>
5:18 pm - Wednesday June 16, 1165

በኦነግ አመራሮች መካከል ትልቅ ውዝግብ ተፈጥሯል....?!? (አለማየሁ አምበሴ)

በኦነግ አመራሮች መካከል ትልቅ ውዝግብ ተፈጥሯል….?!?

አለማየሁ አምበሴ

    • ምክትል ሊቀ መንበሩን ጨምሮ 6 አመራሮች ታግደዋል
• የታገዱት አመራሮች ኦነግን እያደስን እንሄዳለን ብለዋል

በኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሣና  ም/ሊቀመንበሩን ጨምሮ በሌሎች ከፍተኛ አመራሮች መካከል ውዝግብ መፈጠሩ ታውቋል፡፡ ውዝግቡ የተፈጠረው ከሰሞኑ የድርጅቱ ሊቀ መንበር 6 የፓርቲው አመራሮችን ማገዳቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ ድርጅቱን የማዳከም እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በሊቀመንበሩና በሌሎች የፓርቲው አመራሮች መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
ሊቀ መንበሩ የድርጅቱን አመራሮች በፌስቡክ በተሰጠ መግለጫ አግጃለሁ ማለታቸው ከፓርቲው ህገ ደንብ ውጪ የሆነ አካሄድ በመሆኑ ሁላችንም በመደበኛ ስራችን ላይ እንገኛለን ብለዋል፤ አቶ ቀጄላ፡፡
“እንኳን አመራርን ቀርቶ ተራ አባልንም ከፓርቲ ለማባረር ህገ ደንብን መሠረት ተደርጐ ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ “ነገሩ ቀልድ ነው፤ ድርጅቱን ለማዳከምና ለመከፋፈል የተደረገ ጥረት አካል ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
#እኔ ካልመራሁ ምንም ስራ መሠራት የለበትም በሚል ድርጅቱን ለማዳከም ጥረት እየተደረገ ነው፤ ይሄ ደግሞ ህገ ወጥና ስርአት አልበኝነት ነው; ሲሉ የነቀፉት አቶ ቀጄላ፤ #አግደናል የተባለውንም እኛ አንቀበለውም; ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡
የኦነግ ም/ሊቀመንበር አቶ ቢቂላ አራርሶ፣ ቃል አቀባዮቹ አቶ ቀጀላ መርዳሣና አቶ ቶሌራ ኡዳባን ጨምሮ 6 ሰዎች መታገዳቸውን የገለፁት የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሣ በበኩላቸው፤ ጉዳዩ በፓርቲው የህግ ክፍል የተያዘ በመሆኑ ማብራሪያ ለመስጠት አልችልም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፤የኦነግ ም/ሊቀመንበር ቢቂላ አራርሶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኦነግ ከህወሓትም ሆነ ከኦነግ ሸኔ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ጠቁመው፤ በዚህ ሰበብ በአባላቶቻችን ላይ የሚፈፀመው እስራትና ወከባ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በአመራር ውዝግብ ውስጥ መግባቱ በተደጋጋሚ እየተገለፀ ያለው ኦነግ፤ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ #ከህወሓትና ኦነግ ሸኔ ጋር ትሠራላችሁ; የተባሉ ከ600 በላይ አባሎቹና አመራሮቹ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለእስር መዳረጋቸውን አስታውቋል፡፡ ግንባሩ አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታውን ገምግሞ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫው፤ #በህዝብና በመንግስት መካከል ልዩነትን በማስፋት ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚደረግን ጥረት እቃወማለሁ፤ በዚያው ልክ መንግስት ዲሞክራሲያዊ ስርአትን እገነባለሁ ሲል የገባውን ቃል ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል; ብሏል፡፡
የኦነግ ም/ሊቀመንበር ቢቂላ አራርሶ፣ የኦነግ ቃል አቀባዮቹ አቶ ቀጄላ መርዳሣና አቶ ቶሌራ ኡዳባ በጋራ በሰጡት በዚህ መግለጫ፤ ኦነግ የሀገሪቱን ህግ በማክበር ድርጅቱን በማደስ ይበልጥ ዲሞክራሲያዊ፣ አሣታፊና ሁሉን ህብረተሰብ ያቀፈ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑንም አብራርቷል፡፡
በኢትዮጵያ ጉዳይ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በአንድነት ለመስራት በአዲስ እቅድ መነሳቱንም ያስታወቀው ኦነግ፤ አሁን በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ሁነኛ ምክክር ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡ ድርጅቱ ከታጣቂ ሃይሎችና ከህወሓት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው የጠቆመው መግለጫው፤ የኦነግ ሸኔ መዋቅርም በኦነግ እውቅና የሌለው ነው ብሏል፡፡
“ከህወኃት ጋር የመጠራጠርና የስጋት እንጂ የትብብርም ሆነ አብሮ የመስራት ታሪክ የለኝም” ያለው ኦነግ፤ በዚህ ሰበብ ከ600 በላይ አመራርና አባላቱ መታሠራቸው አግባብ እንዳልሆነ በማመልከትም፤ ከእስር እንዲለቀቁና በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ውስጥ በጐ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠይቋል፡፡

ለአገሪቱ ወሳኝ የሆነውን ሠላም ለማረጋገጥ የህዝቡን አንድነት የሚያጠናክር ስራ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሰሩም  ጥሪ አቅርቧል፤ ኦነግ በመግለጫው፡
Filed in: Amharic