የፕሮፈሰር መረራ ጉዲና ነገር!
አቻምየለህ ታምሩ
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ትናንትና ከጀርመን ድምጽ የአማርኛው ክፍል ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “በፋሽስት ወረራ ወቅት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለአምስት ዓመታት ያህል እንግሊዝ አገር ቢቆዩም ኢትዮጵያን ሊያዘምን የሚችል ትምህርት ግን ከአውሮፓውያን አልቀሰሙም” ብሎ ሲተች ሰሟሁት። ይገርማል!
የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ሰው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንግሊዝ አገር ባዝ ከተማ መኖር የጀመሩት ከሐምሌ 12 ቀን 1928 ዓ.ም. ጀምሮ ነው። ሰኔ 17 ቀን 1932 ዓ.ም. ደግሞ ወደ አገራቸው ለመመለስ ከእንግሊዝ ተነስተው ወደ ሱዳን ሄዱ። ይህ ማለት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንግሊዝ አገር የቆዩት ሶስት ዓመት ከአስራ አንድ ወር ወይም ካጠጋጋነው ለአራት ዓመታት ያህል ነው።
የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመኗ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴዋ ኢትዮጵያ ከማንኛውም የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዘመናዊ አገር ተቋማት ጋር ተወዳድረው የማያሳፍሩ ዘመናዊ ተቋማትን ገንብታ ነበር። ከፋሽስት ጥሊያ ወረራ በኋላ የተፈጠሩት እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ቴሌ ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል፣ የአውራ ጎዳና መስሪያ ቤት፣ ወዘተ አይነት ተቋማት በዘመኑ ከየትም አገር ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ተወዳድረው የማያሳፍሩ ተቋማት ነበሩ።
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴዋ ኢትዮጵያ በትምህርት በኩል ወደ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተገፍታ የገባች አገር ነበረች። እነ ፕሮፌሰር መረራ ከተማሩበት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በምስራቅ ኢትዮጵያ በነበረው የሐረር የጦር አካዳሚ፣ ሸዋ በነበረው የደብረ ዘይት አየር ኃይል ኤርትራ በነበረው የምጽዋ ባሕር ኃይል የነበረው የመኮንኖች ሥልጠና ሁለገብና በጣም ከፍተኛ ነበር። እነዚህ ተቋማት ከኢትዮጵያውያን አልፈው በየአገሮቻቸው መሪዎች፣ ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች መሆን የቻሉ አፍሪካውያንንም ማሰልጠን ችለው ነበር።
የትኛውም አፍሪካ አገር ውስጥ በማይቻልበት ሁናቴ የኢትዮጵያ ገበሬ ልጆች ከአህያና ፈረስ ግልቢያ ወጥተው መኪና እንኳን ማሽከርከር ሳይችሉ አውሮፕላን ለማብረር እንዲበቁ፤ ባሻገር የቦረና እረኛ፣ የኢሉባቦር ፍየል ጠባቂ፣ የጅግጅጋ ግመል ተከታይና የጎጃም አፈር ገፊ ልጆች በዝነኞቹ የኦክስፎርድ፣ የሀርቫርድ፣ የየል፣ የሶርቦን፣ የኮሎምቢያ ወዘተ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲማሩ ያስቻለችዋ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴዋ ኢትዮጵያ ነበረች።
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመኗ ኢትዮጵያ የተጀመረው የእርሻ እድገት ኢትዮጵያ ራስዋን ከመቻል አልፋ የእርሻ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረብ የቻለችበት ደረጃ ላይ አድርሷት ነበር። የዚህ ጥረት ውጤት ንጉሡ ሲወርዱ ኢትዮጵያ በነበራት የውጭ ምንዛሬ ክምችት ታይቷል። የፕሮፈሰር መረራ ጉዲና ድርጅት የነበረው የመኢሶን አመራርና የደርግ ሹም የነበረው አንዳርጋቸው አሰግድ “ባጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ” በሚለው መጽሐፉ ገጽ 120 ላይ እንደነገረን ደርግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ካዝማ ውስጥ ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዳገኙ ነግሮናል። ይህ የውጭ ምንዛሬ ክምችት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመኗ ኢትዮጵያ የግብርናና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትሩፋትና የእርሻ ምርት ወደ ውጭ በመላክ የተገኘ ብሔራዊ ሀብት ነው።
በነገራችን ላይ በ1967 ዓ.ም. የነበረው 600 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ በዛሬው ገበያ ሲተመን 3.2 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል። ወያኔ ተወግዶ የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ወደ ስልጣን ሲመጣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ካዝና ውስጥ 3.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አልነበረም። ልብ በሉ! ራሱን እንደ ልማታዊ መንግሥት ይቆጥር የነበረው የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አግዛዝ የሆነው 28 ዓመታት የገዘገዘን ወያኔ ሲወገድ በብሔራዊ ካዝናችን ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ አድሐሪ ተብሎ የተወገዘው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ሲወርድ በብሔራዊ ካዝናችን ውስጥ ተከማችቶ የተገኘው የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ወደ ዛሬ ዘመን ዋጋ ሲተመን ይበልጥ ነበር።
ባጭሩ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ «የብርና የወርቅ እዮቤልዩ አከበሩ» እየተባሉ የሚጠቀሱት ፋብሪካዎች፣ ሚንስትር መስሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ አየር ማረፊያዎች፣ ግድቦች፣ ወዘተ በሙሉ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እነዚህ ሁሉ ተቋማት ሊገነቡ የቻሉት በፋሽስት ጥሊያን ወረራ ወቅት እንግሊዝ አገር በቆዩባቸው አራት ዓመታት ውስጥ በቀሰሙት ትምህርት እየተመሩ ነበር።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን እንግሊዝ አገር አምስት ዓመታት ሲቆዩ ኢትዮጵያን ሊያዘምን የሚችል ትምህርት አልቀሰሙም በማለት የሚከሳቸው የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ሰው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ሁለት ዓመታትን፤ በአውሮፓዊቷ አገር በኔዘርላድ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ አራት ዓመታትን ባጠቃላይ ስድስት ዓመታትን ከኢትዮጵያ ውጭ ሲማር ቆይቷል።
አውሮፓ አራት ዓመታት የቆዩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ አገራቸው ሲመለሱ በአውሮፓ ቆይታቸው በቀሰሙት ትምህርት ቀደም ብዬ የዘረዘርኳቸውን ተቋማት ሲገነቡ፤ አሜሪካና አውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ስድስት ዓመታት ያህል ፖለቲካል ሳይንስ የተማረው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ግን ወደ አገሩ ሲመለስ በተማረው ትምህርት ለኢትዮጵያ ያስገኘው ትሩፋት ቢኖር የሰማኒያ ዓመት አዛውንት ከቤታቸው ጎትተው በማስወጣት በዱልዱም የሚያርዱና አስከሬናቸውን አስር ቦታ በሜንጫ ከቆራረጡ በኋላ የአዛዉንቱን የእጅ ቁራጮች እንደ አጣና ወደላይ በመስበቅ <<ነፍጠኛ ይውጣ>> እያሉ የሚጨፍሩ፤ አማራ አያሳየን ብለው “አማራ ኦሮሞ መሬት ላይ አይወለድም” በማለት የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር በልጆቿና በባለቤቷ ፊት አንጋለው የሚያርዱ፤ በግፍ ያረዷቸው ንጹሐን አፈር እንዳይለብሱ <<ኦሮሞ መሬት ላይ አማራ አይቀበርም>> በማለት አስከሬናቸውን አሞራና ጅብ እንዲበላው የሚያደርጉና ሕልም ያላቸው እድሜ ልካቸውን ለፍተው በቋጠሩት ጥሪት የፈጠሩትን ሀብት ዶግ አመድ የሚያደርጉ ቄሮዎችን ነው።
ይታያችሁ! በአውሮፓ የአራት ዓመታት ቆይታቸው በቀሰሙት ትምህርት ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ይበጃሉ ብለው ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን በዘመነ መንግሥታቸው የገነቡትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን “ከአውሮፓ ቆይታቸው አልተማሩም” በማለት የሚከሰው ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና በአውሮፓና አሜሪካ እየኖሩ የሰው ልጅን ብቻ ሳሆን እንስሳት እንኳን እንዴት እንደሚከበሩ እያዩ ትምህርት ከማይቀስሙ፣ ከትምህርትም ሆነ ከኑሮ ከማይማሩ ጭፍኖች፣ በትኛው ዘመን ላይ እንዳሉ እንኳ እየኖሩ እንደሆነ ማሰብ ከተሳናቸው የኦሮሞ ብሔርተኞች በሚያገኘው የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ እየታገዘ ውሎ አበልና መኪና መድቦ ከገጠር በሚያስመጣቸው ሰው ለማረድ የሰለጠኑ አውሬዎች ንጽሐንን የሚያስቀላው ሰውዬ ነው።
በእውነቱ በአውሮፓ ቆይታው ሥልጣኔ ያልተማረው ማነው? በአራት ዓመት ቆይታቸው በቀሰሙት እውቀት በነበሩበት በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከየትም አገር ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ተወዳድረው የማያሳፍሩ ተቋማትን የገነቡት የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ሰው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወይስ ስድስት ዓመታት ሙሉ አሜሪካና አውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተምሮ በማንነታቸውና በሃይማኖታቸው እየለዩ በዱልዱም የሚያርዱና በሜንጫ የሚቀሉ ቄሮዎችን ያሰለጠነውና ወደፊትም በዱልዱም የሚያርዱበትንና በሜንጫ የሚቀሉበትን የፖለቲካ ስንቅ እየፈጠረ ለመንጋዎቹ እንካችሁ የሚለው የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ሰው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ነው? እስቲ ፍረዱ?!
ከታች የታተመው ታሪካዊ ፎቶ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአውሮፓ ቆይታቸው በቀሰሙት ትምህርት ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ይበጃሉ ብለው በዘመነ መንግሥታቸው ከገነቧቸው ተቋማት መካከል ከፊሉን የሚያሳይ ስዕላዊ መግለጫ ነው። ስዕላዊ መግለጫውን ያገኘሁት ጆፍሬ ላስት በ1961 ዓ.ም. History of Ethiopia in Pictures በሚል ባሳተመው መጽሐፍ ገጽ 51 ላይ ነው።