>

“የኦሮሞ ጥያቄ እና ፈተናዎቹ...!!!" (አሰፋ ሀይሉ)

“የኦሮሞ ጥያቄ እና ፈተናዎቹ…!!!”

አሰፋ ሀይሉ
  በምሥጢር የተሸጠልኝ የሞቲ ቢያ መጽሐፍ!
ጥቂት ወራት ቀርተዋል፡፡ የኦሮሞና የአማራ የኢህአዴግ አንጃዎች ውስጥ ለውስጥ ተማክረው ወያኔን ከቤተመንግሥት ሊያፈናቅሉ፡፡ ልደታ ቤተክርስትያን አካባቢ የፆም በያይነቱ ሲያምረኝ ጎራ ብዬ የምመገብባት አንዲት ጥቂት ደምበኞች ያሏት አነስተኛ ምግብ ቤት አለች፡፡ ካጠገቧ ባለው ትልቅ ፎቅ አናት ላይ የምወደውን ፓስታልፉርኖ በስፕራይት ከማለፊያ ቡና-ያለስኳር ጋር ለመልከስከስ ከኪሴ 60 እና 70 ብር መፈተሽ ይኖርብኛል፡፡ የምፈተሽባቸው ቀናት የዋዛ አልነበሩም፡፡ ግን ደግሞ ይቺኛዋ ዛኒጋባ ምግብ ቤት እንደኔ ላለው የወር ደሞዝተኛ የሚስማማ ጥሩ ቅናሽ አላት፡፡ ፎቅ ውጡኝ ሳትል፣ ሳትራቀቅ፣ ሳታካብድ፣ ቢል ይምጣልህ፣ ባል ይምጣብህ ሳትል፣ 40 ብር ባልሞላ ገንዘብ በቀላል-በቀላል ሽርር የምልባት ቤት ስለሆነች – ለለውጥ ያህል – ካለፍ ገደም በፍቅር እቀላውጣታለሁ፡፡
እውነት ለመናገር ምግቦቿ ግሩም ናቸው፡፡ ልክ የቤት-የቤት ምግብ ይላሉ፡፡ በዚያ ላይ ገጠር ያበቀላት የምትመስል ቆንጅዬ ተቆጣጣሪ፣ እና ልጅ-እግር ፈገግተኛ አስተናጋጆች አሏት ምግብ ቤቷ፡፡ የዕጣኑ ጭስ፣ የሚቆላው ቡና፣ የሚጎዘጎዘው ሣር፣ የተመጋቢውና የአስተናጋጆቹ ለከፋና ቀልዶች፣ ይሄ-ይሄ ሁሉ በጠባቧ ማዕድ ቤት ውስጥ ተቀምጠህ ባይን የሚገባ የነፃ ግብዣ ያክል ነበር፡፡ ብቸኝነት አይሰማህም፡፡ ምሳህን በልተህ እስክትወጣ ባዕድነትህን አውጥተህ ትጥላለህ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደሞ ቤቷ ቀለል ስለምትላቸው ይሁን አላውቅም – ባለ 5፣ 10፣ 15 ብር የሞባይል ሲም ካርዶች፣ ማስቲካ፣ ናፕኪን፣ ለውዝ፣ ወዘተ የያዙ ህጻናት – አሁንም አሁንም በበሯ በፍጥነት ገባ ብለው፣ ተመጋቢውን ቃኘት ደርጉና – ተቆጪ ሳይመጣባቸው በመጡበት በፍጥነት ወጣ ይላሉ፡፡
ከሁሉም የሚያስደምመኝ ደሞ የመጽሐፍት ሻጩ ልጅ-እግር ወጣት ነው፡፡ የምግብ ቤቷ ደጃፍ ላይ ቆሞ ለአላፊ አግዳሚው ያሉትን የመጽሐፍት አርዕስት እየጠራ ይሸጣል፡፡ ዴርቶጋዳ፣ ፍቅር እስከ መቃብር፣ የሣጥናዔል ጎል በኢትዮጵያ፣ ኦሮማይ፣ የስንብት ቀለማት፣ ሴቶችን በፍቅር የማንበርከክ ኃይል፣ ታቦተ ፅዮንን ፍለጋ፣ … ሁሉም መጻሕፍት አሉኝ – ጋሼ መጽሐፍ ግዙ – እናት በርካሽ ዋጋ ለእርስዎ ለልጆችዎ ዕውቀት ሸምቱ – ሁሉም ዓይነት መጽሐፍ በተመጣጣኝ ዋጋ…! እያለ መንገደኛውን በተለያዩ ርዕሶችና ማባበያዎች ሊማርክ ይባክናል፡፡ ልጁ የሚገርመኝ ባንድ ጊዜ ሁለት ቦታዎችን የሚቆጣጠርበት አቴንሽኑም ነው፡፡ የምግብ ቤቷ ደጃፍ ላይ ሆኖ ለአላፊ መንገደኞች መጻሕፍቱን እየሸቀለም – በተመሣሣይ ሰዓት ደግሞ – በምግብ ቤቷ ምሳ ለመቀላወጥ የገቡ ተመጋቢዎች በየትኛዋ ደቂቃ ምግባቸውን ጨርሰው፣ እጃቸውን ታጥበው፣ ለተከታዩ ሻይና ቡና ወይም ለሂሳብ እንደሚዘጋጁም – ትክክለኛ ቅፅበቷን አይስታትም፡፡ ውጪ ላይ ቆሞም ቀልቡን ወደ ማዕድ ቤቷ ይልካታል፡፡ አስገራሚ የኑሮ ‹‹ሳይመልታኒየስ ኢኩዌሽን››!
እና ልክ እጅህን ታጥበህ ወደ መቀመጫህ ስትመለስ – መጻሕፍት ሻጩም ልጅ – አኳኋንህን አይቶ – ዓይነ-ውሃህን አጢኖ – ለአንተ ሊመስጥህ ይችላል ብሎ የገመታቸውን መጻህፍት አፈስ አድርጎ – ጠጋ ይልሃል፡፡ አንዴ እንደዚህ ያለኝን አልረሳሁትም፡፡ ‹‹ጋሼ ለእርስዎ የሚሆኑም መጽሐፎች አሉኝ… እንዳይሸጥ የተከለከለው… ‹ኢህአዴግን እከሳለሁ› የሚለው መጽሐፍ አለኝ፣ ‹የኦሮሞ ጥያቄ እና ፈተናዎቹ› የሚለውም አለኝ፣ ‹የመለስ ልቃቂቶች› አለኝ… ‹የኤርትራ ጉዳይ›ም… አለኝ – እኚውልህ..!›› ብሎ እየመዘዘ በመዓት አበቦች ሥዕል የተዥጎረጎረ የፕላስቲክ ጨርቅ በለበሰችው አራት ማዕዘን የእንጨት ጠረጴዛዬ ላይ መጻሕፍቱን በቅፅበት ደረደረልኝ፡፡
የአደራደሩ ስብጥር ልክ የጾም በያይነቱህን በልተህ ስትጨርስ፣ ፍስክ በያይነቱ – ወይም የመጻሕፍት ሴኮንዶ ሚስቶ – እንደቀረበልህ ዓይነት የሚመስል ለዛ ነበረው፡፡ ለመጻሕፍት ሻጩ ልጅ – አኳኋኔን ሲያየኝ – የተከለከሉ መጸሕፍትን የማስስ ዓይነት ሰውስ መስዬ እንዴት ልታየው ቻልኩ? እያልኩ ለአፍታ እያሰብኩ – ምፀቱ ፈገግ አሰኘኝ፡፡ እና ባልገዛውም ለጥረቱ ልጁን ደስ ይበለው ብዬ – ሳልወድ በግድ – ከቀረበልኝ የመጻሕፍት ‹ዲዘርት› ውስጥ – አንዱን መልከት እንደማድረግ ብዬ አነሳሁ፡፡ “የኦሮሞ ጥያቄ እና ፈተናዎቹ’ ይላል፡፡ የሞቲ ቢያ ስብስብ ሥራዎች ባንድ ላይ ተጠቃልለው ከአዲስ አርትዖት ጋር የቀረቡበት መጽሀፍ ነው፡፡ ይላል መግቢያው፡፡
ሰሞኑ – የፖለቲካ ውጥረት፣ የቄሮ ግርግሮች፣ የጎንደርና ባህርዳር የተቃውሞ ሠልፎች፣ የአስቸኳይ አዋጅ፣ የልዩ ኃይል ኮማንዶዎች ቅኝት፣ እስር፣ ግድያና መፈራራት የነገሠበት ሰሞን ነው፡፡ ሰሞኑ ህወኀት በኦሮማራ አንጃዎች ልትባረር ጥቂት ወራት ብቻ የቀሩት ሰሞን ነው፡፡ ለዚህ ሰሞን ደሞ ሰሞነኞቹ መጻሕፍት በሥልጣን ላይ ያለውን የወያኔ-ኢህአዴግ መንግሥት የሚነቅፉ መጸሕፍት ሆነው ተገኝተዋል፡፡ እና ለመጻህፍት ሻጩ – አኳኋንህን አይቶ ‹‹ባለጊዜ›› የሚያስመስልህ ምልክት ካላገኘብህ – ነፃ ሰው ነህ ማለት ነው፡፡ እና ‹‹መንግሥትን›› የሚያብጠለጥልልህን ‹‹ምሥጢራዊ›› ጥራዝ በተባልከው ዋጋ የመግዛት ፖቴንሻሉም አለህ ማለት ነው፡፡ እና ያቀርብልሃል፡፡ አሳቀኝ፡፡ የበዓሉ ግርማ ‹ኦሮማይ› ተከልክሎ በድብቅ ይሸጥ የነበረበት የ70ዎቹ ዘመን በህሊናዬ አቃጨለብኝ፡፡
እና የሞቲ ቢያን ምዕራፎች ዝርዝር ከማውጫው ገጽ ላይ ተመለከትኩ፡፡ የወያኔ ፋሺስታዊ ሥርዓት ማክተም፣ የነፍጠኛው ኃይል መንኮታኮት፣ የኦሮሞ ልጆች መስዋዕትነት፣ የአዲስ ለውጥ ፈላጊዎች የትብብር ኅብረት መፍጠር አስፈላጊነት፣ ብዙ ነገሮች ተደርድረዋል፡፡ ‹ኦኬ› ለክፉ አይሰጥም፡፡ ‹አፍተር ኦል› ጠፍቷልም፣ ሞቷልም ሲባልለት የሰማሁት የኦነግ ሳተና ፀሐፊ የሞቲ ቢያ መጽሐፍ ነው፡፡ ላንብለት እስቲ፣ ምን ይለኛል? ጠየኩት ልጁን፡፡ ‹‹ስንት ነው ዋጋው?››፡፡ ልጁ አላቅማማም፡፡ ‹‹100 ብር!›› አለኝ፡፡ ዋጋውን በጀርባው ፈለግኩ፡፡ ቅናሽ የለም፡፡ ቅናሽ እንዲያደርግልኝ ጠየቅኩት፡፡ ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚያገኘው ትርፍ 5 ብር ብቻ መሆኑን ነገረኝ፡፡ 5 ብር ብቻ! በዚያ ላይ ፖሊስ ከያዘው እንደሚታሠርም – ያለበትን የ‹ቢዝነስ ሪስክ› እየተሳቀቀ ነገረኝ፡፡
ሞቲ ቢያ ካጓጓኝ በላይ – መጽሐፍ ሻጩ ልጅ አንጀቴን በላው፡፡ እና 100 ብሬን – ከተቀመጠችበት የኋላ ኪስ ዋሌቴ ውስጥ ፈልቅቄ – በአበባ ምንጣፍ ባጌጠው ጠረጴዛ ላይ ፈጠፈጥኳት፡፡ ‹‹አመሠግናለሁ ጋሼ፣ ሌላ ጊዜም የምትፈልገውን ዓይነት መጽሐፍ ንገረኝ፣ ባይኖረኝ እንኳ በትዕዛዝ አመጣልሃለሁ!›› ብሎ እየተደሰተ ወደ ደጃፉ ሥራው ተመለሰ፡፡ እኔም አመስግኜው የምግብና የቡና ሂሳቤን ከእግዜር ውሃ ጋር አወራርጄ ወጣሁ፡፡
አንዳንዴ አይጣል ነው፡፡ ፎቁ ላይ ወጥተህ ምሳህን ብትበላ – አላግባብ የምትፈለጠውን ሂሳብ ሽሽት በመሸግክባት ዛኒጋባ ምግብ ቤትም ውስጥ ብታደፍጥ – አንድዬ ውጪ ያላት ገንዘብ ካለች ትወጣለች፡፡ ሂሳቤን በኳድራቲክ ኢኩዌሽን አሰላሁት፡፡ 100 ብር የመጽሐፍ፡፡ 35 ብር የምግብ፡፡ 3 ብር የጀበና ቡና፡፡ 2 ብር የፍልቅልቋ አስተናጋጅ ‹ቲፕ›፡፡ የእግዜር ውሃ በነፃ፡፡ ጠቅላላ ሂሳብ 140 ብር፡፡ ለምሳና ተያያዥ ጉዳዮች፡፡ በዚህ ከቀጠልኩ – ወሩ መጨረሻ ላይ የምገኘው – በማንኛውም ሰዓት ዱለት በ15 ብር፣ የፆም ፓስታ በ12 ብር፣ ቡና በ1.25 ብር በሚሸጥባት – በጥንቷ በጠዋቷ – የፊሊፕስ የሠራተኞች መዝናኛ ክበብ ውስጥ ነው፡፡ ሌላ መሄጃ አይኖረኝም፡፡ እያልኩ – የሞቲ ቢያን መጽሐፍ ጨብጬ – በራሴ እየቀለድኩም፣ እያሟረትኩም ወጣሁ፡፡
ቅዳሜ መጣች፡፡ ከወዳጆቼ ጋር ሰብሰብ ብለን የሳምንቱን ወጎች የምካድምባትን የቅዳሜ ልዩ ቀኔን ጠብቄ – ጊዜው ባለፈበት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የሸፈንኳትን የሞቲ ቢያን “የኦሮሞ ጥያቄ እና ፈተናዎቹ’” መጽሐፍ ባረኳት፡፡ ብዙዎቹ ሃሳቦች ድሮ ከሞቲ ቢያ ብዕር የወጡና የተባሉ ነገሮች ሆነው አገኘኋቸው፡፡ በእርግጥ ከቀደመው ኦነጋዊው የሞቲ ቢያ አቋም ለዘብ ባለ መልኩ የውግዘቱ ቶን ከተለመደው ‹‹ነፍጠኛ›› ላይ ይልቅ ‹‹ፋሺስታዊ›› ነው ባለው የዘመኑ የወያኔ አገዛዝና ግፎቹ ላይ እንደሚያተኩር ልብ ብያለሁ፡፡ ነገር ግን አዲስ ነገር ልለው የምችለው ብቸኛ ሃሳብ ቢኖር – አንድ የትግልና የሥልጣን አሰላለፍ ግብዣን ወይም ትንቢትን ማካተቱ ብቻ ነው፡፡
ሞቲ ቢያ – በዚህ መጽሐፉ – አማራው (ማለትም ‹‹ነፍጠኛው አማራ››) ኢትዮጵያ የምትባለውን ለዘመናት ገዝቶ – ጊዜው አልፎበት – እና እንዳያንሰራራ ሆኖ ተንኮታኩቶ – በትግሬው የወያኔ ፋሺስታዊ አገዛዝ እንደተተካ ይናገራል፡፡ የወያኔ ፋሺስታዊ አገዛዝ ከአማራው ላይ ተረክቦ የትግሬን አገዛዝ በኢትዮጵያ ላይ አስፍኖ መቆየቱን ያትታል፡፡ እና አሁን የወያኔ ፋሺስታዊ አገዛዝ ጊዜው እንዳበቃለት፣ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው እንጂ የወያኔ የትግራዋዮች አገዛዝም እንዳከተመለት ይናገራል፡፡ የወያኔ አገዛዝ ልክ እንደ ነፍጠኛው አገዛዝ ላይመለስ የሚንኮታኮትበት ቀን ሩቅ እንዳይደለ ይናገራል፡፡ ለአማራውና ለሌሎች የኢትዮጵያ ‹‹ብሔሮች›› እና ‹‹ሕዝቦች›› የሚበጃቸው – ከኦሮሞ ተጋድሎ ጎን አብረው በመሰለፍ – ሊወድቅ አንድ ሐሙስ የቀረውን የወያኔን አገዛዝ በማንኛውም መንገድ (በሠላማዊም በሌላም መንገድ) ተፋልሞ ወደ መቃብሩ የሚሸኝበትን ቀን የማፋጠን ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሆነም ይመክራል፡፡
የሞቲ ቢያ አነጋገር እጅግ ግልጽ ነው፡፡ አማራ ገዝቷል፡፡ ትግሬ ገዝቷል፡፡ አሁን ደሞ ጊዜው የኦሮሞ ነው፡፡ ተንኮታኩቶ የተቀበረውን የነፍጠኛ ሥርዓት አማራው አነግሣለሁ ብሎ ቢነሳ – ይላል ሞቲ ቢያ – ፍጻሜው ‹‹ከወደቁ ወዲያ መንፈራገጥ ለመላላጥ›› መሆኑን ቃል በቃል ይናገራል፡፡ ማንም ሰው መጽሐፉን ካለበት አግኝቶ ሊያነበው ይችላል፡፡ እና አማራው ሞቶ የተቀበረውን ነፍጠኛ ሥርዓቱን እመልሳለሁ የሚለውን ከንቱ ምኞቱን ትቶ – ከኦሮሞ ጋር መተባበር አለበት፡፡ ኦሮሞው በአማራውና በሌሎች ብሔሮች ትብብር – የወያኔን የትግሬ አገዛዝ አሽቀንጥሮ ከጣለ በኋላ – በኦሮሞ የምትመራ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንደምትመሠረት – ለዚህ ለማይቀረው የታሪክ ጉዞ በተለይ አማራው ከጨቋኟ ወያኔ ራሱን አላቅቆ – ጊዜና ታሪክ ከሚጠይቀው ከጭቁኑ የኦሮሞ ሕዝብ ጎን በትግል አጋርነት እንዲሰለፍ ጥሪ ያቀርባል፡፡ ካልተሳሳትኩ እንግዲህ – ከጥቂት ወራት በኋላ ‹‹አሮ-ማራ›› በሚል ስም የታወቀው ስትራቴጂ ነበር – ማለት ነው እንግዲህ – የኦነጉ ብዕረኛ ሞቲ ቢያ – ጥርት አድርጎ ያለምንም መደባበቅ እያስተጋባ የነበረው አቋም፡፡
መጽሐፉን እንደጨረስኩ የመጣብኝ – ለብዙዎች እንደ ሞቲ ቢያ ብዙ ያከረረ አቋም የያዘ መስሎ የማይታያቸው – የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ‹‹ዳንዲ የነጋሶ መንገድ›› የተሰኘ መጽሐፍ ነበር፡፡ ያም መጽሐፍ የሚናገረው ተመሳሳይ ነገር ነበረው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ – የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነቱን መቀዳጀት እንዳለበት ይናገርና – ነገር ግን በስትራቴጂ ደረጃ ኦሮሞው ብቻውን ሆኖ ይሄን ዓላማውን ማሳካት እንደማይችል ይናገራል – እና ኦሮሞው የራሱን ጉልበትና አቅም እስኪያጠናክር ድረስ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ብሔሮችና ሕዝቦች ጋር ሆኖ የወያኔን ሥርዓት መታገል እንዳለበት ነበር አስረግጦ የጻፈው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፡፡ እና ለነጋሶ የኦሮሞ ህዝብና የሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብር ጊዜያዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ነበር፡፡ እንጂ የተክሊል ጋብቻ አልነበረም፡፡ ኦሮሞው የራሱን ነጻነት በጉልበቱ እስኪያውጅ የሚከተለው ስልት ነው፡፡ ገርሞኝ ነበር በወቅቱ፡፡ እንደ ነጋሶ ከለዘበ ሰው ይህ ከወጣ…፡፡ ብዙዎች ከነጋሶ ለስለስ ያሉ አቋሞች በስተጀርባ ይህን አስገራሚ ያገነገነ አቋሙን ያልተመለከቱ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ደግመው ‹ዳንዲ – የነጋሶ መንገድ›ን – እንዲያነቡት እመክራለሁ፡፡
ያኔ የዶ/ር ነጋሶን አቋም ሳነበው አስገርሞኝ ነበር ብያለሁ፡፡ አሁንም የሞቲ ቢያን ሳነበውም ደግሞ ገረመኝ፡፡ ‹‹ጅል በትክክል የመጨረሻውን ትልቁን ግርምት ከመገረሙ በፊት፣ ብዙ ጊዜ እየደጋገመ ይገረማል›› የሚል የአንድ የዌስተርን ምሁር አባባል ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ማን እንዳለው ግን ጠፍቶኛል፡፡ ራስል ይሁን ኤመርሰን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እና እኔም የመጨረሻውን ግርምት ተገርሜ እስኪወጣልኝ ድረስ – እንደ ጅል – ደጋግሜ መገረሜን አላቋርጥ አልኩ፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ገረመኝ፡፡ ሞቲ ቢያ ገረመኝ፡፡ ኦነግም ገረመኝ፡፡ መለስ ዜናዊ አስቀድሞ ‹‹እንደ ፈጣን ሎተሪ ብትፋቁ ኦነግ ናችሁ›› ያላቸው – እና የሞቲ ቢያን መጽሐፍ በማነብበት ሰዓት ወያኔን ከውስጥ ሆነው እየገዘገዙት የነበሩት ኦህዴዶችም ገረሙኝ፡፡ ውስጥ ውስጡን ካድሬዎቹን እያስተባበረ በወያኔ ላይ አመጽና ተቃውሞ ያቀጣጥል የነበረው የአማራው ጉድ ብአዴንም ገረመኝ፡፡ ሁሉም ገረሙኝ፡፡ ሁሉም የአንድ ብሔር የበላይነትን እንደ ‹ኖርማል› የታሪክ ሂደት፣ እና አማራጭ እንደሌለው ነባራዊ ሀቅ ቆጥረው አሜን ብለው ያንን እውን ለማድረግ መዘጋጀታቸው ገረመኝ፡፡ ገረሙኝ እስካፍንጫዬ ድረስ፡፡
አማራ ገዝቶ ተንኮታኩቷል፡፡ ትግሬ ገዝቶ ሊንኮታኮት አንድ ሐሙስ ቀርቶታል፡፡ ኦሮሞ ሊገዛ ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ተረኛው ሙሽራ መጥቷል፡፡ በርበሬያችሁን ቀንጥሱ፡፡ አበባችሁን በትኑ፡፡ ጉሮ ወሸባዬ ብላችሁ ንጉሡን ተቀበሉ፡፡ እልልታችሁን አሰሙ፡፡ ገንዘብ ያለህ በገንዘብህ፣ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ መሣሪያ ያለህ በመሣሪያህ፡፡ ወደድክም ጠላህም ታሪክ የኦሮሞን የገዢነት ተራ መስክራለችና ሁልህም የተረኛውን ገዢ የኦሮሞን የሥልጣን ትግል አምነህ ተቀበል፡፡ በያለህበት ሆነህ የኦሮሙማን የሥልጣን ትግል ሳታቅማማ ተቀላቀል፡፡ ከኦሮሞው ተረኛ ጋር ከተባበርክ – የቱሩፋቱ ተቋዳሽ ትሆናለህ፡፡ ተረኛውን እጋፈጣለሁ ካልክ ግን – የወያኔን ዕድሜ ጥቂት ታራዝም ይሆናል እንጂ – አብረኸው ትቀበራለህ፡፡ ራሴን ችዬም ኦሮሞውን ተጋፍቼ በተረኝነት ወደ ገዢነት ልምጣ ብለህ እንዳታስብ፡፡ የምታስብ ካለህም በወያኔ ላይ የተቀጣጠለው የኦሮሞ የትግል ሠይፍ አንተንም ይበላሃል፡፡ እያንዳንድህ – እያንዳንድሽ – በተለይ አማራ – ትክክለኛ አሰላለፍህን አሳምር – ከኦሮሞ ጋር አብር – እና ወያኔን ወደማይመለስበት መቃብሩ ተጋግዘን እንሸኘው! የሚል ወቅታዊ የትግል ጥሪ ነበር፡፡ ሞቲ ቢያ ከጠፋበት ብቅ ብሎ በመጨረሻው ቁርጥ ሰዓት ላይ ያቀረበው፡፡
ሞቲ ቢያ ገረመኝ፡፡ የቆመለትን ብሔርተኛ አጀንዳ ለማራመድ ምንተ እፍረት የለውም፡፡ ዓይኑን አያሽም፡፡ ሳይደባብቅ ፍላጎቱን ይናገራል፡፡ ሳይደባብቅ የሚመጣውን የኦሮሞ ተረኛ ገዢነት ይመሰክራል፡፡ ልክ ሰሞኑን አደባባይ ወጥቶ እንደሰማነው እንደ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር ማለት ነው፡፡ ወይም በአንድ ወቅት አፈትልኮ አንደሰማነው የለማ መገርሳ የ‹ዲሞግራፊ እንቀይራለን› ንግግር ማለት ነው፡፡ ገረመኝ በጣም፡፡ ሞቷል፣ ጠፍቷል ሲባል የነበረው ትንቢተኛው የኦነግ ሳተና ብዕረኛ ሞቲ ቢያ፡፡ ሞቲ ቢያ ብቻ አይደለም፡፡ ወይም ነጋሶ፣ ወይም ሽመልስ አብዲሳ፣ ወይም ለማ ብቻ አይደሉም፡፡ የወያኔን የተረኛ ገዢነት ሳይንሳዊነትና ታሪካዊነት በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየተነተኑ ብዙ መጻህፍትን ያዋልዱ የነበሩት የወያኔዎቹ ምሁራን እነ ፕሮፌሰር ክንፈ አብርሃም በጊዜያቸው እንዲሁ ይገርሙኝ ነበር፡፡
በዓለም ታሪክ የምናውቀውና ድሮ በኢትዮጵያም ታሪክ የሚጻፈው የሥልጣን ታሪክ የንጉሣን ሥልጣን መፈራረቅ ነበር፡፡ ምናልባት ለ300 ዓመት የቆየው የዛግዌ ዙፋን እና የሠሎሞናውያኑን ሥልጣን ተክቶ መፈራረቅ በዳይናስቲ ደረጃ ያለ መፈራረቅ ተደርጎ ሊወሰድ ይችልም ይሆናል፡፡ በተረፈ በይፋት፣ አዳልና ፋጠጋርም የወላዝማ ዳይናስቲ፣ ወዘተ ስለሚባለው ቤተሰባዊ የሥልጣን አገዛዝ ፈረቃዎች እንዲሁ በታሪክ ተጽፎ አንብበን ይሆናል፡፡ በተረፈ ግን ሥልጣንን ከግለሰብ አሳልፈው፣ ከቡድንም፣ ከቤተሰብም አሳልፈው – ወደ ክፍለ-ሀገርነት ደረጃ አስፍተው ከፍ ያደረጉት ‹ሥልጣን ከትግራይ እጅ ወጥቶ ወደ ሸዋ እጅ ገባ› እያሉ ይጽፉ የነበሩት የትግራይ ሎካል የታሪክ ጸሀፊያን እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ አሁን ደሞ ሀገሩን ሁሉ የሞሉት – ሁሉም የወያኔ ዘመን ያገነናቸው የታሪክ ፀሀፊዎች፣ የፖለቲካ ተንታኞችና ምሁራን (ወይም ሲውዶ-ምሁራን) ደግሞ – ታሪክንና ንግሥናን ወይም ሥልጣንን የሚረዱበት እና የሚያውቁበት ብቸኛ መንገድ እና የሚታያቸው ብቸኛው ነገር  – የነገሠ ወይም የተሻረ ብሔር ሆኗል፡፡ ድሮ የሥልጣን ጀስቲፊኬሽኑ – በፈጣሪ መቀባት ነበር፡፡ ቀጥሎ ቤተሰባዊ የዘር ሀረግ ሆነ፡፡ ቀጥሎ አይዲዎሎጂና ሰፊው ህዝብ ሆነ፡፡ አሁን ደሞ ሰፊው ብሔር የሥልጣን ጀስቲፊኬሽን ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ማለት ነው፡፡
በእነ ሞቲ ቢያ አስተሳሰብ ከብሔር ‹አምቢሽን› ሌላ – የራሱ ግለሰባዊ አምቢሽን፣ የራሱ ዓላማና የራሱ የሥልጣን ፍላጎት ያለው መሪ ወይም ሥልጣን-ፈላጊ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ሊፈጠርም አይችልም፡፡ አሁን ያለው ብቸኛ የሥልጣን ፈላጊም፣ የሀገር መሪም –  ግለሰብ ወይም ሌላ ቡድን ሳይሆን የአንድን ብሔር ሕዝብ ለማንገስ የመጣና የሚመጣ አካል ብቻ ነው፡፡ አሁን ተተካኪ ንጉሥ የለም፡፡ ተተካኪ ብሔር፣ ተረኛ ገዢ ብሔር ግን አለ፡፡ መኖርም አለበት፡፡ የፍትሃዊነት መለኪያውም ቀድሞ ሥልጣን ተነፍጎት ቆይቷል የተባለ ብሔር ሥልጣን ላይ የመውጣቱ ፍትህ ነው፡፡ የእኩልነት መለኪያውም ቀድሞ ሌሎችን እንደገዙ ብሔሮች እርሱም ሌሎችን ገዢ ለመሆን የመብቃት እኩልነት ነው፡፡
በዚህ የጊዜያችን የፖለቲካ ትርክት የባለሥልጣን እና የመሪ መለዋወጥ የለም፡፡ የብሔር ፈረቃና የገዢነት ተራ መለዋወጥ ብቻ ነው ያለው፡፡ እና የሚኖረው፡፡ በዚህ የተሳከረ ቀመር ነው ዓለማዊ እይታቸው የተዋቀረው፡፡ ስለዚህ አማራ የሚባለው ብሔር ነግሧል፡፡ ትግሬ የሚባለው ብሔር ነግሧል፡፡ አሁን ደግሞ ኦሮሞ የሚባለው ብሔር ይነግሣል፡፡ ነው ሁሉም ትርክት፡፡ እና ታሪክ፡፡ ‹ስቴትሁድ›ን፣ ‹ናሽናል አይደንቲቲ›ን፣ የዜጎችን ‹ሶሊዳሪቲ›፣ ‹ኔሽንሁድ› የሚባለውን ለአንድ ሀገር አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ.. እንዴት እናጠናክር፣ እንዴት እንገንባ፣ እንዴት እንፍጠር፣ ህዝቦችን እንዴት እርስበርስ እናስተሳስርና አንድ የጋራ ሀገር እንፍጠር፣ ወዘተ የሚባል የሌሎች ዘመናይ መንግሥታትንና ህዝቦችን የሚያስጨንቃቸው ጭንቀት እኛ ጋር የለም፡፡ ማን ተረኛ ገዢ ብሔር ይሁን የሚል ጭንቀት ብቻ፡፡
በአንድ ወቅት ‹‹ኦሮሚያን በፈረቃ? – አቢሲኒዮክራሲ ወይስ ዲሞክራሲ›› በሚለው መጽሐፉ ሞቲ ቢያ እንዲህ ብሎ ጽፎት ነበር፡- ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ በአምቻና ጋብቻ ማንነቱን አያጣም፡፡ ሌሎች አናሳ ብሔሮች ኦሮሞ ማንነታችንን አሳጣን ሊሉ ይችላሉ እንጂ፣ ኦሮሞ ከሌሎች ጋር በመጋባት ማንነቱን አያጣም፡፡ የነፃነት ጥያቄያችን በጋብቻ ምክንያት አይጨፈለቅም፡፡ ኦሮሞ የኢምፓየሪቱ ብዙሃን ሕዝብ ነው፡፡ ለመቶ አመታት ሞክረውታል፡፡ ኦሮሞ ሌላውን ይለውጣል እንጂ ወደ ማንም አይለወጥም፡፡››
ይሄ ማለት እንግዲህ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በደም፣ በጋብቻ፣ በታሪክ ለዘመናት የተዛመድነው ዝምድና የፈጠረብን ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም፣ ኦሮሞ ኦሮሞ ነው፣ ሌላውን ወደኛ እናመጣለን እንጂ እኛ ወደማንም አንሳብም፣ አንዛነቅም፣ አንዋሃድም – እንደማለት መሆኑ ነው፡፡ የእነ ሂትለርን ‹‹ፒዩሪቲ ኦፍ ብለድ፣ ፒዩሪቲ ኦፍ ማይንድ፣ እና ፒዩሪቲ ኦፍ ስፒሪት›› የሚሉ የአርያን ዘሮች ከማንም ዘር ጋር አይደባለቁም፣ አይዛመዱም፣ የጋራ ማንነት የሚባል አይኖርም የሚሉ የናዚ ዘመን መፈክሮችን ያስታውሰኛል ይሄ አባባል፡፡ ይገርማል፡፡ እንደ ሀገር ያሳለፍናቸውና የስንት ትውልድ ደም ያፈሰስንባቸው እነዚያ ሁሉ የአብሮነት ታሪኮች በዜሮ ተባዝተው – አሁን ተፈጥፍጠን የተገኘንበት የታሪክ ምዕራፍ እጅግ ይገርማል፡፡ ይገርማል ብቻም ሳይሆን ስለ ሀገር የሚጨነቅ አዕምሮ ላለው ያሳዝናልም፡፡
በመጨረሻ ሞቲ ቢያን ፅንፍ በረገጡ ኦነጋዊ አስተሳሰቦቹ ባልጋራውም የወያኔን የዘረኝነት አስተሳሰብ የወለደው ሀገራዊ ጭቆና ግን ገና ከጧቱ በአስገራሚ የተባ ብዕሩ ሲያብጠለጥል የኖረ አንደበተ ርቱዕ ፀሐፊ እንደነበረ ብዙዎች እንደሚመሰክሩለት ሁሉ እኔም ለልቡና ለችሎታው አድናቆቴን ሳልቸረው ባልፍ ቅር ይለኛል፡፡ ሆኖም – ሞቲ ቢያም ሆነ – ሌሎች ኦነጋዊውን ጽንፍ የረገጡ የኦሮሞ ብሔርተኝነት አቀንቃኞች – ከዚህ በፊት በኦነግ ፊታውራሪነት መሬት ላይ የተፈተሸውን የብረቱንና የባሩዱን መራር መንገድ በትንሹም ቢሆን ሞክረው አስከፊ ውጤቱን ያዩት ይመስለኛል፡፡ ኪሣራው ከባድ ነበር፡፡ አሁንም ከፅንፍ በወጣ ብሔርተኝነት የወለደው አምሮታቸው – በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉትም ሆኑ፣ የመንግሥትን ሥልጣን ተጎራብተው ያሉት ኦነጋውያን – ያን የቀደመውን ኪሣራ አሁንም እንዳይደግሙት ከልቤ እመኝላቸዋለሁ፡፡
አንዳንዴ መጻፍ በፈለግከው ሰዓት አይመጣም፡፡ እንደ ዛር ነው፡፡ ዛር ሆኖ ከመጣ ደግሞ አቆመዋለሁ ብለህ አትሞክረውም፡፡ አሁን 4ኛ ገጼን እያስገባደደኝ ነው፡፡ 5ኛ ገጽም ሳልገባ አልቀርም፡፡ ገጽ ሲበዛ፣ አንባቢ ይጠነዛል፡፡ የሞቲ ቢያ ጽሑፍ ከ300 ገጾች በላይ የጨረሰ ይመስለኛል፡፡ ከትውስታ በግምት ነው የምናገረው፡፡ ሞቲ ቢያ በ300 ገጾች ካሰለቸኝ በላይ – 4 እና 5 ገጾቼ አንባቢዎቼን ክፉኛ እንዳያሰለቹብኝ ፈራሁ፡፡ ምክንያቱም ጊዜ የለም አውቃለሁ፡፡ ጊዜ የለም፡፡ መዘናጋት የለም፡፡ ጊዜው የሩጫ ነው፡፡ ሰው ሰክኖ ተቀምጦ የሌላን ሰው አዋዋልና አስተሳሰብ የሚያነብበት ጊዜ የለውም፡፡ ሰው “የኦሮሞ ጥያቄ እና ፈተናዎቹ’ን የሚያነብበት ጊዜ የለውም፡፡ በ“የኦሮሞ ጥያቄ እና ፈተናዎቹ’ ላይ የተጻፈን ማስታወሻም የሚያነብበት ጊዜ የለውም፡፡ የማንበቢያ ጊዜ ጠፋ፡፡ አንባቢ ጠፋ፡፡ ፅሁፍ ረከሰ፡፡ ወረቀት ተወደደ፡፡ ‹ኦንላይን› በዛ፡፡ ፀሐፊ በዛ፡፡ ጎመን ጠነዛ፡፡ ጊዜ ክቡር፡፡ ብቻ ጊዜን የሚሰጥ አንድዬ ጊዜን እንዲሰጠን እመኛለሁ፡፡ እነሆ የጽሑፍ ዛሬን 5ኛ ገጼ ላይ ወጊድ ብዬ፣ ባለ 300 ገጹን ሞቲን አመስግኜ፣ ብዕሬን ከደንኩ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡
Filed in: Amharic