>

ክቡርነትዎ  ቢያንስ ጭፍጨፋውን በግልጽ ለማውገዝ፤ ይቅርታ ለመጠየቅ፤ "ብሔራዊ የሀዘን ቀን" ለማወጅ ምን ያዘዎ??? (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

ክቡርነትዎ  ቢያንስ ጭፍጨፋውን በግልጽ ለማውገዝ፤ ይቅርታ ለመጠየቅ፤ ብሔራዊ የሀዘን ቀን” ለማወጅ ምን ያዘዎ???

ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ

 

 
* “ስለ ጉዳዩ ለማንሳትም በሚያሳፍር መንገድ ሰዎች ሞተዋል!!!”  ዶ/ር አብይ አህመድ
* “ተገድለዋል! የዘር የሀይማኖት ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል!” ላለማለት መቀባባት መሆኑ ነው
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከመያዶች ጋር በነበራቸው ውይይት፣
“ኦሮሚያ ውስጥ መቶ ምናምን ሰው ለመናገርም፣ ለመስማትም፣ ስለ ጉዳዩ ለማንሳትም በሚያሳፍር መንገድ ሞተዋል። ይህንን ነገር ደጋግሞ ማንሳቱም በጣም ይከብዳል” ብለዋል።
የእኔ ጥያቄዎች፣
፩:- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትት በአሰቃቂ ሁኔታ ስለተገደሉና ሰለ ጠፋ ነብስ በመሆኑ “መቶ ምናምን ስንት ነው?” 101? 150? 199?… ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክለኛ የሟቾች ቁጥር አለዎት ወይ?
፪: – ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆነ መንግስቶት ( በተለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት) ለዚህ አሳፋሪ ድርጊት ለምን በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ተሳኖት?…
በዚህ አጋጣሚ እርስዎ ማንም ሳይቀድሞት በጥልቅ ማዘኖትን የገለጹላት የሊባኖስ/ ቤይሩት ጠቅላይ ሚኒስትርና ካቢኔ ስልጣናቸውን ሙሉ ለሙሉ መልቀቃቸው የአለም መገናኛ ብዙሃን በመዝገብ ላይ ናቸው። አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ እርስዎ ስልጣን መልቀቅ አለቦት የሚል አንዳችም እምነት ባይኖረኝም ቢያንስ የአቶ ሽመልስ አብዲሳ የክልል ካቢኔ ሪዛየን እንዲያደርጉ ማስገደድ ነበረቦት። ይህን ቢያደርጉ ያለ አንዳች ጥርጥር አዲሱ የኦሮሚያ ካቢኔ ” ሽሜን ያየ በስልጣን አይቀልድም!” በማለት ዜጐችን አክብሮ መስራት ይጀምር ነበር።
፫: ጠቅላይ ሚኒስትሩ  “ለመናገርም፣ ለመስማትም፣ ስለ ጉዳዩ ለማንሳትም በሚያሳፍር መንገድ ሞተዋል” ብለው የገጹላቸውን የሰማዕታት ቤተሰቦች በአካል በመገኘት ለማጽናናት ምነው ከበዶት? “ብሔራዊ የሀዘን ቀን” ለማወጅ ምነው ከበዶት? የአንድ አመት እድሜ የሚኖረው”መልሶ ማቋቋሚያ ኮሚሽን” ለማቋቋም ምነው ልብዎ አልፈቅድ አለ?
Filed in: Amharic