>

በፀሀይ ፍጥነት ከባለፀጋነት ወደ ድህነት በደግነት...?!?  (በስንታየሁ ሀይሉ)

በፀሀይ ፍጥነት ከባለፀጋነት ወደ ድህነት በደግነት…?!?

 (በስንታየሁ ሀይሉ)

የሚወዷቸው የሚቀርቧቸው ያሳደጓቸው ልጆች ሁሉ በአንድ ቃል “እዳዬ” እያሉ ይጠሯቸዋል።
ጥቅምት 10 ቀን 1928 ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ ጎፌ ሄዩ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ወሰኔ ብሩ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ ሸበል በተባለች መንደር ወ/ሮ አበበች ጎበና(እዳዪ) ተወለዱ።
 ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረሯን ተከትሎ በነበረው ጦርነት የወራት ጨቅላ እያሉ ወላጅ አባታቸው ሞቱ።  11 ዓመት ሲሆናቸው በቤተሰብ ግፊት ወደ ትዳር ቢይዙም በወቅቱ በትዳር መኖርን ጠልተው ወደ እናታቸው ቤት ሸሽተው ቢሄዱም “እንዴት ታዋርጅናለሽ” በማለት ወላጅ እናታቸው መልሰው ለባላቸው ይሰጧቸዋል። ባላቸውም በር ዘግተው በጠባቂ  ከቤት ቢያኖሯቸውም የሸፈተን ልብ መመለሻ የለውምና በውድቅት ሌሊት የደሳሳዋን ጎጆ የሳር ጣራ ፈልቅቀው አመለጡ።
መድረሻቸውን ሳያውቁ ቀን ቀን እየተደበቁና ሌሊት በእግራቸው ለ3 ቀን ያህል ተጉዘው በመጨረሻም የጭነት መኪና ተሳፍረው መሀል አዲስ አበባ ፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የዛሬው እሳት አደጋ መስሪያ ቤት አጥር ስር ተቀመጡ።
ወ/ሮ አበበች ጎበና ለአዲስ አበባ እንግዳ እንደመሆናቸው አጥር ስር ተቀምጠው ቀኑ ቢጨልምም በዘመኑ የተከበሩ ታላቁ ሰው አቶ አስራት  በብዙ ሰው ታጅበው ምሽተን ሲዘዋወሩ የ11 ዓመት ጉብል የሆኑትን የሸዋ እንግዳ ወ/ሮ አበበች ጎበናን ካዩ በኋላ ግን አልፈው መሄድ አልቻሉም።  አቶ አስራት ቤት ቀርበው አናግረዋቸው ይዘዋቸው ወደቤት በመሄድ እንደ ልጅ እየተንከባከቡ አሳደጓቸው።
ክብርት አበበች ጎበና የእንግሊዝ ሀገር የትምህርት እድል አግኝተው በህመም ምክንያት ሎንዶን ባይሄዱም በአዋሳ ከተማ ትምህርታቸውን ተከታትለው በእህል ንግድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ሠርተዋል።
የምንኩስና ህይወትን እንጂ ድጋሚ ትዳር የመመሥረት ፍላጎት ባይኖራቸውም በቤተዘመድ ግፊት ዳግም ጥሩ ትዳርና ቤተሰብ መስርተው የአብራካቸውን ክፋይ ሳያገኙ በትዳር የተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩ ዓመታትን አሳልፈዋል።
በመስከረም 21 ቀን 1972 ዓ.ም የጊሸን ማርያም የንግስ በዓል ለማክበር ወደ ወሎ ክፍለሀገር በጉዞ ላይ እያሉ የወቅቱን ረሀብ ተከትሎ ሞት ከፊታቸው የተደቀነባቸውን ሁለት ሕፃናትን ያገኛሉ። አጋጣሚው ከባድና ፈታኝ ቢሆንም በወቅቱ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ያገኟቸውን ሕፃናት ይዘው ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ።
ምንም እንኳ በእጃቸው ሁለት ህፃናትን ብቻ ይዘው ቢመለሱም በልባቸው ብዙ አስበው ነበርና የሕፃናቱን ቁጥር ከሁለት ወደ ሦስት ከሦስት ወደ አራት እያሳደጉ በአንድ ዓመት ውስጥ ሃያ አንድ አደረሱት።
 ባለቤታቸው አቶ ከበደ ኮስትሬ መልካም ስራውን ቢወዱትም ነገሩ ግን እየከበዳቸው መምጣቱ በመካከላቸው ፀብ ተፈጥሮ ለሽምግልና ቤተ ዘመድ ተሠባስቦ ያቀረቡት የፀብ ምክንያት በሁሉም ዘንድ “አበበች አብዳለች!” የሚል ስለነበር ባለቤታቸው “አበበች ጠበል ትግባ” የሚል ምክር ያቀርባሉ።
በሽማግሌዎቹና በባለቤታቸው ውሳኔ ያልተስማሙት ዶ/ር አበበች የተቀማጠለውን ህይወታቸውን፣ ሀብታቸውንና ትዳራቸውን ትተው ከቤታቸው ፊት ለፊት በአንዲት የሳጠራ ቤት ውስጥ በስጋ ያልወለዷቸውን ሃያ አንድ ልጆች ይዘው
ከሕፃናቱ ጋር ኑሮን በድፍረት ያለማንም ረዳት “ሀ” ብለው ጀመሩ።
በፀሐይ ፍጥነት ከባለጸግነት ወደ ድህነት በመውረድ ዛሬ ድረስ የዘለቀውንና የሺዎች ቤተሰብ የሆነውን ማዕከል በማቋቋም ለብዙሀን የፍቅር ቤት በመሆን የመጀመሪያውም መንግሥታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል የሕፃናት ማቆያ ድርጅት በዚያው መሠረቱ።
ክብርት አበበች አንድ ወፍጮ ያለውም ሰው እንደ ትልቅ ሀብታም በሚታይበት ዘመን በአዲስ አበባ፣ በሙሎና በፍቼ አካባቢዎች አስራ ሁለት ወፍጮዎች እና ትልቅ የዘመኑ ፋሽን ቪላ ቤትም ቢኖራቸውም ከቤታቸው ሲወጡ ግን ጥቂት ልብስና የወርቅ ጌጣጌጦቻቸውን ብቻ ይዘው ነበር።
ግና ወርቁም ልብሱም እነዚያን ሆድ ብቻ ይዘው የመጡ ሕፃናት ተሸክሞ መዝለቅ ስላልቻለ ሌላ የገቢ ምንጭ መፈለግ ግድ ሆነ። በወቅቱ ለወይዘሮ አበበች ተመራጭና አዋጭ የነበረው ሥራ ቆሎና ንፍሮ እያዘጋጁ መሸጥ ነበር። ይህም ቢሆን በአንድ ሰው እየተከወነ እነዚህን ሁሉ ሕፃናት ማሳደር ስለማይችል ከጣት ጣት ይበልጣል እንዲሉ ትንሽ ከፍ ከፍ ያሉትን ልጆች የተዘጋጀውን ቆሎና ንፍሮ እያዞሩ እንዲሸጡ እስከ ማድረግ ደርሰው ነበር።
ግና በልባቸው ሃሳብ ቆርጠው ነበርና ሁሉንም በድፍረት እየተጋፈጡ በቀጥሉም ጉዞው ግን እጅግ ፈታኝ ነበር። ከአልጋ ወርዶ መደብ መተኛት፤ ሰልባጅ መልበስ፤ ልብሳቸውን ቀዶ ለሕፃናት ሰፍቶ ማልበስ፤ ልጅ አብልቶ ጾም ማደር፤ የሰው ፊት ማየት ከፈተኗቸው መከራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ክብርት አበበች እግር በእግርም የቆሎውን ንግድ ወደ ጠጅ መጣል፤ ከዚያም አልፎ ቅመማ ቅመም በማዘጋጀት ማስፋፋት ይቀጥላሉ። ባልትናቸው እንዲህ እንዲህ እያለ ዛሬ ድረስ በመዝለቅ ስልሳ አምስት ዓይነት የባልትና የምግብ ግብአት ምርቶችን በማምረት ከሁለት መቶ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ምርቶቹም እንደ ሸራተን አዲስ ሆቴል ፤ ፍልውሃ ሆቴል፤ ግዮን ሆቴል፤ ሰሜን ሆቴል፤ ግሎባል ሆቴልና ሌሎችንም መዳረሻ በማድረግ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ከፍቶ ይገኛል።
እንዲህ እንዲህ እያለ ያ ሰፊ ቤተሰብም ባለፉት አርባ ዓመታት ከሦስት ሺ አምስት መቶ በላይ ሕፃናትን የልጅነት ጊዜያቸውን በማቆያው እንዲያሳልፉ በማድረግ ለወግ ማዕረግ አብቅቷል። በአሁኑ ወቅትም በአመት ከ7 ሺ 500 በላይ ሕፃናትን በተለያዩ ፕሮግራሞች በአዲስ አበባ፤ ጉደርና፤ ቡራዮ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ሙሉ ለሙሉ ወጪያቸው የሚሸፈን ያሉ ሲሆን ከዘመድ አዝማድ ጋር እየኖሩ የተወሰነ ድጋፍ ብቻ የሚደረግላቸውም አሉ።
ወይዘሮ አበበች ለልጆች ለየት ያለ ፍቅር ያላቸው እናት ናቸው። በተለይም ለጨቅላ ሕፃናት በዚህም የተነሳ በተቋሙ ሁሌ የሚተገብሩት አንድ ያልተጻፈ ህግ አላቸው። በምንም ምክንያት ዓመት ያልሞላቸው ሕፃናት ወደ ማዕከሉ ከመጡ የመጀመሪያዎቹን ቀናት አልያም ሳምንታት እሳቸው ጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው ብለው እስከሚያምኑ ድረስ የሚቆዩት በእሳቸው እጅ ብቻ ነው።
የክብር ዶ/ር አበበች በታሪካቸው ለአገልግሎታቸው አንድም ቀን ደመወዝ ተቀብለው የማያዉቁ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጌጣ ጌጥና ልዩ ልዩ ስጦታዎች ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ቢበረከትላቸውም አንዱንም ለራሳቸው ጥቅም አውለው አያውቁም። በሺዎች የሚቆጠሩ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከእንግሊዝ ሀገር ወርልድ ቢዝነስ አዋርድ፤ ሁለት ጊዜ የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት፤ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሂዩማኒቲስ የክብር ዶክትሬት፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሞያቸው የላቀ አስተዋጽኦ ስላበረከቱ 50 ኛ የኢዩቤልዩ ሜዳሊያ፤ ማዘር ትሬዛ ኦፍ አፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ የሚጠቀሱ ናቸው።
የክብር ዶ/ር አበበች እርጅና እየተጫናቸውና በየወቅቱ ይገጥማቸው የነበረው ጭንቀት የማስታወስ ችሎታቸውን ቀንሶ የመዘንጋት የጤና እክል ገጥሟቸው ከቤት ለመዋል ቢገደዱም አካላዊ ለውጥ ቢፈጥርባቸውም ለዘመናት የዘለቀውን ርህርሄ የተሞላው የእናትነትነት ፈገግታቸውን ግን ሊነጥቃቸው አልቻለም።
 እዳዬ የሚለው ስም የልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችም የሚጠሯቸው ሁለተኛ ስማቸው ነው።
Filed in: Amharic