>

"ሳናጣራ አናስርም" ያሉን ጠ/ሚ :- ዜጎችን ጨለማ ቤት አስረው መረጃ ለማሰባሰብ ሲሯሯጡ ማየት አሳፋሪ ነው...!?! (ደረጄ ከበደ)

“ሳናጣራ አናስርም” ያሉን ጠ/ሚ :- ዜጎችን ጨለማ ቤት አስረው መረጃ ለማሰባሰብ ሲሯሯጡ ማየት አሳፋሪ ነው…!?! 
 ደረጄ ከበደ

በእስክንድር ነጋ ላይ የተመሰረተው ክስ ከቶ አንዳችም ውነትነት የለውም። ክሱን በመሰረቱበት በአቢይ አህመድና በአቃቢ ህጉ እጅግ አፍሬአለሁ። ዶ/ር አቢይ የሰውን ቆዳ ከነህይወቱ የገፈፉትን ወንጀለኞች እየፈራህ እስከመቼ ንፁሃንን ታጠቃለህ?
እስክንድር ነጋ እንኩዋንስ ወጣቱን በገንዘብ ለአመፅ ሊያነሳሳ ይቅርና ጨዋነት ያልተላበሰ አነጋገር እንኩዋን ከአንደበቱ የማይወጣ፣ ከዴሞክራሲና ከፍትህ ውጭ ምንም አጀንዳ የሌለው የህዝብ ልጅ ነው። በዚህ ክቡር ኢትዮጵያዊ ላይ አይን ያወጣ ውሸት መዋሸት ሽቅብ ሊለኝ ዳድቶታል። በሃሰት መመስከር ሃጢአት ነው። ወንጀል ነው። በእስክንድር ላይ ዛሬ የአቢይ መንግስት በሃሰት መስክሮአል። ዛሬ እንደ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያ በጣም አፍሬአለሁ።
አቢይና ታከለኡማ ቤቱን እያፈረሱ በኮሮና ወረርሽኝ ሜዳ ለወረወሩት ዜጋ ደራሽ ነው እስክንድር። ይህ ያበሳጫቸዋል መሰል። ሃላፊነት የጎደለው ክፉ አስተዳደር ሜዳ ላፈሰሳቸው ወገኖች የአንድ ቀን እንኩዋን መጠለያ ሳይሰጣቸው የትላንት ባለቤቶችና ባለተስፋዎች ዛሬ አስፓልት ላይ ግራ ተጋብተው በገዛ ሃገራቸው ሲጎሳቆሉ አቢይና ሹሞቹ ዝምብን የጎዱ ያህል እንኩዋን ሆኖ አይሰማቸውም። በሞቀ ቤታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ኑሮአቸውን እንደወትሮው ያለሃሳብ ይኖራሉ። እስክንድር ግን ያንን ዝም ብሎ የማየት ድንዳኔ አልፈጠረበትም። ለተገፉ እድሜውን ሁሉ በእስርና በስቃይ ያሳለፈ ጨዋ ኢትዮጵያዊ ነው። የአቢይ መንግስት ስንት ጊዜ ይህንን ምግባረሰናይ ሰው አንገላታው? በቅርቡ የሞአ አንበሳ ዘ እምነገደ  ኢትዮጵያን የአንበሳ ሃውልት በአረምና በቆሻሻ መሃል አዲስ አበባ ጥለውት እስክንድርና ባልደረቦቹ ሄደው ሊያፀዱ ቢሞክሩ የመንግስት ፖሊስ ልክ ወንጀል እንደተፈፀመ አይነት ፅዳቱን ከማስቆሙም በላይ በፈቃደኝነት በሰላም የሃውልቱን ዙሪያ የሚሰቀጥጥ ቆሻሻ ሳይፀየፉ ሊያፀዱ የመጡትን ምስኪኖች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱዋቸው። ይህን ጉድ ምን ይሉታል? ይሄ ነው የዴሞክራሲና የመደመር ገፅታው?
መንግስት የጣላቸውን፣ ያጎሳቆላቸውን፣ መኖራቸውን የረሳቸውን ዜጎች እስክንድር በማሰቡ የአቢይ መንግስት ምን አስቆጣው?? ከእስክንድር ለምን አይማርም?  ዜጎችን መንከባከብን ለምን ከእስክንድርና ከባልደረቦቹ አይማርም? ሰው ራሱ በጎ ማድረግ ካልቻለ ሌላው ቢቀር ሌሎች በጎ ሲያደርጉ መንገድ ባለመያዝ መተባበር እኮ ትልቅነት ነው። እዎ እስክንድርን በተግባር ማየት ለብዙዎችን ሆድ አደር ፖሊቲከኞች ከህሊናቸው ጋር እንዲጋፈጡ የሚያደርግ መስተዋት ስለሚሆንባቸው  አይወዱትም። ሃጥአን የፃድቃን ጠረን ያስጨንቃቸዋል።
የእስክንድር ባልደራስ ፓርቲ አመራሮች እነ ስንታየሁ ቸኮልና አስቴር ስዩም የመሪያቸው የእስክንድር ደቀመዝሙሮች ናቸው። በምግባር የታነፁ። ስለዴሞክራሲ ዋጋ የከፈሉ ናቸው። ዴሞክራሲ አለ የምንለው እንደነ ስንታየሁ ቸኮልና እስክንድር ነጋ አይንት ዜጎች ያላቸውን የፖሊቲካ አቁዋም ያለምንም ገደብ ለማስተላልፍ መድረክ ሲያገኙ፣ መግለጫ ለመስጠት ከየሆቴሉ በመንግስት የእጅ አዙር ክልከላና እቀባ ሳይባረሩ፣ በመንግስት በታጀበ ቄሮ ሳይዋከቡ መናገርና መፃፍ ሲችሉ ብቻ ነው። እስክንድር በታከለ ኡማ ሴራ አዳራሽ ሁሉ እንዲዘጋበት ተደርጎ አስፓልት ዳር መግለጫ ሲሰጥ ማየት እጅግ እጅግ ያሳፍራል። እስክንድር በአደገበት ከተማ ስቴዲዮም ገብቶ ኩዋስ እንኩዋን እንዳያይ በአቢይ ፖሊሶች መከልከል መለስ ዜናዊስ እንዲህ አድርጎአል እንዴ? ትዝ አይለኝም።
እስክንድር ናጋ ተነፍጎት የቆየው የንግግርና የመሰብሰብ ነፃነት ለጀዋር መሃመድ እስከ ነአጃቢዎች ነበር የተሰጠው። እናም አቢይ ለፈቀደው የመንቀሳቀስ መብት ይሰጣል ላልፈቀደውና ለሚፎካከረው ግን ወዮለት ነው ነገሩ?  ያ ነው እንግዲህ የብልፅግና ፓርቲና የመሪው የጠ/ሚኒስትር አቢይ ዴሞክራሲ። የሚፎካከርህን አፍ መዝጋት፣ ማዋከብ፣ መደብደብ፣ ጨለማ ቤት ማሰር፣ አስሮ መረጃ ለማሰባሰብ መሩዋሩዋጥ? ያለምንም ምክንያት የታሰሩ ተቃራኒ ፓርቲ አባላትን አስሮ የቀጠሮ ልዋጭ ለ20 ለ 30 ጊዜ በመስጠት ታሳሪዎችን ያለምንም በደል ለወራት አስሮ ማሰቃየት ያ ነው የአቢይ ዴሞክራሲ? የሰኔውን የአማራ ክልል አመራሮች ግድያ ተከትሎ በጉዳዩ ምንም እጃቸው የሌለበትን ነገር ግን የአቢይን መንግስት የሚቃወሙትን የተለያዩ በተለይ የአማራ መብት ተሙዋጋቾችን ከያሉበት እስር ቤት አጉሮ በቀነ ቀጠሮ ብዙ ወራቶች ሲያሰቃያቸው መክረሙ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። አሁንም በእስር ያሉ አሉ። አቢይ የሚያስረው ለስልጣኑ የሚያስፈሩትን ተፎካካሮዎችን ብቻ እንጅ ነፍሰ ገዳዮችንና ባንክ ሰባሪዎችን አይደለም፣ ይህንን በተደጋጋሚ አይተናል።
ጠ/ሚኒስትሩ አስረን አናጣራም፣ አጣርተን እናስራለን አለ በስልጣኑ ሰሞን። ያ አባባል አመትም አልቆየም ሰዎች ያለምክንያት እየታሰሩ መንግስትም መረጃ ልፈልግ በሚል ሳቢያ ወንጀል አልባ እስረኞችን ለዘመናት ሲያንገላታ።
ክቡር ጠ/ሚኒስትር አሁን የምንጠይቀው ያለምክንያት የታሰሩትን ንፁሃንን እንድተፍታ ነው።እስክንድር ነጋ ላይ የተደረደሩት ክሶች የተፈበረኩ እንደሆኑ ጠላቶቹም ያውቃሉና መንግስት ሆይ ትክክለኛውን ነገር አድረግ። እስክንድር ነጋን ከባልደረቦቹ ከስንታየሁ ቸኮልና ከአስቴር ስዩም ጭምር በነፃ አሰናብት። ከ200 ቀናት በላይ ያሉበትን የማናውቀውን የታገቱትን የአማራ ተማሪዎችንም ያሉበትን ሁኔታ ለህዝብ በግልፅነት አስታውቅ።
ፍትህ ለህሊና እስረኞች፣ ለእስክንድርና ለባልደረቦቹ
Filed in: Amharic