>
5:18 pm - Friday June 16, 8237

ባለጡንቻዎች መናገር የማይፈልጉትን መናገር ያሳስራል!!! (ግርማ ካሳ)

ባለጡንቻዎች መናገር የማይፈልጉትን መናገር ያሳስራል!!!

ግርማ ካሳ

በሕግ የበላይነት አምናለሁ። ማንም ከሕግ በላይ መሆን የለበትም። እስክንድር ነጋ፣ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ ወንድም ስንታየሁ ቸኮልን አውቃቸዋለሁ።  በአካል ብዙ ጊዜ ተገናኝነተን አውርተናል።  እነርሱም ራሳቸው የሚያወቁት፣  ግርማ ካሳ ካልተስማማ ዝም የሚል እንዳልሆነ ነው። ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን ብዙ ጊዜ ተችቼው ተቃውሜው ጽፊያለሁ። እርሱና ድርጅቱ አብሮነት የሽግግር መንግስት ብለው ያሉት ሐሳብ ውድቅ ነው ያደረኩት። እነ እስክንደር ነጋና ስንታየሁ ቸኮልን እንደዚሁ። ከመስከረም 30 በኋላ የባለሞያዎች መንግስት ይቋቋም ያሉት ሪያሊስቲክ ያልሆነ ሐሳብ ነው ብዬ ነው በይፋ ውድቅ ያደረኩት። እነ እስክንድርን በጭፍንና በስሜት የምደግፍ ሰው አይደለሁም።
ሆኖም ግን አንድ እርግጠኛ የሆንኩበት ነገር እነዚህ ወንድሞች ኢንቴግሪቲ ያላቸው ናቸው። አደርባይና አጨብጫቢ አይደሉ።፡ለመርህ ፣ ለዴሞክራሲና ለፍትህ የቆሙ ናቸው።
ኢንጂነር ይልቃል ከማንም በላይ በተለይም በኦሮሞ ክልል ባሉ ሌሎች ማህበረሰባት  ላይ የሚደርሰው ግፍና ሰቆቃ consistently ሲያጋልጥ የነበረ ሰው ነው። የነዚህ ወገኖ አጋርና አድቮኬት ነበር። እስክንድርና ስንታየሁ ቸኮል ደግሞ እየሰሩት የነበረውን አገር የሚያውቀው ነው። ለዜግነት ቆመናል የሚሉ የስም የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች፣ ዝምታን በመረጡበት ጊዜ፣ ለተገፋው፣ መድልዎ ለሚፈጸምበት፣ መብቱ ለተረገጠው አዲስ አበቤ መብት የሞገቱ፣ የባለጊዜዎችን ዘረኝነት ያጋለጡ ናቸው።
ብዙ ርቀን መመራመር የለብንም። እነ እስክንድር የታሰሩት የዘመኑ ባለጡንቻዎች መስማት የማይፈለጉትን በመናገራቸው ነው። አራት ነጥብ።
እሺ ባለጡንቻዎቹ እነ እስክንድርን ሲያስሩ “ለፖለቲካ ስልጣናቸው ብለው ነው። በፊትም በሕወሃት ጊዜ የነበሩ ሰዎች እንደመሆናቸው፣  ያ የማፈንና የዜጎችን መብት የመርገጥ አባዜ አሁንም ስላልተለያቸው ነው ” ልንል እንችላለን።
ግን በጣም የሚደብረው የአንድነት ኃይል ነን፣ ለዲሞክራሲ ቆመናል የሚሉ ተደማሪዎችና ተለጣፊዎች፣  የነ እስክንደርን መታሰር ጀስትፋይ ሊያደረጉልን ሲሞክሩ ማየት ነው። ይሄ አይነት ፖለቲካ የምሬን ነው የምላችሁ disgusting ነው። ጃዋር ታስሯል። ጃዋር ከስድስት ወራት በፊት ነበር መታሰር የነበረበት። የጃዋርን ደጋፊዎች ለማባበል ፣ ለማባያ፣  እስክንድር መታሰሩ እነዚህን ሰዎች አያሳስባቸው። ለነርሱ ንጹህ ሰው የመታሰሩ ነገር ሳይሆን፣ አሳሪዎቹ እንዳይቀየሙን የሚለው ነገር ነው ውስጣቸውን የሞኮረኩረው።
አንዳንዶች ደግሞ በቀጥታ እስክንድርን ከጃዋር ጋር የሚያገናኙም አሉ። ይሄ የለየለትን ነዋራነት ነው። ጃዋር ለብዙ ዜጎች መሞትና መገደል ምክንያት የሆነ ወንጀለኛ ነው። እስክንድር ፍጹም ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሰው ነው። ጃዋር ብዙ መሳሪያ የታጠቁ  አጅበውት እንደ አገር መሪ የፈለገውን የሚያደርግ ነው። እስክንደር በታኪስና በባስ ነው በአዲስ አበባ በነጻነት የሚመላለሰው። ጃዋር ፌንፊኔ የኦሮሞ ናት ብሎ ኦሮሞ ልዩ ተጠቃሚ መሆን አለበት የሚል ነው። እስክንድር ኦሮሞ ሆነ ማንም የአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ እኩል ተጠቃሚ መሆን አለባቸው የሚል ነው። ጃዋር ኢትዮጵያ ብትፈራርስ ግድ አይሰጠውም። እስክንደር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት መጠበቅ አለበት የሚል ነው። ጃዋር ጥጋበኛ ነው። እስክንደር ትሁት ነው። ….ሁለቱ ሰማይና ምድር ናቸው። ሁለቱን ማነጻጸር ደግሜ እልለሁ ነውረኛነት ነው።
የሚያሳዝነው ደግም እንዲህ የሚሉት ከማንም በላይ እውነታውን የሚያውቁ፣ እስክንድርን የሚያውቁ ሰዎች ናቸው። ማፈሪያዎች !!!! በቃ የኛ ፖለቲካ ከሃዲ የበዛበት ፖለቲካ ነው ያሳዝናል።
እኔ ግን ይሄን እላለሁ፣ ግርማ ካሳ ማለት እስክንደር ነጋ ማለት ነው። ግርማ ካሳ ማለት ስንታየሁ ቸኮል ማለት ነው። ግርማ ካሳ ማለት ይልቃል ጌትነት ማለት ነው። አበቃው።
Filed in: Amharic