>
5:18 pm - Friday June 15, 2446

የብሔር ሚድያ + የብሔር ፖለቲካ = ሰኔና ሰኞ (በለው አንለይ)

የብሔር ሚድያ + የብሔር ፖለቲካ = ሰኔና ሰኞ

በለው አንለይ

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞትና የአሟሟቱ ጉዳይ ዛሬም ድረስ ቀዳሚ ዜና ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ የአርቲስቱን በግፍ መገደል ተከትሎ የደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ሌላው መነጋገሪያ ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰውን ጥፋት አየር ላይ ሆነው ስለመሩት መገናኛ ብዙኃን ግን ብዙ እየተባለ አይደለም፡፡ በቅጡ ያልተገሩ ብሔር-ተኮር ሚዲያዎች ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በሃጫሉ ሞት የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ ሲባል እንደ ኦኤምኤን (OMN)፣ ድምፀ ወያኔ (DW) እና ትግራይ ቴሌቪዥን የመሳሰሉ መገናኛ ብዙኃን በተልዕኮ፣ በይዘትና በአጀንዳ ቀረጻ ዙሪያ ተቀናጅተው፣ ተናበውና ተመጋግበው ሰርተዋል፡፡ ኦኤምኤን በመንግስት ህጋዊ እርምጃ ወዲያውኑ ሲዘጋ፣ ህወሃት የሚዘውራቸው መገናኛ ብዙኃን ከሳተላይት እንዲወርዱ እስከተደረገበት እስከ ነሃሴ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ኦኤምኤንን ተክተው፣ የአርቲስቱን የግድያ ወንጀል ነፍጠኛ ብለው ከፈረጁት ከአማራ ህዝብ ጋር በማያያዝ፣ የኦሮሞ ህዝብ ለበቀል እንዲነሳ ያልተቋረጠ ዘመቻ ሲያካሂዱ በገሃድ አይተናል፡፡
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ “ቧ” ብሎ የተከፈተውን የሚዲያ ነጻነት፣ የህዝብን መብትና ጥቅምን በሀሳብ ትግል ከማስከበር ይልቅ አንዳንዶች አመጽ ቅስቀሳ ላይ መሰማራትን መረጡ፡፡ በአቶ ጃዋር ሙሃመድ የተቋቋመው ኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ በሃጫሉ ሞት ማግስት ነሐሴ 24 ቀን 2012 ዓ.ም ሲያስተላልፈው የነበረው የእልቂት መልዕክት በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ሲታወስ የሚኖር አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ በዕለቱ ወጣቶች ቀጥታ ስርጭት ላይ ገብተው በንዴትና በቁጣ ስሜት ይነዙት የነበረው መረን የለቀቀ የጦርነት ቅስቀሳ “ኢትዮጵያን እንደ ሩዋንዳ” ለማድረግ የታቀደ ስራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሚዲያ የሚቀርቡ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች፣ ከዘርና ከሃይማኖት አድልኦ ነጻ፣ ከመሰረተ ቢስ ውንጀላና ስም ማጥፋት ተግባር የራቁ መሆን እንዳለባቸው በህግ ተለይተው የተመለከቱ አድራጎቶች ቢሆንም፣ ህጎች በዚህ ጣቢያ ላይ የማይሰሩ እስኪመስል ድረስ ከሁለት ዓመት በላይ በተመሳሳይ የጥፋት ጎዳና ዘልቋል፡፡ “ከነፍጠኛ ጋር አትጋቡ” … “በእነሱ ቋንቋ ገበያ አትገበያዩ” … እና የመሳሰሉት የጥላቻ ፕሮፓጋንዳዎች በዚህ ጣቢያ ሲተላለፉ መክረማቸውን ልብ ይሏል፡፡
“የነጻነቶች እናት” በመባል የሚታወቀው የአመለካከትና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ ሁሌም ፍጹም ሊሆን ስለማይችል በሌላው ሰው መብት ወይም መሠረታዊ ጥቅሞች ላይ የተመረኮዙ ገደቦች ይኖሩታል:: ሰዎች ሀሳባቸውን የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ የሌሎችን ደህንነትና ሰላም አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ መሆን የለበትም፡፡ በመሆኑም ሀሳብን በነጻነት በመግለጽ መብት ላይ በህግ የተጣለ ገደብ ተፈጻሚነት የሚኖረውና መተርጎምም ያለበት በህዝብ ሰላምና ደህንነት ላይ ሊከሰት ከሚችል አደጋ ጋር በማመዛዘን ነው፡፡ የነጻነት ገደብ ከነጻነት እውቀት የሚመጣ ነው ይባላል፡፡ ነጻነቱን ያላወቀ ኃላፊነቱን አያውቅም እንደ ማለት ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት በጎደለው አካል ስር ሲወድቁ የሚያደርሱት ጉዳት ምን ያህል አውዳሚ እንደሆኑ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በተለይ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የሚተላለፉ የቅስቀሳና የጦርነት መልዕክቶች አንዴ ከተሰራጩ ለማገድ የማይቻልና በፍጥነትና በስፋት ተደራሽ ከመሆናቸዉ አንጻር የሚያደርሱት ጉዳት የከፋ እንደሆነ የሩዋንዳው አር.ቲ.ኤም (RTM) ራዲዮ በዋቢነት ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ በራዲዮና በቴሌቪዥን የሚቀርብን መረጃ ኃላፊነት ከሚሰማው አካል የተላለፈ እውነተኛ መልዕክት አድርጎ የመቀበል ልማድ አለው፡፡
የሚዲያን ነጻነት አስፈላጊ ያደረገው ልዩነት ነዉ፡፡ ልዩነት ደግሞ የሚመጣዉ ከሀሳብና አመለካከት መለያየት ነው:: የሀሳብና አመለካከት ልዩነት ማክበር ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ቢሆንም ሁሉም ዓይነት ልዩነት ሁልጊዜ በተመሳሳይ አረዳድ ይተረጎማል ማለት ግን አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከአገር ደህንነትና ሉአላዊነት በተቃራኒ መቆም ወንጀል እንጂ የሀሳብና አመለካከት ልዩነት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ድምፀ ወያኔ እና ትግራይ ቴሌቪዥን የአገርን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ገሸሽ አድርገዉ ለግብጽ ያዳሉ ዘገባዎችን ሲሰሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የግብጽ ሚዲያዎች “ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ውሃ ሙሌት ለማዘግየት ተስማማች” የሚል ዜና ስለሰሩ ብቻ የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ዜናው ሀሰት ነው ብሎ በይፋ ያስተባበለውን ችላ ብለው የግብጽ ሚዲያዎች ያሉትን እንደ አስተማማኝ ምንጭ (credible source) ወስደው ሲዘግቡ አስተውለናል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ለአሰራር ነጻነትና የተለያዩ አመለካከቶች እንዲስተናገዱባቸው ሲባል የህግ ጥበቃ የሚደረግላቸውን ያህል አገራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥልና ህዝብን ከህዝብ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ ዘገባ ሲያሰራጩ ደግሞ በህግ ይጠየቃሉ፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት በህዝብ መካከል ሁከትና ግርግር ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በነበሩ መገናኛ ብዙኃን ላይ እየወሰደ ያለዉ የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር የሚደገፍ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙኃኑ በፈጸሙት ወንጀል፣ ባስተላለፉት የሀሰት ዘገባ በህግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከሃጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ በድምፀ ወያኔና ትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢዎች ላይ ሲተላለፉ የነበሩ አብዛኛዎቹ ዘገባዎች ምንጫቸው “ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ሰዎች በስልክ እንደተናገሩት” በሚል ሽፍንፍን የተሞሉ ነበሩ፡፡ እንዲህ ዓይነት ዘገባዎች ሲደጋገሙ እውነተኛነታቸው ያጠራጥራል፡፡ በዚህ ጊዜ መገናኛ ብዙኃኑ ለዘገባቸው ምንጭ የሆኑ ሰዎችን ያሳውቁ ዘንድ በፍ/ቤት ትዕዛዝ መገደድ ይችላሉ:: በህጉ አግባብ መሰረት መገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡላቸውን አስተያየቶች ባለቤቶች የማወቅ ግዴታ ስላለባቸው የአስተያየቱን ባለቤት አላውቅም የማለት መብት የላቸውም፡፡
“ባድሜን እንደ ምክንያት” እንዲሉ የሃጫሉን ሞት ሰበብ አድርገው የሩዋንዳን የዘር ፍጅት ኢትዮጵያ ላይ እንዲደገም ጥሪ ሲያደርጉ የነበሩ መገናኛ ብዙኃን ከጀርባቸው መንግስትና ህዝብ የማያውቀዉ ድብቅ አጀንዳ ይዘው ሲሰሩ እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ እንደሚታወቀው ኦኤምኤን እና ድምፀ ወያኔ የተመዘገቡት የንግድ መገናኛ ብዙኃን (commercial media) ተብለው ነዉ፡፡ ይህ ሲባል ዋና የገቢ ምንጫቸው ማስታወቂያ ነው ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተለይ ኦኤምኤን ይህ ነው የሚባል ማስታወቂያ የሌለው ሲሆን ወጪዎቹን (የስቱዲዮና የቢሮ ኪራይ፣ የሰራተኛ ደመወዝ) የሚሸፍነው ከየት በተገኘ ገንዘብ እንደሆነ ግራ ያጋባል፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ “በውጭ ኃይሎች ጉርሻ የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎች” ሲሉ የገለጹበትን አግባብ እዚህ ላይ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡
የአርቲስት ሃጫሉ ሞት በአገራችን የሚገኙት ብሔር-ተኮር ሚዲያዎች ራሱን የቻለ የአሰራርና የህግ ማዕቀፍ ሊዘጋጅላቸው እንደሚገባ ያስገነዘበ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል:: የብሔር ሚዲያዎች የተሳትፎ መጠን ከየት እስከ የት መሆን እንዳለበት አንድ “የሃጫሉ ህግ” የተሰኘ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ያለብን ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ብሔር-ተኮር ሚዲያዎች ልክ እንደ ማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን በተወሰኑ ይዘቶችና ጉዳዮች (እንደ ባህል እና ልማት) ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚያደርግ አስገዳጅ ህግ እስካልወጣ ድረስ ከሰሞኑ እንደተደረገው የተወሰኑ ሚዲያዎችን በመዝጋት ብቻ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አይቻልም፡፡ የብሔር ሚዲያዎች ለተሻለ ኅብረተሰብ ግንባታ፣ ልማትና ዕድገት ውጤታማ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ህጋዊ መንገድ መቀየስ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ አንዳንዶች የጉዳዩን አጣዳፊነት “ሳይቃጠል በቅጠል” በሚል ተርጉመውታል፡፡
የጋዜጠኝነት ሳይንስም እንደሚለው፤ በታሪክም እንደምናውቀው ዘርና ብሔርን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ መገናኛ ብዙኃን የጋዜጠኝነትን መሠረታዊ መርሆዎች ተከትለው ይሰሩ ዘንድ የተቋቋሙበት ምክንያት፣ ዓላማና ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አይፈቅድላቸውም፡፡ አገራዊ አጀንዳ ቀርፀው የጋራ ዓላማ፣ ጥቅምና መግባባት ላይ መስራት ቀዳሚ ጉዳያቸው አይደለም:: የብሔር ሚዲያዎች በተፈጥሯቸው ወገንተኛ ናቸው፡፡ ውግንናቸው ደግሞ ቆመንለታል ለሚሉት ለአንድ ወገን ብቻ ነው::  ከዚህ አንጻር በአገራችን የሚገኙት ብሔር-ተኮር ሚዲያዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አፈ-ቀላጤነት የተለየ ባህሪ አይስተዋልባቸውም:: በእንደዚህ ዓይነት አሰራርና አደረጃጀት ውስጥ ሚዲያ የተቆጣጣሪነት ሚና (watchdog role) መጫወቱ ቀርቶ ኃላፊነቱ ፖለቲካውን መቆጣጠርና መምራት ይሆናል፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች ፖለቲካውን ሲቆጣጠሩና ሲመሩ ደግሞ ትርፉ ምን እንደሆነ በግላጭ ታይቷል፡፡ የልዩነትና የአክራሪነት ምክንያት ነው እየተባለ በሚጠቀሰው የብሔር ፖለቲካ ላይ የብሔር ሚዲያ ሲታከልበት ውጤቱ ሰኔ እና ሰኞ እንደሚሆን የመጣንበት መንገድ ያሳያል፡፡

Filed in: Amharic