>
1:39 pm - Tuesday June 6, 2023

አሰቃቂውን የግፍ ተግባር ሳትጠየፉ የወንጀሉ መጠሪያ እንቅልፍ ለነሳችሁ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አሰቃቂውን የግፍ ተግባር ሳትጠየፉ የወንጀሉ መጠሪያ እንቅልፍ ለነሳችሁ…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

አዎ በዘር እና በሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተፈጽሟል። ይሄን ጸሃይ የሞቀው ወንጀል በማስፈራሪያ እና በመግለጫ መሸፈን አይቻልም!!!
1ኛ/ በኃይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በተፈጸሙባቸው አካባቢዎች የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ክርስቲያኖች፤ በተለይም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዬች የጭፍጨፋው ሰለባ ሆነዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የጥቃቱ መስፈርት ኃይማኖት ስለነበር ከሁሉም ብሔር ያሉ ክርስቲያኖች ተጠቅተዋል።
2ኛ/ በብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ደግሞ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች፤ ሙስሊሞችን ጨምሮ የተለያዩ ጏይማኖት ተከታዬች የጭፍጨፋው ሰለባ ሆነዋል።
የተበዳዬቹ በጎሣም ሆነ በኃይማኖት መሰባጠር ወንጀሉን የዘር ማጽዳት ወይም የዘር ፍጅት ከመባል አያስቀረውም። በኦሮሚያ ክልል ሹማምንትም ሆነ በአንዳንድ ግለሰቦች ስለወንጀሉ ባህሪ እየተገለጸ ያለው የተምታታ እና ሆን ተብሎ ጉዳዩን አቅጣጫ ለማሳት የሚደረጉ ገለጻዎች ሦስት ነገሮችን መነሻ ያደረጉ ናቸው።
1ኛ/ ተበዳዬቹ የአንድ ብሔር ሰዎች ወይም ኦሮሞ ያልሆኑ ብቻ አይደሉም። ኦሮሞዎችም ተገድለዋል የሚል ነው።
አዎ ክርስቲያን ኦሮሞዎች በኃይማኖታቸው ብቻ ተለይተው በአክራሪ ሙስሊምች ተገድለዋል። ገዳዬቹ በኃይማኖት አንድ ይሁኑ እንጂ የተለያዩ ብሔር ሰዎችም ሊሆኑ ይችላሉ።
2ኛ/ ተበዳዬቹ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ አይደሉም ሙስሊሞችም የጥቃት ሰለባ ሆነዋል የሚል ነው።
አዎ በብሄር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በተፈጸመባቸው ስፍራዎች ሙስሊም አማራ ወይም ሙስሊም ጉራጌ ጭምር የጥቃቱ ሂላማ ተደርገዋል። ለእነዚሆቹ አጥቂዎች መሴፈርቱ ኦሮሞ መሆን አለመሆን ነው። በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉ አጥቂዎች ሁሉም ኦሮሞዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ኃይማኖታቸው ደግሞ የተለያየ ሊሆን ይችላል።
በሁለቱም መስፈርቶች የተፈጸሙት ጥቃቶች ማንነትን መነሻ ያደረጉ ናቸው። አንዱ ኃይማኖትን፤ ሌላው ዘርን።
3ኛ/ ሌላው የሚነሳው መከራከሪያ የዘር ፍጅት የሚለውን አገላለጽ ብዙዎች ካለማወቅ፤ አንዳንዶች ደግሞ በሕግ ሙያ ስመ ጥር ሆነውም በጎሰኝነት ስሜት ታውረው፤ አንድ ብሔር ሙሉውን ተሰብስቦ በሌላው ላይ የፈጸመው ጥቃት በማስመሰል፤ የኦሮሞ ሕዝብ ማንንም አላጠቃም። ጥቂቶች የፈጸሙት ድርጊት ደግሞ የዘር ፍጅት ሊባል አይገባውም። የሚል ከቅን ልቦና የወጣ እና ፍሬ ጉዳዩን ሆን ብሎ ያንሻፈፈ መከራከሪያ ያነሳሉ።
በመጀመሪያ ደረጃ የኦሮሞን ሕዝብ በጥቅል ለዚህ አስነዋሪ ተግባር ተጠያቂ የሚያደርግ ሰው ካለ እሱ እራሱ ነውረኛ ነውና ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል። እንደ አግባቡም ቀሕግ ሊጠየቅም ይችላል።
አጥፊዎቹን በደንብ ለይቶ መግለጽ እና አላማቸውን በግጽ ማስቀመጥ ይህን ንትርክ ከመፍታትም አልፎ የወንጀሉን አይነት ለማወቅ ይረዳል። ወንጀሉን ለመደባበቅ የሚጥሩትንም አደብ ግዙ ለማለት ያመቻል።
የጨፍጫፊዎቹ ማንነት፤
1ኛ/ አጢፊዎቹ ቁጥራቸው በሺዎች የሚቆጠር፣ በዕድሜ ወጣቶች የሚበዙት፣ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች፣ የፖለቲካ ግብ ያላቸው፣ በደንብ የተደራጁ፣ አክራሪ ብሔረተኞች እና የኃይማኖት ጽንፍ የረገጡ ናቸው። እነዚህ ቡድኖች ኦሮሞን ወይም የትኛውንም ኃይማኖት አይወክሉም፤
2ኛ/ አጥቂዎቹ የሚገድሏቸውን ሰዎች ስም  እና የሚያቃጥሉትን ቤት ዝርዝር ቀድመው አዘጋጅተው የያዙ፣ ነፍጠኛ ከክልላችን ይውጣ፣ አማራ እና ክርስቲያን እኛ ክልል አይኖርም የሚል መፈክር ያሰሙ የነበሩ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የገደሉትን ሰው አካል ቆርጠው እና ቤት እያቃጠሉ አላህ ዋአክበር ይሉ የነበሩ፣ ዘር እና ኃይማኖት እየጠሩ ጥቃት ይፈጽሙ የነበሩ፣ ክርስቲያኖችን በጏይማኖታቸው፣ ሙስሊሞችን በዘራቸው ያጠቁ፣ ኢላማ ያደረጉትን ቤት ብቻ እየለዩ ይዘርፉና ያነዱ እንደነበሩ፣ የብሔር ጥቃት ይፈጽሙ የነበሩት ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎችን ብቻ ያጠቁ እንደነበር ከበቂ በላይ ማስረጃ ተገኝቷል።
3ኛ/ በወንጀል አድራጎት የአጥፊው ሰው ሃሳብ፣ ዝግጅት እና አድራጎት የወንጀሉን አይነት እና ባህሪ ለመወሰን ወሳኝ ነገሮች ናቸው። አድራጊዎቹ ነፍጠኛ ብለው የሚያስቡትን የአማራ ተወላጆችን፣ ኦሮሞ ያልሆኑ ሌሎች ኢትዬጵያዊያንን ኢላማ ማድረጋቸውን ባደባባይ ገልጸዋል። በOMN  ጭምር በይፋ አውጀዋል፣ ስም ዝርዝር አዘጋጅተዋል፣ ከመዘጋጀትም አልፈው የአውሬነት ተግባራቸውን በተዘጋጁበት ልክ ፈጽመዋል። ሃሳባቸው በዝግጅት ተደግፎ ውጤቱም ታይቷል።
ገና ለገና ወንጀሉ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚያስጠይቀው የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈረጁ እኛንም ያስጠይቀን ይሆናል ከሚል ስጋት ተነስተው የክልሉ ባለስልጣናት ነገሮችን ለማደባበስ እያደረጉ ያለው ጥረት እና የወንጀሉን ስም አትጥሩ የሚሉ ዛቻ እና ማስፈራሪያዎችን ከወዲሁ ማዥጎድጎድ መጀመራቸው ከወዲሁ የፍትህ ነገር ደህና ሰንብት  እንድንል አድርጎናል። የወንጀሉ መገለጫ ከወዲሁ እንቅልፍ የነሳቸው የክልሉ ባለሥልጣናት መረጃዎችን የመደበቅ ወይም እንዳይታወቁ የማድረግ ዝንባሌዎችም ይታዩባቸዋል። ለዚህም ነው ገለልተኛ የሆነ አካል ሳይውል ሳያድር ተሰይሞ ጉዳዩን ያጣራ የምንለው።
አጥፊዎቹን፣ የጥፉት ተባባሪዎቹን፣ ጥፋቱን ለመደበቅ ወይም ሌላ ስም ለመስጠት የሚጥሩትን የመንግስት አካላት ጭምር የምንፋረድበት የሕግ መድረክ መፈለግ የግድ ይላል።
ፍትህ የዘር እና የኃይማኖት ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ወገኖቻችን!
Filed in: Amharic