>

የአምባላጌውና የአድዋው ጀግና  የፊታውራሪ ገበየሁ (አባ-ጎራ)   (ዮሴፍ ሳሙኤል)

የአምባላጌውና የአድዋው ጀግና 

የፊታውራሪ ገበየሁ (አባ-ጎራ) 

 ዮሴፍ ሳሙኤል

የሐበሾቹ ጦር ከመካከለኛው በቀር በግራ በኩልም ስለተጫነ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተጠባባቂው ባታሊዮን እንዲመጣ አዘዘ። በዚህ ጊዜ የእቴጌ ጣይቱ ጦር ስድስት ሃኪንስ የሚባሉትን መድፎች ይዘው ከተዋጊው ሦስት ሺ ሜትር ርቀው መድፍ እየተኮሱ ምንም እንኳን በጣልያኖቹ ላይ ጉዳት ባያበዙም ተዋጊዎቹን ሐበሾች ስለደገፏቸው ሁሉም በኪዳነምህረት በር ወደ ፊት እየገፉ ይዋጉ ጀመር በዚህ ጊዜ ተጠባባቂው የሰባተኛው ባታሊዮን ጦር ደርሶ አንድነት ያደረጉት መቋቋም ሐበሾቹን አንድ ሺ ሜትር ያህል ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አደረጋቸው በዚህ አይነት ተዋጊው የጦር ሠራዊት ወደፊት ለመግፋት እንዳመነታ ባየ ጊዜ ቀይ ልብስ የለበሰው ፊታውራሪ ገበየሁ ወደ ሰዎቹ ፊቱን አዙሮ የአምባላጌው አሸናፊ ፊታውራሪ ገበየሁ በምን አኳኋን እንደሞተ ወደፊት ወደ ሸዋ የሚመለሱት ይናገሩ ብሎ ተናግሮ እንደ አንበሳ ተወርውሮ ወደ ጣልያኖቹ መስመር ገብቶ ሲዋጋ ሦስት ሰዓት ላይ በመትረየስ ተመቶ ኪዳነምህረት እበሩ ላይ ወደቀ። ይላል ጣልያናዊው ጸሐፊ ኮንቲሮሲኒ በመጽሐፉ።
ፊታውራሪ ገበየሁ በፈረስ ስማቸው አባ-ጎራ የጦር አበጋዝ ነበሩ። የጦርነቱ ክተት አዋጅ ከታወጀ በኋላ አፄ ምኒልክ በጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ተነስተው በጥቅምት 18 ቀን 1888 ዓ.ም. ወረይሉ ከተማ እንደገቡ ራስ ሚካኤልን፣ ራስ ወሌን፣ ራስ መንገሻ አቲከምን፣ ራስ መኮንንን፣ ራስ አሉላን፣ ዋግሹም ጓንጉልን፣ ደጃች ወልዴን፣ ፊታውራሪ ገበየሁን፣ ፊታውራሪ ተክሌን፣ ሊቀ መኳስ አድነውን፣ ቀኛዝማች ታፈሰን…ቀድማችሁ ወደ አላጌ ዝመቱ የሚቀላችሁ እንደሆነ ውጉት፤ የሚከብዳችሁ እንደሆነ ወደ እኔ ላኩብኝ፤ ብለው እንደላኩባቸው ጸሐፊ ትእዛዝ ገብረሥላሴ ጽፈዋል።
ይህ ግንባር ቀድሞ  በራስ መኮንን አበጋዝነት ከወረይሉ ተነስቶ በመጓዝ ላይ እንዳለ ከደብረ ሃይላ ጦርነት የመጡት ራስ መንገሻ ከነጦራቸው በአሸንጌ ሲጠባበቁ ነበርና ከነራስ መኮንን ጋር ተገናኝተው ሁሉም ጉዞአቸውን ወደ አላጌ ቀጠሉ
 ጉዳዩን በሰላም ለመጨረስ ራስ መኮንን እና ማጆር ቶዞሊ ደብዳቤዎች እየተለዋወጡ ራስ መኮንን ከበው መጠባበቅን እንጂ በቶሎ በጦር ማጥቃቱን የፈለጉ አይመስልም ነበር።
ህዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም. ግን ከዚህ ቀደም ራስ አሉላ በዶጋሊ ጦርነት እንዳደረጉት ፊታውራሪ ገበየሁ ለጌታ አፄ ምኒልክ ድግስ እንጂ የጦር መስተንግዶ እንዲጠብቃቸው አላደርግም በማለት ከጠቅላይ አዛዡ ከራስ መኮንን ትእዛዝ ሳይጠብቁ ፊት ለፊት መድፍ እየተኮሰ እያላገጠ ባበሳጫቸው በማጆር ቶዞሊ ጦር ላይ ውጊያ ከፈቱ የፊታውራሪን ገበየሁ ስሜትና ጀግንነት የተጋሩት ቀኛዝማች ታፈሰና ፊታውራሪ ተክሌ ተከታትለው ሄደው ውጊያውን አፋፋሙት።
በዚህ ጊዜ ራሶቹ ሁሉ በየድንኳናቸው ነበሩ ተኩሱን ሰምተው የጦር መሣሪያቸውን ታጥቀው ከየድንኳናቸው ወጥተው ወደ ጦርነቱ ሲያመሩ የአላጌን ምሽግ የሚያውቁት ሹም አጋሜ ተስፋዬ የአላጌ በር እንኳን ጠበንጃና መድፍ ተጠምዶበት በድንጋይ እንኳን አንድ ሰው ሊከላከልበት ይችላልና አልጋውን እንዳታፈርሱት በምኒልክ አምላክ ወደየድንኳናችሁ ግቡ ብለው ተማጽነዋቸው ነበር፤ እራሶቹ ግን እርስ በእርስ ተመካክረው እኛ እዚህ ተቀምጠን የንጉሡን አሽከር ፊታውራሪ ገበየሁን ዝም ብለን እንዴት እናስገድለዋለን ተባብለው ወደ ጦርነቱ ገብተው ገጠሙ።
ራሶቹ በደረሱበት ሰዓት ፊታውራሪ ገበየሁ በበቅሎ ሆነው ዘንጋቸውን ይዘው አይዞህ ጥይትም ያለቀብህ በጎራዴ በለው እያሉ ወታደሩን እያደፋፋሩ እየተዋጉ እንደነበር ከራስ መንገሻ ዮሐንስ መልዕክተኛ እንደሰሙ ጸሐፊ ትእዛዝ ገብረሥላሴ አስነብበዋል።
ራሶቹም በቀኝ በኩል የራስ ወሌ ጦር በመካከል የራስ መኮንንና የራስ ሚካኤል ጦር በስተጀርባ የራስ መንገሻና የራስ አሉላ ጦር ሆነው ገጠሙ፤ ዋና አዝማቹ ማጆር ቶዞሊ ወዲያና ወዲህ እያለ ጦሩን ሲያዋጋ በያለበት ያለው ጦር የመከበብ አደጋ እንደገጠመው ተረዳ የጦሩን ግንባር ለማጥበብ ሃይሉን በመሰብሰብ ለመዋጋት ከሞከረ በኋላ የሁሉም መዳከም ስለተቃረበ ተጠባባቂውን ጦር እንዲዋጋ አዘዘ…..
ውጊያው ጠዋት ጀምሮ ስድስት ሰዓት ድረስ ቀጥሎ የጣልያን ጦር ሽሽት ጀመረ። ማጆር ቶዞሊም ፊቱን በሀዘንና በንዴት እንደጨመደደ አዙሮ ወደ ኋላ ሲወርድ የራስ አሉላ ሰዎች ዞረው እንደያዙበት ተመለከተ በዚያን ጊዜ ያደረጉትን ያድርጉኝ ብሎ ፊቱን ወደ ጠላቶቹ ሲመልስ ወዲያው ከደረቱ ላይ ተመትቶ ወደቀ።
የአምባላጌው ጦርነት በጠቅላይ አዛዡ በራስ መኮንን ትእዛዝ ሳይሆን በአበጋዙ በፊውታራሪ ገበየሁ ስለተከፈተ ምንም እንኳን ድሉ የኢትዮጵያውያን ሆኖ እራሳቸውም በደንብ የተካፈሉበት ቢሆንም የጦርነቱ ጉዳይ በድል ከተደመደመና የጦር ኃይላቸውን ኃይል ካሳዩ በኋላ ራስ መኮንን ጦርነቱን ያለ ትእዛዝ የጀመሩትን ፊታውራሪ ገበየሁንና ቀኛዝማች ታፈሰን አሰሯቸዉ።
የአምባላጌ ድል የምስራች ወሎ ግዛት ለሚገኙት ለአፄ ምኒልክ ለመንገር በደብዳቤና በቃል አሽከራቸውን የላኩ
ራስ መንገሻ ዮሐንስ ናቸው። ደብዳቤውም እንዲህ ይል ነበር
ይድረስ ከስዩመ እግዚአብሔር ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፤ መድሃኒአለም ጤና ይስጥልኝ ብዬ እጅ እነሳለሁ።
          ልጅዎ ራስ መንገሻ
ጃንሆይ ጦርነቱ አልታሠበም ነበር ፊታውራሪ ገበየሁ ሄዶ ገጠመው እኔ በግንባር መኳንንቱ ደግሞ በጀርባው ገቡበት ከመኳንንቱ ሠራዊቱ፤ ከሠራዊቱ መኳንንቱ እንደዚህ ያለ ተዋጊ ታይቶ ተሰምቶም አይታወቅም፤ ይህ ሁሉ የሆነ በምኒልክ ሀብት ነው ፈረንጅ እንኳን መድፍና ወጨፎ ይዞ የአለጌ አንባ ሲሰበር ከጥንት አባቶቻችን በድንጋይ ይመለስ ነበር። ከዚህ በፊት ተደርጎ የማይታወቅ ዛሬ በምኒልክ ሀብት ተደረገ እንግዲህም የምኒልክ ሀብት ይጠብቀናል።
      ታህሳስ 4 ቀን 1888 ዓ.ም. ተጻፈ።
ይህ መልዕክት ለአፄ ምኒልክ እንደደረሰ መልዕክተኛውን ሸልመው እኔም መጣው እግዚያብሔርም ቀኙን ለኛ ያድርገው ብለው መልሰው ሰደዱት።
በዚያን ሰሞን ልጁም አዋቂውም ገበየሁ ገበየሁ እያለ እንዳነሳው “ጎበዝ አየሁ” የሚል ስያሜም እንደወጣለት ጸሐፊ ትእዛዝ ገብረሥላሴ ጽፈዋል።
“ጎበዝ አየሁ” በጊዜው የነበረ ጠበንጃ ስም ነበር።
       ከነፍጥ ጎበዝ አየሁ
       ከአሽከር ገበየሁ
       የንጉሥ ፊታውራሪ ያ ጎራ ገበየሁ
       አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው
       ለምሳ ሳይደርሱ ቁርስ አደረጋቸው።
በማለት ትንሹም ትልቁም ገጥሞላቸው ነበር።
የአላጌውን ምሽግ በመስበር በጣልያን ላይ ድል ያስገኙትና የመቀሌውን ጦርነት በመካፈል እጃቸው የቆሰለው የጦር አበጋዙ ፊታውራሪ ገበየሁ የአድዋ ዕለት ወደር በሌለው ጀግንነት ነበር ተዋግተው ሕይወታቸውን የሰጡት።
በአድዋ ጦርነት ተማርኮ አዲስ አበባ መጥቶ የነበረው የጣልያን መኮንን ጆቫኒ ቲዶኒ በጻፈው ማስታወሻ ላይ ይህን አስፍሮ ነበር… ይላሉ ተክለጻድቅ መኩርያ….
በቪያንኪኒና በማዜቶ በሚመሩት መድፎች እየተመቱ ሐበሾች ወደ ኋላ ሲያፈገፍጉ አይቶ ፈሪ ሁላ እንዴት ትሸሻላችሁ “እኔ እንዴት እንደምሞት ለንጉሡ ሄዳችሁ ንገሩ”
በማለት ፈረሱን በአለንጋ አስነስቶ በግልቢያ በሚዘንበው የመድፍ ጥይት መካከል ገባ እሱን ሲያይ ሁሉም እየሮጠ ተከታትሎ ገብቶ ከመድፈኞቹ ጋር ተጨፋጭፎና ገድሎ መድፈኞቹን ማረከ፤
የገበየሁ ሬሳ ከወደቀበት ቦታ የኛዎቹም የጀግኖች ሬሳ አብሮ በመውደቅ አከበረው፤ ይልና ጆቫኒ ቴዶኒ በዚያን ሰሞን ምርኮኛ በመሆን በንጉሠ ነገሥቱ ሠፈር ሳለ በዓይኑ እንዳየው ስለ ገበየሁ ሰው ሁሉ ያለቅስ ነበር ከዕለታት አንድ ቀን ከሞት የተረፈው በየአለቃው ተሰልፎ በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ሲያልፍ፤ የፊታውራሪ ገበየሁ የተጫነ በቅሎ የገዛ ወጣት ልጁ ተቀምጦበት ሲያልፍ አፄ ምኒልክ አይተው ማልቀሳቸውን ጽፏል።
ፊታውራሪ ገበየሁ ገና ወደ አድዋ ሲዘምቱ ተናዘውም ነበር፤
“ስሸሽ ከኋላዬ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ እኔ እንደ አባቶቼ አይደለሁምና ወግ አይገባኝም ከፊት ለፊቴ ስፋለም ከወደቅሁ ግን እሬሳዬን (አጽሜን) ትውልድ ቦታዬ ውሰዱልኝ”
ብለው ነበር። እንዳሉትም ሆነ።
አድዋ ላይ ለሀገራቸው ነፃነት ሲዋጉ በጀግንነት የወደቁት ፊታውራሪ ገበየሁ(አባ-ጎራ) አድዋ ሥላሴ ተቀብረው ከቆዩ በኋላ አጽማቸው ወደ አምባላጌ ጊዮርጊስ ተወሰደ።
በቃል ኪዳናቸው መሠረት ከሰባት ዓመት በኋላ አጽሙ በትውድል አካባቢያቸው በአንጎለላ ኪዳነ ምህርት ቤተክርስቲያን አረፈ።
ያ ጎራ ገበየሁ ምን አሉ ምን አሉ
ያ ትንታግ ታፈሰ ምን አሉ ምን አሉ
እነ ደጃች ጫጫ ምን አሉ ምን አሉ
ተማምለው ነበር ከጦሩ ሲገቡ
ሀገሩን አቅንተው አድዋ ላይ ቀሩ።
#ክብር #ለሚገባው #ክብር #እንስጥ!!!
#ኢትዮጵያ #ለዘላለም #ትኑር!!!
Filed in: Amharic