>

ገዳ - የኤርትራ ልሂቃን (የዶ/ር አስመሮም) ነባር የመጫወቻ ካርድ!  (አሳፍ ሀይሉ)

ገዳ – የኤርትራ ልሂቃን (የዶ/ር አስመሮም) ነባር የመጫወቻ ካርድ!

 አሳፍ ሀይሉ
 ፎቶግራፍ ዶክተር (ፕ/ር) አስመሮም ለገሠ በገዳ አልባሳትና በገዳ ባህላዊ ዕቃ (ወሸላ) ተውበው፡

በነገራችን ላይ የሰው ምስጋና አትርሱ እንጂ! የገዳ ሥርዓት መኖሩን ራሱ ለኦሮሞዎች የነገራቸው ኤርትራዊው ዶ/ር አስመሮም ለገሠ ነው፡፡ የዶ/ሩ ጥናት አሁንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬኔዲ ላይብረሪ ውስጥ፣ እና በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በሚገኘው በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም (አይ ኢ ኤስ) ላይብረሪ ውስጥ ይገኛል፡፡ ማንም ሊያነበው ይችላል፡፡
ያ ጥናት በዶ/ር አስመሮም ከተሠራ በኋላ ነፍሳቸውን ይማረውና ዛሬ በህይወት የሌሉት ፕ/ር መርዕድ ወልደአረጋይ እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው የታሪክ ምሁራን የኢትዮጵያ ታሪክ መማሪያ ሲያዘጋጁ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት በሚል በኢትዮጵያ ከፍተኛ ት/ት ሥርዓት ውስጥ በታሪክ ትምህርት መስክ እንዲካተትና ዜጎች እንዲያውቁት አድርገውታል፡፡
በወታደራዊው መንግሥት (በደርግ) ዘመን ደግሞ በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችም ውስጥ ስለ ገዳ ሥርዓት በታሪክ የትምህርት ዓይነት ውስጥ ተካትቶ ለመላው ኢትዮጵያ ተማሪዎች እንዲሰጥ ተደርጎ ቆይቷል፡፡ ፀረ-ታሪክ የሆነው የወያኔ-ኢህአዴግ ሥርዓት በመጨረሻ የታሪክ ትምህርት ከናካቴው አያስፈልግም ብሎ ከየዩኒቨርሲቲዎቹ የታሪክን የትምህርት ክፍሎችን ቢዘጋም፣ ይህ የገዳን ሥርዓት ያካተተ ሞጁል ግን ለፍሬሽ (የመጀመሪያ ዓመት) የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተሰጠ ቆይቷል፡፡ አሁን የገዳን ሥርዓት እንደ አዲስ እንደ አንድ ራሱን የቻለ የትምህርት ዓይነት አድርጎ በየትምህርት ቤቱ ሁሉ ለማስተማር የተፈለገበት ምክንያቱ ግን ግልጽ አልሆነልኝም፡፡
በነገራችን ላይ ስለ ገዳው ፈጣሪ ኤርትራዊው ልሂቅ – ስለ ዶ/ር አስመሮም ለገሠ ከተነሳ አይቀር – ሁሌ የሚገርመኝ አንድ የኤርትራውያኑ ነገር አለ፡፡ ኤርትራውያኑ የ60ዎቹ ልሂቃን ለኢትዮጵያ የወደፊት የማህበራዊና ፖለቲካዊ ኃይሎች መሠረታዊ የልዩነትና የክፍፍል አጀንዳዎችን ቀርፀው ለኢትዮጵያውያን የመስጠቱን ነገር ከብዙ አሰርት ዓመታት በፊት አስቀድመው በጥንቃቄ ተዘጋጅተውበት የከወኑት መሆኑን ሳስበው ግን አርቆ አስተዋይነታቸው ይገርመኛል፡፡
ከመሬት ላራሹ አጀንዳ ጀርባ (እና ከእነ ኢህአፓ ህዝባዊ መንግሥት አሁን፣ እና የኢትዮጵያ ህዝብ የኤርትራን ህዝብ አይወጋም አጀንዳዎች ጀርባ) የኤርትራውያን ረጅም እጅ ነበረበት፡፡ በእነ ዋለልኝ እንዲቀነቀን ከተደረገው የኢትዮጵያ የብሔሮች ጥያቄ ጀርባም የኤርትራውያን እጅ አለ፡፡ ከብዙዎቹ ፀረ-ነፍጠኛ እና ፀረ-የኦርቶዶክስ ትርክቶች በስተጀርባ ረጃጅም የኤርትራውያን ቀደምት እጆች አሉ፡፡ ኢትዮጵያን እና በተለይ አማራውን እንደ ቅኝ ገዢ አድርጎ በማቅረብና – የጎሳ እንቅስቃሴዎችን ‹‹የነፃነት›› (ወይም የ‹ኀርነት›) እንቅስቃሴ አድርጎ በማቅረብና በአምሳላቸው በርካታ የብሔር ታጣቂዎችን እያሠለጠኑ በኢትዮጵያ ምድር የማሰማራት ተግባራት ከብዙዎቹ ጀርባ – የኤትርራውያን (ማለትም የሻዕቢያ-ጀበሃ) እጅ አለበት፡፡
እንደሚታወቀው ኡስማን አብደላ፣ ኡመር ኢብራሂም፣ አሊ መሀሙድ አህመድ፣ ሠላሃዲን አብደላ፣ ህያቡ ኢብራሂም (ከዋጃ)፣ እና ሌሎችም የእስልምና ተከታዮች ነበሩ የሻዕቢያ አከርካሪ አጥንት ሆነው ‹‹የነፃነት ትግል›› የሚሉትን ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ያካሄዱት፡፡ እና ብዙዎቹ ፀረ-ኦርቶዶክስና ፀረ-ክርስትና አስተምህሮቶችንና ቅስቀሳዎችን እንደ ዋነኛ ‹‹ፀረ-ኢትዮጵያ›› የትግል ማራመጃ መሣሪያነት በሰፊው ይጠቀሙበት የነበሩትም ኤርትራውያን ናቸው፡፡
የሚገርመው ሻዕቢያም ሆነ ጀበሃ በአምሳላቸው የፈጠሯቸው እንደነ ወያኔ፣ ኦነግና ጃራ የመሣሰሉ ፀረ-ኢትዮጵያ ተዋጊ ኃይሎችም – ለምን እንደሆነና ምንነቱን እንኳ ሳይፈትሹ – እንደ ዓይነተኛ ‹‹ዲኮንስትራክሽን ሬቶሪክ›› እያራመዱ የተገኙት ይሄንኑ የኤትርራ ‹‹ነፃ አውጪዎች›› በራሳቸው ምክንያትና ለራሳቸው ጥቅም አራምደውት የነበረውን የፕሮፓጋንዳ ስልትና አስተምህሮ ነው፡፡ ባጠቃላይ አሁንም ድረስ በእስልምና ተከታዩ ላይ ካነጣጠሩና ፅንፍ ከወጡ ብዛቹ ነባር ሃይማኖታዊ ቅስቀሳዎችና አጀንዳዎች ጀርባም የምናገኘው አስቀድሞ በሻዕቢያ የትግል ዘመን የተዘረጉ ረዣዥም የኤርትራውያንን እጆች ነው፡፡
እና ሳስበው ሳስበው – ኤርትራውያኑ – የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ገና በፖለቲካ ብስለትም፣ ሀገራዊ ብሶቶችንና አጀንዳዎችን አንጥሮ በመለየትም፣ በዕውቀትም፣ በትግል ጅማሮና ልምድም ገና ጮርቃ ከነበሩበት በዚያ የ60ዎቹ ጊዜ ጀምሮ እስካሁንም ድረስ ተሸክመናቸው የምንዞራቸውን ብዙዎቹን አጀንዳዎች ‹‹ሻሞ›› ብለው በትነውልን፣ እነዚያን የሙጥኝ ብለን ስንራኮት – እነርሱ የፈለጉትን ያለሙትን አጀንዳና የተነሱበትን ዓላማ – ኮንቪንስም ኮንፊዩዝም አድርገው – አሳክተዋል፡፡ ሳስበው ኤርትራውያኑ – ከእኛ እጅግ ቀድመው ሄደው ነበር – ማለት ነው፡፡
አንድ አይረሴ ገጠመኝ አንስቼ ልሰናበት፡፡ በአንድ ወቅት በባድሜው ጦርነት ወቅት በሁለቱ ሀገራት ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን አስመልክቶ በዓለማቀፉ ቀይመስቀል አማካይነት በኢትዮጵያውያን በኩል፣ እና በኤርትራውያን በኩል ያሉ የጉዳት ካሣ ይገባኛል ጥያቄዎች እንዲነሱ ለሁለቱም ሀገራት ዕድሉ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ታዲያ ከእነዚህ መድረኮች በአንዱ ላይ – በኤርትራ በኩል – አሁን ይሄን ለወሬያችን መነሻ የሆነውን የገዳን ሥርዓት ለኢትዮጵያ ኦሮሞዎች አስተዋውቆ ሀገሩ የገባው ኤርትራዊው ዶ/ር (ፕ/ር) አስመሮም ለገሠ ተቀምጦ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የዶ/ር አስመሮም የቆየ የልብ ወዳጅ የነበረው (ለእኔም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነመንግሥትና ህገፍልስፍና መምህሬ የነበረው) ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ ተቀምጧል፡፡
በዚያ ዕለት በኢትዮጵያ በኩል ከተነሱት የካሣ ጥያቄዎች መካከል አንድ አስገራሚ ‹የቆየ ክሌም› ነበረበት፡፡ ኤርትራ ስትገነጠል (ነፃነቷን ስታውጅ) ከኤርትራ ከተባረሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የቀማቻቸውን ሀብትና ንብረቶች በዋጋ ተሰልተው በካሣ መልክ ለዜጎቼ ሊመሰሉልኝ ይገባል የሚል፡፡ ጥያቄው ተገቢ ቢሆንም – የተጠየቀበት አኳኋንና መቼት ለኤትራውያኑ ተደራዳሪዎች መስሎ የታያቸው ‹‹ጉራጌ በሞተ በሰባት ዓመቱ፣ ብር ይዞ ይመጣል ትላለች እናቱ›› – እንደሚለው የልጆች ጭፈራ ነበር፡፡ ወያኔዎች በአደባባይ ክደው አፈር ምሰው የቀበሩትን እውነት – አሁን ከስንት ዘመን በኋላ ‹መጫወቻ ካርድ አገኘን› ብለው ዓይናቸውን አፍጥጠው የጠየቁበት አኳኋን የራሱ የሚገርም ነገር ነበረው፡፡
ስለ ካሣው ጉዳይ መነሳት ተገቢነት ጉዳይ ላይ በሁለቱ ወገኖች ጥቂት ክርክር ከተነሳ በኋላ በመጨረሻ – የገዳው የሳይንስ አባት ዶ/ር አስመሮም ለገሠ ጉሮሮውን አጥርቶ ተነሳና አይረሴ የሆነውን ቅስም ሰባሪ ቃል በጓደኛው በፕ/ር አንድርያስ ላይ ወረወረ፡፡ እንደዚህ ነበር ያለው፡- ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ እንኳ ብዙ መጨቃጨቅ ያለብን አይመስለኝም፣ በኤርትራ ምድር ይኖር ከነበረ አንድም ኢትዮጵያዊ ላይ፣ አንዲትም ሽራፊ ሳንቲም እንዳልወሰድን፣ ይኸው አጠገቤ የተቀመጠው ወዳጄ ፕ/ር አንድርያስ፣ በወቅቱ በአደባባይ ለዓለም ምስክርነቱን የሰጠበት ጉዳይ ስለሆነ፣ ከእኔ በበለጠ አሁንም እርሱ ደግሞ ሊያስረዳ የሚችለው ጉዳይ ይመስለኛል፣ እና እባካችሁ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጊዜ ባናጠፋ!››፡፡
እና ባጠቃላይ ኤርትራውያኑ ልሂቃን (ወደ ሻዕቢያ ቀረብ ያሉትን ማለቴ ነው) ከድሮ እስከ ዘንድሮ በጣም ይገርሙኛል፡፡ ከእኛ ቀድመው ነው የኛን አጀንዳ ቀርጸው የሚሰጡን፡፡ ከእኛ ቀድመው ነው አጀንዳ አዘጋጅተው የሚጠብቁን፡፡ ከኛ ቀድመው ነው ማን የቱጋ እንዳለና ምን እንደሚፈልግ፣ ምን ደካማ ጎን እንዳለው አውቀው ነው አስቀድመው ያዘጋጁትን ተመጣጣኝ መጫወቻ ካርድ መዝዘው የሚቆምሩት፡፡
ከብሔር ጥያቄ እስከ መገንጠል፣ ከተማ ውንብድና እስከ ገጠር ሶሻሊዝም… እስከ እስልምና፣ ከነፍጠኛና ኦርቶዶክስ እስከ ፊውዳልና ንጉሠነገሥት፣ ከአባ ገዳ ፖለቲካ እስከ ቁቤና ቀቀቤ ድረስ፣ እና ሌሎችንም የአሁን ‹‹ነፃነትን የማያውቁ ብዙ ነፃ አውጪ ነን ባዮች›› የሙጥኝ ብለው የቀሯቸውን ብዙ ዓይነት አጀንዳዎችን እንደ ጥሩ ጠራቢ ቁጭ ብለው በሥነሥርዓት ቀርፀው ‹‹እንካችሁ ተራኮቱበት›› ብለው የሰጡን ኤርትራውያን ናቸው፡፡ የሰመዓት ዓይነት አጀንዳዎችን  ወያኔን የፈጠሯት ኤርትራውያን ናቸው፡፡ ድምጥማጧን እያጠፏትም ያሉት እነርሱው ናቸው፡፡
ወያኔን እንደ ዕቃ-ዕቃ ጨዋታ በአፈርን ጭቃ ለውሰው ጠፍጥፈው የፈጠሩት እነዚሁ ኤርትራውያን ናቸው፡፡ ወያኔን 24 ሰዓት ያስቃዧት የነበሩትም እነዚሁ ጉደኞች ናቸው፡፡ አሁን ድምጥማጥሽን ልናጠፋው ነው ብለው የሚያርዷትም እነዚያው ፈጣሪዎቿ ናቸው፡፡ ኦነግን ያሠለጠኑት፣ ያስታጠቁት፣ የደበቁት፣ የፈለፈሉት፣ ያሰማሩት… እዚህም ያደረሱት እነርሱው ኤርትራውያኑ ናቸው፡፡ ኦነግን ለአብይ ጭዳ ያደረጉትም፣ በሪሞት ኮንትሮል የሚዘውሩትም እነዚሁ ጉደኛ ኤርትራውያን ናቸው፡፡
የገዳን ሥርዓት በሳይንሳዊ መንገድ ተንትነው ለኦሮሞው ያሳወቁትም፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት እንዲካተት ያደረጉትም፣ እያንዳንዳችንን (ራሴን ጨምሮ) የገዳን መሳፍንት – እነ አባ ቦኩን፣ አባ ቢያን፣ አባ ገዳን፣ ወዘተ እየሸመደድን እንድናልፍ የዳረጉንም – እነዚሁ አጃኢብ ኤርትራውያን ናቸው፡፡ አሁንም ገዳ በትምህርት ቤት መጣ፣ አሊያም እንደ ለማ ገበያም ወረደ፣ አሊያም ቤተመንግሥት ወጣ… – ብቻ ማንኛውም ‹‹መራኮቻ›› አጀንዳ ከተገኘ – በበኩሌ ከእነርሱ – ማለትም ከእኛ ቀድመው ከተገኙትና ከሚገኙት ኤርትራውያን – ራስ አልወርድም፡፡
ብቻ ሁሉ ነገራችን እንዳልነበር ሆኖ ተበሸቃቀጠ፡፡ እና ብሽቅ ሆኖ ቀረ፡፡ ሁሉ ነገር፡፡ ወንድሜ… ጉዳችን ብዙ ነው፡፡ መራኮቻችን ማለቂያ የለውም፡፡ ይኸው ሁሉንም በኤርትራ አላከኩልህ፡፡ ቀለል ይበልህ፡፡ ማመካኛ ባለማጣትህም ተመስገን በል፡፡ ቀለል ካለህ ዘንዳ ግን – ፈጠን ብለህ ንቃ፡፡ ትግላችን ረዥም ነው፡፡ ህይወት ግን አጭር ናት፡፡ የሚባክን ጊዜ የለም፡፡ የድሮ የቀይ ኮከብ ጥሪ ዜማዎች ትዝ አሉኝ፡፡ ‹‹ተነስ፣ ታጠቅ፣ ዝመት – ተደፍሯልና ያገር አንድነት››፡፡ የሚሉ የነበሩት፡፡ ሳልነሳ፣ ሳልታጠቅ፣ ሳልዘምት – ይኸው እንዳለሁ አለሁ፡፡ እንዳለን አለን፡፡ ሁሉ ነገር ጎፈየ፡፡ የሞተ ተጎዳ፡፡ ምን ዋጋ አለው?! ሺህ አምስት መቶ፡፡ ባስመራ ከተማ!! ኦሮማይ፡፡ ሴላቪ፡፡
ሠላማችሁ ይብዛ!
አንድዬ አንዲቱን ይባርክ!
አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic