>
5:09 pm - Tuesday March 3, 0736

ለንጽጽር የማይቀርበው የነገስታቱና የገዳው ስርአት...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ለንጽጽር የማይቀርበው የነገስታቱና የገዳው ስርአት…!!!

አቻምየለህ ታምሩ

 

* ኦሮምኛ የተስፋፋበት የገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲና አማርኛን አስፋፋ በተባለው የኢትዮጵያ ነገሥታት የቋንቋ ፖሊሲ መካከል ያለው ግልጽ ልዩነት!
* የገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ «ኦሮምኛ የሚናገር “ቢርመዱዳ እንጡቂና” ኦሮምኛ የማይናገር “ዲና በሌሣ”» የሚል እንደነበር “የገዳ ስርአት የቋንቋ ፖሊስ ትናንት እና ዛሬ” በሚል ርእስ ባሰፈርኩት ጽሁፍ አመላክቻለሁ። «ኦሮምኛ የሚናገር “ቢርመዱዳ እንጡቂና” ኦሮምኛ የማይናገር “ዲና በሌሣ”» የሚለው የገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ ትርጉም «ኦሮምኛ የሚናገር ወገናችን ነው ይገብር፤ ኦሮምኛ የማይናገር ጠላታችን ነው ይጥፋ”» እንደ ማለት ነው!
 
 ይህ የገዳ ወታደራዊ ሥርዓት  የቋንቋ ፖሊሲ ኦሮምኛ ከሚናገረው ማኅበረሰብ ውጭ ያለውን ከሀያ ስምንት በላይ የኢትዮጵያ ነገዶች ቋንቋ በተሳካ ሁኔታ ያጠፋ የቋንቋ ፖሊሲ ነው።
ከገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ በተቃራኒ  የቋንቋ ፖሊሲ የነበራቸው የኢትዮጵያ ነገሥታት በተለይም ኦሮሞ ኢትዮጵያን ከመውረሩ ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት ከነበረው  ከዛጉዌ  ዘመነ መንግሥት ጀምሮ  እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ ድረስ የነበራቸው  የቋንቋ ፖሊሲ ቋንቋ የሚያጠፋ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን አፋቸውን ከፈቱበት ቋንቋ በተጨማሪ ከዳር እስከ ዳር የሚግባቡበትን አማርኛን በተደራቢነት እንዲያውቁ  የሚያደርግ፣ የተለያዩ የኢትዮጵያ ነገዶች የነበራቸውን ቋንቋ የሚያጠፋ ሳይሆን በነበራቸው ቋንቋ ላይ  በተደራቢነት  እሴት የሚጨምር ስርዓት ነበር።
በሁለቱ የቋንቋ ፖሊሲዎች መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል  ተቃራኒ ነው። አንዱና ዋናው ልዩነት የገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ የአንድን ነገድ ማንነት ቋንቋ  ብቻ  ሳይሆን ባሕልና ማንነቱን የሚያጠፋ ሲሆን የኢትዮጵያ ነገሥታት የቋንቋ ፖሊሲ ግን በአንድን ነገድ ማንነት፣ ቋንቋና ባሕል ላይ ጭማሪ የሚያደርግ ነበር።
ሁለተኛው ልዩነት በገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ አንድ ሰው የራሱን ቋንቋና ባሕል ትቶ ኦሮምኛ ብቻ ለመናገር ካልፈቀደ ያለው ብቸኛ እድል መገደልና መጥፋት ነው። ባሕሉንና ቋንቋውን ትቶ ኦሮምኛ መናገር ቢፈቅድ እንኳ  በገዛ ርስቱ ገርባ  ይሆናል እንጂ ባለ ርስት ወይም  ባለ መሬት  እንኳ አይሆንም። ይህ ብቻ ሳይሆን የአመጋገብ ሥርዓቱም ይለያል። ገርባ እንደ ኦሮሞ ጥሩ ምግብ መብላት አይፈቀድለትም። ኢኔሪኮ ቸሩሊ «Folk-literature of the Galla of Southern Abyssinia» በሚል በ1914 ዓ.ም. ባሳተመው ጥናቱ ገጽ 140 ላይ  እንደነገረን በበአል ጊዜ ለኦሮሞው ጠቦት ወይም ኮርማ ሲታረድለት ለገርባው ግን ይታረድለት የነበረው ያረጀችና የነጠፈች ላም ተፈልጋ ነው። ቸሩሊ ጨምሮ እንደነገረን የኮርማ ስጋ የበላ ገርባ ቢኖር ይታረዳል።
በገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ ቋንቋውን እንዲያጣ የተደረገ ገርባ መብት የለውም ብቻ ሳይሆን፣ ባለቤቱ በፈለገው ጊዜ የሚሸጠው ባሪያ ነበር። ይህን እውነት የኦሮሞ ብሔርተኛው መሐመደ ሐሰን ከሰላሳ ዓመታት በፊት <<The Oromo of Ethiopia: A History, 1570-1860>> በሚል ባሳተመው መጽሐፉ ከ124 -127  ባቀረበው ሀተታ ነግሮናል።
ሰው ያለባሕሉ፣ ያለአባቱ፣ ያለ ቋንቋው ምሉዕ አይደለም። አካል ነው፤ ስጋ ነው። የኦሮሞ አባገዳዎች «ኦሮምኛ የሚናገር “ቢርመዱዳ እንጡቂና” ኦሮምኛ የማይናገር “ዲና በሌሣ”» በሚለው የቋንቋ ፖሊሲያቸው የሰውን ማንነት ሲያጠፉ አካሉን እንጂ ሰውነቱን አልፈለጉም። ሰው ስጋው ብቻ ከቀረ ከጋማ ከብቶቻቸው አንዱ ይሆናል። የገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ  ኦሮሞ ያልሆነውን  ከጋማ ከብቶች አንዱ የሚያደርግ ፖሊሲ ነው።  አባገዳዎች ሲስፋፉ ሰውን ለጦርነት ሲማግዱና በባርያ ንግድ ሸቀጥ አድርገውት የኖሩት ቋንቋውን በማጥፋት እንዲህ አድርገው አዋርደውት ነው። ከደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም በጊቤ የኦሮሞ ባላባቶችና በወለጋ ሞቲዎች  ኤክስፖርት የሚደረጉ ባሪያዎች ኦሮምኛ ተናጋሪ የነበሩበትም ምክንያት ይህ ነው። የአባገዳዎች ጭካኔ የገርባቸውን ልጆች ነጥቀው በሞጋሳ ቤታቸው ውስጥ ካሳደጓቸው በኋላ ጭቡ አድርጎ በባርነት እስከመሰጥ ድረስ ነው።
በኢትዮጵያ መንግሥታት የቋንቋ ፖሊሲ እንደዚይ አይነት ሰውን የሚያዋርድ ጭካኔ ኖሮበት አያውቅም። የኢትዮጵያ ነገሥታት የቋንቋ ፖሊሲ ኢትዮጵያውያን በተደራቢነት እየተናገሩ በጋራ ይግባቡበት የነበረውን ቋንቋ ብሔራዊ ቋንቋ አድርጎ የዘረጋና ኢትዮጵያውያን ተምረውት በተደራቢነት እንዲናገሩትና እንዲገለገሉበት ያደረገ እንጂ የአፍ መፍቻ ቋንቋን በመደምሰስ አንድ ቋንቋ ብቻ እንዲናገሩ የሚያስገድድ፣ የሰውነት ደረጃ የሚወጣና ቋንቋ የመለያ መሳሪያ የሚያደርግ አልነበረም።
ባጭሩ በገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲና አማርኛን አስፋፋ በሚባለው የኢትዮጵያ ነገሥታት የቋንቋ ፖሊሲ መካከል ያለው ትልቅ ነው። በገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ ኦሮምኛ የተስፋፋው ኦሮምኛ የማይናገረውን ማኅበረሰብ ባሕል፣ማንነትና ቋንቋ በተሳካ ሁኔታ አጥፍቶ ሲሆን አማርኛ ግን የተስፋፋው አማርኛ በማይናግረው ማኅበረሰብ ባሕል፣ማንነትና ቋንቋ በላይ ጭማሪ ሆኖ ነው።
በመሆኑም የኦሮሞ አባ ገዳዎች «ኦሮምኛ የሚናገር “ቢርመዱዳ እንጡቂና” ኦሮምኛ የማይናገር “ዲና በሌሣ”» በሚለው የቋንቋ ፖሊሲያቸው እየተመሩ ቋንቋና ባሕላቸውን ላጠፉባቸው፣ መሬታቸውን ነጥቀው ገርባ ላደረጓቸው፣ ባሪያ አደርገው ለሸጧቸው ከሀያ ስምንት በላይ የኢትዮጵያ ነገዶች በይፋ ይቅርታ ሊጠይቁና ካሳ ሊክሱ ይገባል።
Filed in: Amharic