>

አገራችን በውስጥና በውጭ ሽብርተኞች እየታመሰች ያለችው ኢትዮጵያዊ መንግሥት ስለሌለን ይሆን? (ከይኄይስ እውነቱ)

አገራችን በውስጥና በውጭ ሽብርተኞች እየታመሰች ያለችው ኢትዮጵያዊ መንግሥት ስለሌለን ይሆን?

ከይኄይስ እውነቱ


በወያኔ ትግሬ ይመራ የነበረው አገዛዝ ያለተጠያቂነት መጥፎ ባህል (culture of impunity) መገለጫው ቢሆንም ሥር የሰደደው ግን በዚህ ሁለት ዓመት ተኩል የዐቢይ አገዛዝ ዘመን ነው፡፡ ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን በማስረጃነት ላንሳ፤

1ኛ/ ከማለዳው ከቡራዩ ዘር-ተኮር ጭፍጨፋ ጀምሮ እስከ ቅርቡ በሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ አርሲ፣ ባሌ በኦሮሞ ጐሠኞች እና አክራሪ እስላሞች ዘርን እና ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) የመንግሥት መዋቅርንና በየደረጃው ያሉ ባለሥልጣናትን ተገን አድርጎ ሲፈጸም የተወሰደ ሕጋዊ ርምጃ የለም (ለይስሙላ ጥቂት የበታች ሹማምንቶችን የማሠር ድራማ ይፈጸማል፤ በሕግ ተፈርዶባቸው ቅጣት ሲቀበሉ ግን አይታይም/አይሰማም፡፡ ይልቁንም አገዛዙ ለማዘናጋት ሌሎች አጀንዳዎችን ለሕዝቡ ሰጥቶ እነዚህን አጥፊዎች ከሥር ከሥሩ የሚለቀቁበት ሁናቴ ነው ያለው)፡፡ 

2ኛ/ ልጃገረድ ተማሪዎች ታፍነው (በሕይወት ይኑሩ/አይኑሩ) የደረሱበት የማይታወቅባት ብቸኛ አገር የኛው ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም (ዐቢይ ኅሊና ቢኖረው በነዚህ ልጆች ጉዳይ ብቻ ሥልጣን መልቀቅ ነበረበት፤አሁን በተግባር የምናየው ግን ለሱ ሥልጣን ሲባል አገራችንም ብትጠፋ ደንታ ያለው አይመስልም፤ ለአገርና ለሕዝብ ደንታ የሌለው ሰው ስለ ፓርክ ቢያወራ ለኢትዮጵያዊ ምኑ ነው? ንቀት ካልሆነ በቀር ማንን ነው በብልጭልጭ ሊያታልል የሚፈልገው?):: 

3ኛ/ በአዲስ አበባ በሕገ ወጥ መንገድ ሕግ አሻሽሎ ሕገ ወጥ ከንቲባ ከመሾም አንስቶ ነዋሪውን ማፈናቀሉና የኔ በሚላቸው ጐሣዎች የሕዝብ ስብጥሩን የመቀየር ሕገ ወጥ ዘመቻ፣ በነዋሪው ቁጠባ የተሠሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አፓርታይዳዊ በሆነ መንገድ ለኔ ለሚላቸው ጐሣዎች ማደሉ፣ ቅጥ ያጣው የመሬት ወረራና ንቅዘት፣ ቢሮክራሲውን በአድሎ ካንድ አካባቢ በመጡ ጐሣዎች መሙላትና ሌላው ኢትዮጵያዊ እኩል የሥራ ዕድል እንዳያገኝ ማድረግ፣ በትምህርት ቢሮው በቅጥር ከሚታየው አድሎ አንስቶ ትውልድን የሚያጠፋ ተግባር እየተፈጸመ መሆኑ (አማርኛ ቋንቋን ለማዳከም በዕቅድ የሚመራው ተግባር እንዲሁም ገዳ የሚባለውንና አብዛኛውን የኦሮሞ ማኅበረሰብ የማይወክል አጥፊ የወረራና የአረመኔ ሥርዓት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት በአ.አ. ት/ቤቶች የሥርዓተ ትምህርት አካል ተደርጎ እንዲሰጥ መወሰን)፣ በልማት ስም ታሪካዊ ቅርሶችን የማጥፋት ተግባር፣ ወዘተ. በዐቢይ ዕውቅናና ቡራኬ የሚፈጸሙ ወንጀሎች/ነውሮች አይደሉም? 

4ኛ/ የድሬ ደዋ ከተማ ነዋሪዎች በሕወሓት የተጀመረው 40-40-20 የሚባለው የመድሎ የአገዛዝ ሥርዓት እንዲቀጥል ከማድረጉ በተጨማሪ ነዋሪዎች በማንነታቸው ለከፍተኛ በደል ተጋልጠው በአገዛዙ ተረኞችና ሽመልስ የኔ ነው ባለው ቄሮ በሚባለው አሸባሪ ቡድን ምክንያት ዕለት ዕለት የሥጋትና የሰቀቀን ኑሮ እንዲመሩ ሲደረጉ አገዛዙ አልፎ አልፎ የመከላከያ ኃይል የሚለውን ከመላክ ባለፈ ከፍተኛ እልቂት እስኪፈጸም ሁናቴውን በዝምታ እያለፈ መሆኑ ለዜጎች ያለውን ደንታ ቢስነትና ተጠያቂነት ያለመኖር ሌላ ማሳያ ነው፡፡

ለነዚህ ግዙፍ ጥፋቶች ከእሱ ጀምሮ እስከ ታችኛው ዕርከን ያሉ ኃላፊዎች በሕግ ተጠያቂ ሆነዋል? ይልቁንም የሚበረታቱና በሙሉ ድጋፍ የሚከናወኑ ድርጊቶች አይደሉም?

5ኛ/ ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ የሰየመው የኢትዮጵያ ግዛት ላይ ፈላጭ ቆራጭ የሆነው ቄሮው ሽመልስ አንድ ማኅበረሰብ በሌላው ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ የጥላቻ ቅስቀሳና ንግግር ከማድረጉ በተጨማሪ፣ በቅርቡ ይፋ በሆነው በአ.አ.ም ሆነ በመላው ኢትዮጵያ ላይ እየፈጸመ ስላለውና ወደፊትም በዕቅድ ስለሚፈጽማቸው አገር የማፍረስ ተግባራት ወይም የኦሕዴድ አቋም ላይ የድርጅቱ መሪ ዐቢይ ምን ዓይነት ሕጋዊ ርምጃዎች ወሰደ?

6ኛ/ የፍትሕ ሥርዓቱን ማላገጫ ሲያደርገውና እውነተኛ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ንጹሐንን ለበቀል ወኅኒ ቤት ወርውሮ በፌዝ ፍርድ ቤት፣ በፌዝ ዐቃቤ ሕግ፣ በፌዝ የፖሊስ ተቋም ሲያንገላታ ተጠያቂነት አለ ወይ?  

7ኛ/ ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ እሤቶችና ብሔራዊ ማንነት መገለጫዎች ጋር የመጣላቱ ጉዳይ ግን ኢሕአዴግ የሚባለው ቆሻሻ አገዛዝ፣ የኦነግ እና የጐሣ ድርጅቶች ሁሉ ዓይነተኛ መለያ ነው፡፡ ‹‹ፈናፍናታሙም›› ዐቢይ የነዚህ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች አካል ነው፡፡ ይህንን የምትጠራጠሩ ካላችሁ ዓይን ሳላቸው አያዩም÷ ጆሮ ሳላቸው አይሰሙም እንደተባሉት ግዑዛን ጣዖታት ወይም ግዕዛን እንደሌላቸው ፍጥረታት አእምሮና ኅሊና አልባ መሆን ነው፡፡ (የፈናፍንታምነት ገጽታውን በሚመለከት አንባቢ ከዚህ ቀደም የጻፍኩትን አጭር አስተያየት በዚህ አገናኝ ድረ ገጽ ሊያገኝ ይችላል፡፡ https://www.ethioreference.com/archives/23408)

ሊቃውንተ ኢትዮጵያ ክፋትና ተንኰሉ ሳይታወቅበት በረቀቀ መልኩ የሚፈጽምን ሰው ልዝብ ሰይጣን ይሉታል፡፡ ፈናፍንታም ባሕርይው ካልሸፈነው በቀር በአሁኑ ሰዓት የአገዛዙ አለቃ ማንነት ገሃድ እየወጣ መጥቷል፡፡ ያም ሆኖ ልዝብ ሰይጣንነትም የ‹ሰውየው› መገለጫ በመሆኑ በዚህ ረገድ ማሳያ የሚሆኑ ጥቂት ባለማድረግ/በዝምታ ያለፋቸውን ጉልህ ጥፋቶች ለማሳያ ያህል አነሳለሁ፡፡

አ/ ልዝብ ሰይጣንነት ካልሆነ በቀር አሸባሪዎችን ወደ አገር ቤት አስገብቶ አገር ሲያስፈርስ ሕዝብን በሰቈቃ ሲያምስ ባልተገኘ ነበር፤ 

በ/ ልዝብ ሰይጣንነት ካልሆነ በቀር አገር መበተኛ የወያኔ ‹ሰነድ› በደም በመሥዋዕትነት የተገኘ በመሆኑ እንጠብቀዋለን ባላለ ነበር፤ 

ገ/ ልዝብ ሰይጣንነት ካልሆነ በቀር መናገሻ ከተማችንን አ.አ. የከተማ ጠል ዘረኞችና ተረኞች መፈንጫ ባላደረገ ነበር፤ 

ደ/ ልዝብ ሰይጣንነት ካልሆነ በቀር አባ ዱላን የመሰለ ከርሳም ወንጀለኛ የደቡቡን ክፍለሃገር ለመበተን ወይም ቄሮው ሽመልስ እንዳለው በራሳቸው መልክ ጠፍጥፈው ለመሥራት ባልሾመውና በወላይታ ሕዝብ ላይ ግፍ ባልፈጸመ ነበር፤ 

ሀ/ ልዝብ ሰይጣንነት ካልሆነ በቀር ጣናን እያደረቀ ሰው ሠራሽ ሐይቅ እገነባለሁ እያለ ባልተሳለቀብን ነበር፤ 

ወ/ ልዝብ ሰይጣንነት ካልሆነ በቀር ዜጎች በማንነታቸውና በሚከተሉት እምነት ምክንያት የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምባቸው ብሔራዊ የሐዘን ቀን ማወጅ፣ በቦታው ተገኝቶ ማፅናናትና ካሣ እንዲያገኙ በማድረግ መልሶ ማቋቋም የመሪ ወጉ በነበር፤

ዘ/ ልዝብ ሰይጣንነት ካልሆነ በቀር አገር አዝኖ ልቅሶ ተቀምጦ ሳለ በራስ ፍቅር/በግል ዝና ሰክሮ ዘጋቢ ፊልም እዩ እያለ አገራዊ ምጸት ባልፈጸመ ነበር፤ 

ሐ/ ልዝብ ሰይጣንነት ካልሆነ በቀር የዕርቅና የወሰን ኮሚሽኖች እያለ በኢትዮጵያ ሕዝብ ባልቀለደ ነበር፤ 

ኀ/ ልዝብ ሰይጣንነት ካልሆነ በቀር ‹ልዩ ኃይል› የተባለ ሕገ ወጥ የታጠቀ የጐሣ ቡድን በመላው አገሪቱ በተለይም የምርጫ ማኅበራዊ መሠረቴ ነው በሚለው ክ/ሀገር፣ የአገር መከላከያን በሚገዳደር አቋም ሲደራጅ ዝም ብሎ ባልተመለከተ ነበር፤ 

ጠ/ ልዝብ ሰይጣንነት ካልሆነ በቀር የድርጅቱን የቀድሞ የሕወሓት ነውረኛ ባህል ባህሉ አድርጎ ፓርቲ እና መንግሥት ተለዋዋጭ ሆነው እንዲቀጥሉ ባላደረገ ነበር፤ በተመሳሳይ መልኩ የፓርቲ ሠራተኞች ለፓርቲው ለሚሰጡት አገልግሎት ክፍያ ሲፈጸም የኖረው ከመንግሥት በጀት መሆኑ አሁንም ባልቀጠለ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም እንደገለጽኹት ምርጫ ይደረጋል በተባለበት ጊዜ የዐቢይ ድርጅት ኦሕዴድ የሕዝብ/የመንግሥት ሀብትና መዋቅሮችን ተጠቅሞ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደረገውን ውድድር ትርጕም አልባ አድርጎት ነበር፡፡ እንቀጥል ካልን ዝርዝሩ ማለቂያ የለውም፤ ለአብነት ያህል የተዘረዘረው ይበቃናል፡፡

በቡሃ ላይ ቈረቈር እንዲሉ ዐቢይ እመራዋለሁ የሚለው አገዛዝና የሚመራው ‹የፖለቲካ ድርጅት› ኢትዮጵያዊነትን ‹ነፍጠኝነት› እያለ አምርሮ የሚጠላ በመሆኑ ኢትዮጵያን በውጭ አሸባሪ ቡድኖች ጭምር እያስደፈራት ይገኛል፡፡ ሰሞኑን ስለ ‹አይ ኤስ እና አልሻባብ› እየተነገረን ያለው እውነት ከሆነ (አገዛዙን አላምነውምና)፡፡ እውነቱን ለመናገር እነዚህ የሽብር ኃይሎች አገራችን ገብተው ጥፋት እያደረሱ ከሆነ፣ ለም መሬቱን የፈጠረላቸውና ተጠያቂው አገዛዙ ነው፡፡ ለምን? በጐሣ እና በአክራሪ እስልምና ሽፋን ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት የፈጸሙ ሀገር-በቀል አሸባሪዎች የመንግሥትንና የኦሕዴድን መዋቅሮች ተጠቅመውና በየደረጃው ባሉ ባለሥልጣናት ታግዘው መሆኑ ገሃድ በመውጣቱና አሸባሪው ጀዋርና ማኅበሩ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑ የአንዳንድ ዐረብ አገራት የጥፋት ተልእኮ ተሸካሚዎች በመሆናቸው፡፡ በዚህ ሴራ ውስጥ አሸባሪው ሕወሓት የለበትም ማለቱ ሥዕሉን የተሟላ አያደርገውም፡፡ 

ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ነውና፡፡ ኢትዮጵያን በጐሣ የተከፋፈለችና የምትናቈር ደካማ አገር ማድረግ ቀድሞ በወያኔ አሁን በኦሕዴድ የሚመራው ኢሕአዴግ የሚባል ነውረኛ ድርጅት ዕቅድና ፍላጎት ነው፡፡ ደካማም አድርገዋታል፡፡ በነገራችን ላይ አገዛዞች ሕዝብ እምነት ሲያጣባቸው ሆንብለውም ሆነ መካር ባለመፈለግ በሚፈጽሙት አገራዊ ስህተት እንደ ዐባይ ግድብ ዓይነት ብሔራዊ የሚመስል አጀንዳ ይፈጥሩና ባንድ በኩል ተቀባይነት ለማግኘት፣ በሌላ ወገን ዋና ከሆነው አገራዊ ጉዳይ ሕዝብን ለማናጠብ ይጠቀሙበታል፡፡ ለእኔ ከአገር ህልውናና ከሕዝብ ደኅንነት የማስቀድመው ብሔራዊ አጀንዳ የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል በአያት ቅደመ አያቶቻችን አጥንትና ደም ተከብራ አሁን ያለንበት ዘመን የደረሰች ብሔር (አገር) ህልው ሆና ስትቀጥል፣

  • ያለፉትን ግማሽ ምእተ ዓመታት የጥላቻ፣ የቁርሾ እና ያለመተማመን ምዕራፍ የምንዘጋበት እውነተኛ ዕርቀ ሰላም ማውረዱን፤
  • በአገዛዞች በደል ለደረሰባቸው ዜጎች እውነተኛ ፍትሕና ርትዕ እንዲሁም ካሣ የሚያገኙበትን ሁናቴ ማመቻቸት፤
  • አንኳር በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች (የታሪክ አረዳድ፣ የጐሣ/ዘር ፖለቲካ፣  ሕገ መንግሥት እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች /ቅርፀ መንግሥት፣ ሥርዓት መንግሥት፣ ዋና ከተማ፣ ብሔራዊ ቋንቋ/ዎች፣ ሰንደቅ ዓላማ ወዘተ./ እውነተኛ ብሔራዊ መግባባት የምንደርስበትን፤
  • ሕዝብ የሚሳተፍበት አዲስ ሕገ መንግሥት የመጻፍ፤
  • ይህንንም ተከትሎ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በማድረግ ኢትዮጵያውያን በሙሉ (የጐሣ/ነገድ፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የፆታ፣ ሌሎችም ማንነቶች ወዘተ. ልዩነት ሳይደረግ) በእኩልነት የሚታዩበት ሥርዓት (ሕዝበ መንግሥት) ማቆም፤
  • እግዚአብሔር በቸርነቱ ያደለንን የጋራ የተፈጥሮ ሀብታችንን በፍትሐዊነት በመጠቀም ሕዝባችንን ከድህነት አላቅቆ ለተሻለ ዕድገት መሥራት፡፡

 

በመጨረሻም ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በቀጣናው የበላይነት ለመያዝ ኃያላን አገሮች ግዙፍ ወታደራዊ ኃይሎች ያሠፈሩበት መሆኑ ቢታወቅም፣ ይህ ሁናቴ ለኢትዮጵያ ሰላምና ጸጥታ ቀላል የማይባል ተጽእኖ እንዳለው ብንገነዘብም፣ እንደ አይ ኤስና አልሻባብ ያሉ አሸባሪዎችም የመሸጉበት መሆኑ እንግዳ ነገር ባይሆንም፣ ሕዝባችንን በጐሣ ከፋፍሎ እና የኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ላይ የማያቋርጥ ጥቃት በመፈጸም ኢትዮጵያን ማዳከም የታሪካዊ ጠላቶቻችንና የራሳቸው ልዩ አጀንዳ ያላቸው የውጭ ኃይሎች እጅ መኖሩ ዛሬ የተጀመረ አለመሆኑን በሚገባ ብናውቅም፣ ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበትን ቀውስ ውጫዊ ለማድረግ መሞከር በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም፡፡ ቊልፍ ችግራችን ኢትዮጵያዊነትን መሠረት ያደረገ ውስጣዊ አንድነትና ኅብረት መጥፋቱ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የጐሣ ፖለቲካው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አገራችን ጐሣዊ አገዛዝ እንጂ ኢትዮጵያዊ መንግሥት አለመኖሩ ለውጭ ኃይሎች ጥቃት በእጅጉ አጋልጦናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አገዛዝ በራሱ መርገም ነው፡፡ ጐሠኛነት ሲጨመርበት ጽላሎተ ሞት (በጨለማ ላይ የዛፍና የገደል ጥላ ሲጨመርበት እንደማለት) ማለት ነው፡፡ 

በነገራችን ላይ እነዚህ በሥልጣንና ዘረኛነት የናወዙት የኛ ደናቁርት ተሳክቶላቸው ትናንሽ የመንደር ‹አገዛዞችን/መንግሥታትን› መመሥረት ቢችሉ ዛሬ አገር በማፍረሱ የሚያግዟቸው የውጭ ኃይሎች መጫወቻ ባሮች እንደሚሆኑና እንደሚንቋቸው ያውቃሉ? የኢትዮጵያዊነት ክብርና ኩራት ባንድ ጀምበርና በብላሽ የተገኘ እንዳይመስለን፡፡

ስለዚህ ሳይረበሹ ሁሉን በጥንቃቄና በማስተዋል መከታተል ያሻል፡፡ አገዛዙ ዕለት ዕለት በሚሰጠን አጀንዳዎች አጥንት እንዳዩ ጉንዳኖች በዙሪያው ከመሰባሰብ ትኩረታችንን ዐበይት በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማድረጉ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

Filed in: Amharic