>

ይድረስ ለግርማዊ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ንጉሠነገሥት ዘኢትዮጵያ!!! ( በቴዎድሮስ ጸጋዬ - ኢትዮጵያዊ)

ይድረስ ለግርማዊ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ንጉሠነገሥት ዘኢትዮጵያ!!!

 በቴዎድሮስ ጸጋዬ – ኢትዮጵያዊ
 ግርማዊ ሆይ አንድ ቅሬታ አለኝ?!?
 ጃንሆይ፤ እርግጥ ይህ ቀን የምስጋና ቀን ነው፡፡ የ“እንኳን ተወለዳችሁልን” የ “እንኳን አገራችንን ተደፍታ ከነበረበት አቀናችሁልን” እለት፡፡፡፡ ስለሆነም፣ ንጉሠነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ እና እቴጌ ጣዪቱ ሆይ፣ እነሆ በጋራ የልደት ቀናችሁ ፍቅሬን፣ ክብሬን እና ምስጋናዬን ተቀበሉ፡፡ የአባት አያቶቻችሁን የነገሥታቱን የእነአብርሃ እና አጽበሀን፣ የእነካሌብን፣ የእነገብረመስቀልን፣ የእነዳዊትን፣ የእነአምደጽዮንን፣ የእነዘርአያእቆብን ፈለግ ተከትላችሁ ወራሪ በየአይነቱ ገብቶ ያድፋፋውን የኢትዮጵያችንን ጓዳ እንደገና አደርጅታችሁ፣ ስርአት አበጅታችሁ አቅንታችሁታልና በዚህ ሁለታችሁንም ባገኘንበት ልዩ እለት ዘልአለማዊ ምስጋናዬን እንካችሁ፡፡ ሻርክ በሞላው ባህር ውስጥ በጥበብ ዋኝታችሁ፣ ጦር የያዘውን ጠላት በሰይፍ፣ ወረቀት የያዘውን አታላይ በእልፍኝ ሰልፍ አስተናግዳችሁ  ኢትዮጵያን አሻግራችሁልናልና፡፡
 ንጉሥ ሆይ፣ በዚህ በእኛ ዘመን አባትን አንቱ አይሉትም እና አንተ እያልኩ እንድቀጥል ብትፈቅድልኝ እለምናለሁ፡፡
 ግርማዊ ሆይ፣ አንድ ቅሬታ ግን አለኝ?!
 ከአህመድ ግራኝ እና ከተከተሉት የገዳ እና ሞጋሳ ስርአት ዘር ጨፍጫፊ እና ነባር ህዝብ አፍላሽ ወረራዎች በፊት የነበረችዋን፣ ጥንታዊቷን፣ ሥልጡኗን፣ ባለብዙ ቋንቋዋን፣ ነገር ግን ባለአንድ ልብ እና ሰንደቋን ኢትዮጵያ፣ የዳግማዊ ቴዎድሮስን፣ የዮሃንስ አራተኛን ውጥን በመቀጠል ትንሳኤዋን ስላበሰርክልን፣ ቀድሞ የነበራትን ሁሉም ባይሆን ሰፊ ግዛቷን ስላስመለስክልን አመሰግንሀለሁ፡፡ የሰራኸው ትንግርት ቀናችንን ይበልጥ የሚያበራ፣ ሌታችንን የሚያፈካ ነውና፤ አገር ከባለአገሩ እንዲገናኝ፣ ህዝብም ከቀደመ ማንነቱ እንዲሰናኝ፣ ስርአት እንዲጸና፣ አልጋው እንዲረጋ አስችለሀልና አደንቅሃለሁ፡፡
 ግርማዊ ሆይ፣ አንድ ቅሬታ ግን አለኝ!?
 ዳር በሌለው ምስጋናዬ፣ ወሰን በሌለው አድናቆቴ መሃል ብቅ የሚል፡፡ ስለቀደሙት ነገስታት ህልም እውን አድራጊነትህ፣ ስለአደጋ አሽታች እና ተከላካይነትህ፣ ስለአሸናፊነት ትእምርትነትህ፣ ስለምናብህ ስፋት ሁሉ አመሰግንሀለሁ፡፡ መጪውን የአለም ዳና ስለመተንበይህ፣ የኢትዮጵያችንን ነገ ስለመተለምህ፣ ከዘመንህ ስለመቅደምህ ሁሉ ሳስብ እጅጉን ደስ እሰኛለሁ፡፡
 ነገር ግን፣ አገሩን እንደገና ስታበጃጅ፣ የፈረሰውን ስታድስ፣ በወረራ ሳብያ ምድረበዳ በሆነው የነገሥታቱ ባድማ ላይ ደግመህ ህይወት ስትቀልስ፣ ስልጣኔ ስትቀሰቅስ፣ በወራሪዎች በገዳ እና ሞጋሳ ስርአት መሳርያነት ዘር እና ማንነታቸው ለተደመሰሰባቸው፣ ተጽፎም ሆነ ተነግሮ የማያልቅ ግፍ እና በደል ለተሰራባቸው ነባር ባለርስት ኢትዮጵያውያን ፍትህ እንዲበየን አለማድረግህ ያሳዝነኛል፡፡
 እርግጥ፣ ከባለሰይፍ ፍትህ ይልቅ ባለዘንባባ እርቅ ይሻላል ማለትህ ከታላቅነትህ እና ከተራማጅነትህ እንደሚመነጭ አሳምሬ እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን ግርማዊ ሆይ፣ እኔ ካንተ ባላውቅም፣ አገር ያለፍትህ አይቆምም፡፡ ምህረትም ቢሆን ፍትህን ተከትሎ ቢመጣ የተበደለው ይካስ ነበር፣ የቆሰለው ይጠግግ ነበር እላለሁ፡፡ በዳይ እና ተበዳይም፣ ነባር እና አፈናቃይም፣ ምህረት ሰጪ እና ተቀባይም ረድፋቸውን ይለዩ ነበር እላለሁ፡፡ ሁናቴውም እንዲህ ተዘባትሎ፣ የበደለው እንደተገፋ ሁሉ እዬዬ የሚልበት፣ የተበደለው ደግሞ በጨቋኝነት የሚከሰስበት፣ ወራሪው ነባሩን ሰፋሪ የሚልበት ግራ እና ወለፈንዲ አይሆንም ነበር፡፡ በገዳ ድርጅት እና በሞጋሳ ስርአት የዘር ማጥፋት የተፈጸመባቸው፣ ማንነታቸው የተደመሰሰባቸው የኢትዮጵያ ነገዶች የትላንት መከራቸው አልበቃ ብሎ፣ ዛሬም በገዛ አጽመርስታቸው መታረዳቸው፣ መገደላቸው፣ መጨፍጨፋቸው እና መሳደዳቸው ልቤን ይሰብረዋል፡፡
 ያኔ ግርማዊ ሆይ፣ አንተ አገሩን ስታቀና፣ በነባሩ እና ባለርስቱ ላይ የተፈጸመው አይነተ ብዙ ወንጀል ተዘርዝሮ፣ ቂም የማይወልድ ፍትህ ተበይኖ ቢሆን ኖሮ፣ አንተም ቸርነት ባደረግህላቸው፣ ካሳ ሊከፍሉ ሲገባ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በክብር ባጎናጸፍካቸው በእነኝያ ሰዎች ስሁት ልጆች ቀን ከሌት ባልሰራኸው ሀጢአት ባልተከሰስክ፤ እኛም ዛሬ ላይ የምናየውን የተገላቢጦሽ ግፍ እና ጭካኔ ባላየን እላለሁ፡፡
 ግርማዊ ሆይ፣ አንተ ያንን ያደረግኸው ከታላቅነት እና ከቀና ልቦና በመነጨ እንደሆነ በሚገባ አውቃለሁ፡፡ የዋልክላቸውን ውለታ እና ያገኙትን ታላቅ እድል ተገንዝበው፣ ይቅርታህን በአመስጋኝነት በህሊናቸው ጽፈው፣ የኢትዮጵያ ዕጹብ ስልጣኔ አባል መሆናቸውን በደስታ የተቀበሉት እና ያከበሩትማ የእኔው ወገን ባለሀገር ናቸው፡፡ ከእውነቱ ታርቀዋልና፡፡ በቸርነትህ ከወንጀል መንጻታቸውን ያውቃሉና፡፡ ስለኢትዮጵያ ሲሉ ህይወታቸውን በየጦር አውድማው ቤዘዋልና፡፡
 ውለታህን ክደው እጅህን የነከሱትን፣ ስምህን የሚያቆሽሹትን አፈናቃዮች፣ አራጆች፣ ጨፍጫፊዎች እና አሳዳጆች ግን በእውቀት፣ በእውነት እና በፍትህ መሟገት እና ማረቅ የትላንቱን ስህተት ማረም የእኛ የባለዛሬዎች ተልእኮ እና ተግባር ነው፡፡
 ንጉሠነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ እና እቴጌ ጣዪቱ ሆይ፣ ስላቀበላችሁን አገር፣ ስለክቡር ዜግነታችን፣ ስለመልካም ትሩፋቶቻችሁ ሁሉ አመሰግናችኋለሁ፡፡
 አርፋችሁ እንኳ ዛሬ ከምልእቷ ኢትዮጵያ መሬት ቆርሰው ጭንጋፍ እና ኩርማን አገር መመስረት የሚሹትን የቁም ሙታን ታሸብራላችሁና፡፡ አሸልባችሁ እንኳ ከኢትዮጵያዊነት ክብር ወድቀው ዘር ሲስቡ እና ሲሳሳቡ የሚውሉትን ከንቱዎች ትገስጻላችሁና፡፡እኛንም እድሜ፣ ጤና እና ጥበብ ሰጥቶ አደራችሁን ለመወጣት ያብቃን፡፡
 አሜን፡፡
 ኢትዮጵያ በቀደመ እውነቷ ትድናለች፡፡
 ተላከ ለዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠነገሥት ዘኢትዮጵያ እና ለእቴጌ ጣዪቱ ብጡል ብርሀን ዘኢትዮጵያ
#MinilikThe2nd #EthiopianHistry #HabtamuTegegne #TewodrosTsegaye #EthiopiaForever
Filed in: Amharic