>

“ ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ” (አሰፋ ታረቀኝ)

ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ”

 


 ከላይ የሰፈረው ጥቅስ፣የ 1966ቱን አብዮት ፍንዳ ተከትሎ ተከፍቶ በነበረው የውይይት መድረክ፣ ኢህአፓና መኢሶን ሲነታረኩ፣ በወቅቱ ፕሮፌሰር መረራ ጉድና ይደግፉት የነበረው መኢሶን አመራር የነበሩትና በመንግሥቱ ኅ/ማርያም ጭካኔ የተገደሉት ሐይሌ ፊዳ ላሰፈሩት አስተያየት፣ የኢህአፓ አባል መልስ ሲሰጥ የተጠቀመበት ርዕስ ነበር፡፡ ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና የወለጋው አናጺ የኦቦ ፊዳ ልጅ ሐይሌ ፊዳና የወሎው ባላባት የአቶ ጎበዜ ጣፈጠ ልጅ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ከመሰል ጓደኞቻቸው ጋር የመሰረቱት ድርጅት አባል የነበሩ ናቸው፡፡ አንዱ ከሰሜን አንዱ ከምዕራብ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ያ ትውልድ ለሁሉም የሰው ልጆች ነጻነት የታገለ እንጅ የጎሳ ከረጢት ውስጥ የተኮደኮደ አልነበረም፡፡እንደ አማሩ አይሞቱ ሆነና ነገሩ፣ ፕሮፌሰር መረራ ወጡ ወጡና ከመንከባለል አልፈው እንዘጭ አሉ፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ያልተወከሉ ጽንፈኞች በሰው ልጅ ታሪክ ወስጥ ያልነበረ ሥልተ ምርት ፈጥልረው “ የነፍጠኛ ሥርአት”  እያሉ ትውልድ ሲያደናግሩ ማስተካከል ሲጠበቅባቸው፣ ሰሞኑን በተደረገው የፓርቲወች ውይይት ላይ ሚዛኑን ከሳተ ሃምሳ አመት ያለፈውን ‘የታሪክ ትንተና’ ተንደርድረው ሲዘፈቁበት አየኋቸው፡፡ በኮሙኒስቱ ትንተና መሠረት፣ የጋርዮሽ፣ የፊውዳል፣ የካፒታሊስትና የሶሻሊስት—አራት የሥልተ ምርት አይነቶች እንዳሉ ፕሮፌሰር መረራ ከራሳቸው አለው ሌሎችን አጥምቀውበታል፡፡ “የነፍጠኛው ሥርአት” አምስተኛው ሥልተምርት ነው? ወይስ ምድቡ ከየት ነው? “የነፍጠኛው ሥርአት” የሥልተምርት አካል ከሆነ፣ በምን መመዘኛ ነው የአንድ ሔረሰብ/የአማራ ብቻ ሥርአት ሊሆን የሚችለው? ይህንን ያጭበርባሪወች ስያሜ ባለሙያወች ሊወያዩበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ጤነኛ የመሰሉን ሁሉ እየታመሙ ስለሆነ፣  በዝምታ መመልከቱን አቁሞ የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ሁሉ በ”ምሁራን” ካባ ሥር ተደብቆ  የሚዋሸውን በማስረጃ ማጋልጥ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ከ1760-1840 በአውሮፓና በአሜሪካ የተካሄደው የኢንዱስትሪ አብዮት የሰውን ልጅ ማኅበራዊ ግንኙነት ከመሠረቱ እንደቀየረው ሁሉ፣ የአደዋ ጦርነትም የሰውን ልጅ ግንዛቤና ሥንልቦና አናግቶታል፡፡ ጥቁር እንደእንሥሣት ለመነዳትና ለመገዛት ነጭ ደግሞ ለመግዛትና ለዘላለም የበላይነት የተፈጠረ አስመስሎ የተሳለውን ስነ-ልቦና መቀምቅ ያስገባ ወጤት ነው፡፡ የአድዋ ድል ለነጭ ዘር ሁሉ የትውልድ ቁስል ነው፡፡ ጦርነቱ በቁሳዊ መለኪያ ሲታይ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ወራሪ ላይ የተቀዳጀችው ድል ይሁን እንጂ በሥነ-ልቡናዊ ውጤቱ ጥቁሮች በነጮች ላይ የተቀዳጁት ድል ነበር፡፡ የአደዋ ድል በየትም አለም ለሚገኙ ጥቁሮች የጋራ ድል ሲሆን በቅኝ ግዛት ለቋመጡት ነጮች ደግሞ የማይቀበሉትም የማይክዱትም አስደንጋጭ ውጤት ነበር፡፡ የአድዋ ድል በነጮቹ ላይ ያሳረፈውን የታሪክ ጠባሳ ጥቁሮቹ ረስተነዋል፡፡ እነሱ አይረሱትም አልረሱትምም፡፡ ለዛም ነው በቅጥረኞቻቸው አማካይነት በኢትዮጵያ መቃብር ላይ “ኦሮሚያ” የምትባል ሐገር ለመፍጠርና የአጼምኒልክን ሐውልት ለማፈራርስ ሚጣደፉት፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው መጠሪያና የአጼምኒልክ ምልክቶች ክተወገዱ የአድዋ ድል የሚባል ታሪክ አይኖርም፣ የሚያስታውስም  አይገኝም፡፡ እንደጥንቱ መሳሪያ ጭኖ መዝመትና ቅኝ መግዛት ዘመኑ አልፎበታል፡፡ Scholarships በመስጠትና በመኮትኮት፣ ዶ/ር እገሌ፣ ፕሮፌሰር እንትና በማለት የጎሳ ነጋዴ መፈልፈልና ሐገር ማወክ በቂ ነው፡፡ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን ከዚያ ትውልድ የተረፉ የሐገር አድባር አድርጌ ነበር የማያቸው፡፡ ዶ/ር አብይንና የአንድነት ኅይሉን ለማስፈራራት በሚመስል መልክ፣ ኢትዮጵያን ከቀድሞዋ ሶቬየት ህብረት መፈራረስ ጋር ያመሳሰሉበት አካሄድ የሚገርም ነው፡፡ ከራሽያ ፌደሬሽን የተለዩት አገሮች በ /annexation/ በኅይል የተቀላቀሉ እንጅ በፈቃዳቸው የተከናወነ አልነበረም፡፡ ኦሮሞ ከደቡብ ተነስቶ ወሎና ጎንደር ላይ ሥርዎ-መንግሥት እስክሚመሰርት ድረስ የተጓዘውን የሕዝቦች ውህደት፣ እንደት ክሶቬየት ሕብረት መበታተን ጋር ሊያወዳድሩት እንደፈለጉ አስገራሚ ነው፡፡ ቢያንስ ለሙያቸው ክብር ሲሉ ተጠንቅቀው ቢናገሩ መልካም ነበር፡፡ ለጽንፈኛ የኦሮሞ “ተቆርቋሪወች” ክአፋሩ ልጅ ሙሳ አደምና ከሶማሌው ልጅ ሙስጠፌ መማር ቢችሉ ጥሩ ነበር፣ ጉዳዩ በነጻነት ስም የተሸፈነ business ሆነና ሰሚ አልተገኘም፡፡ ለአንባቢ ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ፣ የ “ቅኝ ገዢውን”  የአጼ ምኒልክን ባለሥልጣኖች የጎሳ ስብጥር እንመልከት፤

 1. አፈንጉስ ነሲቡ የ አብቹ ኦሮሞ ለ26 አመት የአጼ ምንልክ የፍርድ ሚንስትር የነበሩ
 2. ራስ ሚካኤል አሊ የወሎ ገዥ 
 3. ራስ ወሌ ብጡል የየጁ ገዥ 
 4. ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ የጦር ሚንስትር 
 5. ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ የሲዳሞ ገዥ
 6. ናደው አባውሎ የአሩሲ ገዥ
 7. ደጃዝማች ገብረ እግዚአብሄር ሞረዳ የወልጋ ሌቃ ገዥ
 8. ደጃዝማች ጆቴ የወለጋ ቄለም ገዥ
 9. አባጅፋር የጅማ ገዥ
 10. ፊታውራሪ ኢብሳ
 11. ፊታውራሪ ቱሉ ጅማ
 12. ቀኛዝማች አቤቤ ቱፋ
 13. ቀኛዝማች ወርዶፋ ጨንገሬ

ከላይ ክ1-13 ዝርዝር ውስጥ በህዋህትና በኦነግ የጎሳ መስፈርት መሰረት ሁሉም ኦሮሞ ናቸው፡፡ በተለይ ተራ ቁጥር  አንድና አራት በጣም ወሳኝ ቦታወች ነበሩ፡፡ እኒህን ሐገርና ሕዝብ በስስና በፍቅር ያያቸውና ይታዘዛቸው የነበሩትን መሪ ነው ህዋህትና ኦነግ ታሪካቸውን ካላጠፋን ሞተን እንገኛለን እያሉ ያለው፡፡ በ ‘ቅኝ ግዛት የያዙትን’ ሕዝብ ልጆች የመንግሥት ሥልጣን በማከፋፈላቸው ከአውሮጳው ቅኝ ግዥወች የተሻሉና ሩህሩህ ‘ቅኝ ገዥ’ አያደርጋቸውም ትላላችሁ? “አሟሟቴን አሳምረው”፤ አያቴ በቀን ሦሥት ጊዜ የሚጸልዩት ጸሎት ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መረራ ጒድና ከኢትዮጵያዊነት ማማ ላይ አወዳደቀወ ክፍቷል፤ አሟሟቴን ያሳምረው በሉ፡፡ የቀረንም ዕድሜ ትንሽ ነው፡፡ ይህች ታምረኛ ሀገር አጥፊወቿን እያጠፋች ጉዞዋን ትቀጥላለች፡፡ ያላትን በገፍ የሰጠቻቸው ጽንፈኛ የኦሮሞ ልጆች ለጥፋቷ ሲሰለፉ፣ የቀይ ባህር አንበሶችን ከአፋር፣ የምራቅ ተርቦችን ከሶማሌ ቀስቅሶ ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ እያሰኘ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አሠራር እንድህ ነው፡፡ ከማይጠብቅና ከማይታሰብ ቦታ ይጀምርና ታምር ይሰራል፡፡ ለነገሩማ “ሐገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል” ሆኖ እንጂ ስንትና ስንት የኦሮሞ ጀግኖ ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር ተጋድለው አልነበር ኢትዮጵያን በነጻነት ያቆዩን?

Filed in: Amharic