ ነው፡፡ 

ላለፉት 27 ዓመታት ኢሕአዴግ የሚባል ድርጅት የለም ሕወሓት እንጂ ስል ቆይቼአለሁ፡፡ በእርግጥም ከስም ባለፈ አልነበረም፡፡ ወያኔ ከሥልጣኑ ገለል ብሎ የመንደር አሸባሪ ከሆነ በኋላ ውላጁ ኦሕዴድ የወያኔን ቦታ በተረኝነት ተክቶ ከባርነት ወደ ጌትነት ሲመጣ ኢሕአዴግ የሚባለው የአገዛዝ ደዌ ካለመኖር ወደመኖር ተሻገረ፡፡ ቢያንስ በኦሕዴድ በኩል፡፡ ወያኔ ሦስቱን ውላጆቹን ‹ገበሮ/ገርባ› አድርጎ ቆሻሻ ሥራውን እያሠራ ዝንተ ዓለም እንደሚቀጥል ነበር የሚያስበው፡፡ ‹አዲሱ ጌታ› የቀድሞ ጌታውን መለ ከሸኘ በኋላ በተራው ኢሕአዴግን ኦነጋዊ ጠበል አጥምቆ አዲስ ስም በማውጣት ሎሌ ጓዶቹን (ብአዴን፣ደሕዴን) እና ‹አጋር› ተብዬዎችን በየአካባቢው በውክልና አስቀምጦ ከወያኔ የቀረውን ጥፋት በሚገርም ፍጥነትና መጠን እየፈጸመና እያስፈጸመ ይገኛል፡፡  ወገኖቼ ሰው ጥርሱን ነቅሎ ካደገበት ቆሻሻ ‹የፖለቲካ ሕይወት› የሚፀዳ ይመስላችኋል? በግፍና በንቅዘት ላይጠገኑ የተበላሹት ወያኔና ውሉዶቹ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት በሕግ ለተወሰኑ ዓመታት ካልታገዱና በፈጸሙትም ግዙፍ ጥፋቶች ካልተጠየቁ ኢትዮጵያ አገራችንና ሕዝቧ ሰንበት ያገኛሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብ አስተዳደር (ፖለቲካ) ዐውድ ስናየው አንድ ሰው ባንዴ የዘር/ጐሣ ፖለቲከኛ እና ኢትዮጵያዊ ዜግነትን መሠረት የሚያደርግ ፖለቲከኛ ሊሆን አይችልም፡፡ የሁለቱ ቅይጥ የሚባል ነገር የለም፡፡ ፈናፍንታምነት ካልሆነ በቀር፡፡ የፖለቲካ ትኩሳቱ ወዳየለበት ወይም የኃይል ሚዛኑ ወዳጋደለበት ዥዋዥዌ የሚጫወተውም ከፈናፍንታዊ ወገን ነው፡፡ አገር ሲፈርስ የታይታ ዕጉሥነት÷ ሥልጣን ሲሆን ያዙኝ ልቀቁኝ ባይነት ፈናፍንታምነት፡፡ ዐባይ እና ጣና÷ አንዱ የንትርክ ሌላው የጥፋት ቀጣና፡፡ ይህ አልያዝ አልጨበጥ ባይነት÷ የቃልና የተግባር ሥምረት ማጣት፣ ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ መውጣት፣ ሲመች አገር ሳይመች መንደር፣ ቀን ድንፋታ ሌት ዱለታ፣ እያፈረሱ እያፈናቀሉ ለግል ዝና የሚደረግ ግንባታ÷ ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ላጭታ፣ ሽብርተኛው ቤተኛ ሕጋዊው መጻተኛ፣ የውጭ ዜጋው ባለሥልጣን÷ ሹመኛ እና ፖለቲከኛ፣ ባለሀገሩ/ዜጋው ባይተዋር÷ ተሳዳጅ÷ ተፈናቃይና ታሳሪ፡፡ እየበተኑ አንድነት ፈናፍንታዊነት፡፡

ወገኖቼ በዚህች በተቀደሰች ምድር ከአጋንንት መካከል ምርጫ ሲቀርብላችሁ እንቆቅልሽ አይሆንባችሁም? 

Filed in: Amharic