>

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ!!!

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ!!!

ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀመው «የዘር ማጥፋት ወንጀል» እንደሆነ በመግለፅ በጥፋቱ የተሳተፉ፣ ሕዝቡን ከጥቃት የመከላከል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግስት አመራሮችም በጉድለታቸው ልክ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን የመልሶ ማቋቋም ስራ እንዲሰራ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
አብን ጥቃቱ መፈፀም ከጀመረበት ዕለት አንስቶ የነቃ ክትትል በማድረግ በርካታ ወገናዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል። ጥቃቱ ወደተፈፀመባቸው ቦታዎች በጊዜው በመንቀሳቀስ ዝርዝር ማስረጃዎችን ሰብስቦ እና አጠናቅሮ በልዩ ሁኔታ በጉዳዬ ዙሪያ ለሚሰሩ የአማራ ማኅበራት እና ተቋማት አስተላልፏል። በቅርቡ በተቋማቱ በኩል ለመላው ዓለም በተለይም ለሚመለከታቸዉ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ለሆኑ ድርጅቶች እና ዓለምአቀፍ የድፕሎማቲክ ተቋማት የሚያቀርብ ይሆናል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል በሆሮጉድሩ ዞን ጃርኔጋ ወረዳ ነሽ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀመሮ በተፈፀሙ ዘር-ተኮር ጥቃቶች ከአስራ አምስት(15) በላይ አማራዎች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሲሆን በርካቶችም መፈናቀላቸውን አብን አረጋግጧል፡፡ በአካባቢው እስካሁን የጸጥታ ስጋት እንዳለም ለማወቅ ችለናል። የሕግ የበላይነትን በፅኑ እናስከብራለን በሚል የኦሮሚያ ክልል እና የፌዴራል መንግስት በቃል የገለፁትን በተሟላ መልኩ በተግባር የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው። መንግስት ይሄን ታቅዶ እየተፈፀመ ያለ የዘር ማጥፋት እና ማፅዳት ወንጀል በአስቸኳይ እንዲያስቆም አብን ይጠይቃል።
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ከነበረው ጥቃት ጋር በተያያዘ ከታሰሩት ግለሰቦች መካከል የተወሰኑትን ጉዳይ ስንመለከት ወንጀልን በሰበብነት ተጠቅሞ የፖለቲካ አመለካከትን ለመደፍጠጥ ወይም ለጥፋተኞች የፖለቲካ ሚዛን መጠበቂያነት የማዋል ዝንባሌ እንዳለ ለመገንዘብ ችለናል። በመንግስት በኩል ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ ተጣርቶ ተገቢው እርምት እንዲሰጥ አብን ያሳስባል።
በተለይም የአስራት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች የሆኑት አቶ በላይ ማናየ፣ አቶ ሙሉጌታ አንበርብር፣ አቶ ዬናታን ሙሉጌታ እና አቶ ምስጋናው ከፈለኝ የታሰሩት ለአማራ ሕዝብ ድምፅ በመሆናቸው ብቻ እንደሆነ አብን ያምናል። ለአማራ ሕዝብ ድምፅ ሆነው በሰሩባቸው ጊዜያት ሙስናን፣ ዘረኝነትን እና በሕዝባችን ላይ የሚፈፀም ግፍን ሲያጋልጡ መቆየታቸውን እያስታወስን በሌላ በኩል በዘረኛ እና ሙሰኛ የመንግስት ባለስልጣናት ቂም እንደተያዘባቸው እና አጋጣሚውን በመጠቀም ለእስር እንደዳረጓቸው መረዳት ይቻላል።
ለዘመናት በአማራ ሕዝብ ላይ ሲፈፀሙ የቆዩ ግፎች የሚዲያ ዘገባ እንዳይኖራቸው ጭምር ይደረግ እንደነበር ይታወቃል። የአስራት ቴሌቪዥን ወሳኝ ለሆኑ የአማራ ሕዝብ ጉዳዬች የሚዲያ ሽፋን በመስጠት ጉልህ ድርሸ ሲወጣ ቆይቷል። በትግሉ የተለያዩ ዘርፎች እንደታዩት በርካታ ክፍተቶች ሁሉ በድጋፍ ማነስ ምክንያት በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወንጀሎች ሲፈፀሙ የአስራት ቴሌቪዥን ከሳተላይት ስርጭት ውጭ እንደነበረ እየታወቀ በመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች በጣቢያው ላይ ሲነገር የነበረው ፍፁም የተሳሳተ ፍረጃ/ውንጀላ/ በቀጣይ የተፈፀመውን እስራት ተዓማኒነት ያሳጣዋል።
እነዚህን ጉዳዬች በተመለከተ ድርጅታችን ያለውን ቅሬታ በወቅቱ ለሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች የገለፀ እና በተደጋጋሚ ያሳሰበ ሲሆን በቀጣይ በነበሩ ጊዜያት ኃቀኛ እና ፈጣን እልባት ሊያገኙ ይችላሉ የሚል እምነት ነበረው። አብን በአንድ በኩል በግልፅ የጥፋት ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ የሚዲያ ተቋማት፣ መላ የኢትዬጵያ ሕዝብ የታዘበው የጥፋት ጥሪ እና እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ እያሳሰበ በመንግስት በኩል ከፖለቲካ አመለካከታቸው ባለፈ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ጥፋት በሌለባቸው ወገኖች ላይ የተፈፀመውን እስር ለመኮነን ውስብስብ እና ፍትኅ አልባ የሆነው የሀገራችን ወቅታዊ የማኅበረ-ፖለቲካ ቅኝት ወሳኝ ተግዳሮት ሆኖበት እንደቆየ ለመግለፅ ይወዳል።
በእስር ላይ የሚገኙት ወገኖቻችን እንቅስቃሴያቸው በሙሉ ሰላማዊ ብቻ እንደሆነና የተቀነባበሩ ጥቃቶች የተፈፀሙባቸውን ወገኖች ጉዳይ በማጋለጥ አተኩረው እንደሚሰሩ ጭምር እናውቃለን። ሁሉም ሰላማዊ መሆናቸው፣ አማራ መሆናቸው፣ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ የሰላ ትችት ሲያቀርቡ የነበሩ መሆኑን ስናስተውል የታሰሩት አጋጣሚውን በመጠቀም ለበቀል ወይም ድምፃቸውን ለማፈን እንደሚሆን ለመገመት ይቻላል።
በመሆኑም ያለምንም ተጨባጭ ጥፋት በእስር ላይ የሚገኙት የአስራት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ አብን ይጠይቃል።
አዲስ አበባ ፥ ሸዋ ፥ ኢትዮጵያ
ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በከፈተው አዲሱ የቴሌግራም ቻናል የአብን ቤተሰብ ይሁኑ!
****
ፍኖተ አብን
ይህ ቻናል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ወቅታዊና ስትራቴጂካዊ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቋሞች ለአባላት፣ ደጋፊዎችና ምልዓተ ሕዝቡ የሚቀርቡበት የቴሌግራም አማራጭ ነው።
ፍኖተ አብን
ይህ ቻናል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ወቅታዊና ስትራቴጂካዊ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቋሞች ለአባላት፣ ደጋፊዎችና ምልዓተ ሕዝቡ የሚቀርቡበት የቴሌግራም አማራጭ ነው።
Filed in: Amharic