>

ባንዲራው ህገ ወጥ አይደለም! (የትነበርክ ታደለ)

ባንዲራው ህገ ወጥ አይደለም!

የትነበርክ ታደለ

ከለውጡ ወዲህ በየአጋጣሚው ህዝብ በአደባባይ በሚወጣባቸው ጊዝያት ሁሉ የተለያዩ አርማዎች ሲውለበለቡ ይታያሉ። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን እንደ ገለጹት “ለመለወጥ ፍላጎት የሌላቸው ተቸንካሪዎች” በተለይም አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩን አርማ እያሳደዱ በብስጭት ሲሰበስቡ ሲላቸውም ሲቀዳድዱ ይታያል። ይህ ህገ ወጥነት እንጂ ህግ አስከባሪነት አይደለም።
ምክኒያቱም እነዚህ ብስጩ የፖሊስ አባላት እልሀቸውን የሚወጡበት አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ባንዲራ የኢትዮጵያ የቀድሞ መለያ ከመሆኑም ባሻገር አሁን ያለውም ቢሆን ሰማያዊ ኮከብ ከመጨመሩ በቀር ሙሉ በሙሉ የእነዚሁ ቀለማት ቅምር ነው።
ይህ ሰንደቅ አላማ ህገ ወጥ አይደለም። አልተባለም ሊባልም አይችልም። ህዝብ ከታሪኩ ጋር የተሰናሰለን አርማ መያዝ ፈጽሞ ወንጀል ወይም ክልክል ሊሆን አይችልም።
ህግ አስፈጻሚ ነን ባይ ለውጥን መቀበል ተስኗቸው የሚያሰነክሉ የፖሊስ አባላት የሚሰሩትን አያውቁትም። ይልቁንም ሆን ብለው ህዝብ ላይ ትንኮሳ በመፈጸም ግጭት መቀስቀስ ነው አላማቸው እንጂ የሚደግፋቸው አንድም የህግ መሰረት የለም። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን ከሰው እጅ አሳዶ ለመንጠቅ የሚያጠፉትን ጊዜ ወንጀልን መከላከል እንዲሁም ህዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ አካባቢውን በመቃኘት ቀና ትብብር ቢያደርጉ ከሚከፈላቸው የላባቸው ደሞዝ በላይ የህዝብንም ፍቅርና ከበሬታ ያገኙበታል። ይህ ባይሆንም ግን ያልተጻፈ ህግ ለማስከበር ሲጋጋጡ በህዝብ ፊት ትዝብት ከማትረፍ ይድናሉ! ባንዲራው ህገ ወጥ አይደለም!!
Filed in: Amharic